>

የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ባልደራስ አባላትና ደጋፊዎች በጅምላ እየታሰሩ ነው!!! (የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ)

የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ባልደራስ አባላትና ደጋፊዎች በጅምላ እየታሰሩ ነው!!!
 የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ
(ኢትዮ 360) የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ባልደራስ አባላትና ደጋፊዎች በጅምላ እየታሰሩ መሆኑን  የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አስታወቀ።
ጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ እስክንድር ነጋ ለኢትዮ 360 እንደገለጸው  አባላቱና ደጋፊዎቹ  ወንጀላቸው ምን እንደሆነ ባልታወቀበት ሁኔታ ውስጥ በፖሊስ በጅምላ እየታፈሱ ነው።
በዚህም የተነሳ ለነገው ሰልፍ የሚያደርገውን ቅስቀሳ አቋርጦ የታሰሩትን ለማስፈታት ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።
ደጋፊና አባላቱ የታሰሩት በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ቢሆንም የተቻለውን ሁሉ በማድረግ እስረኞቹን ለማስፈታት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጿል።
እስክንድር ነጋ እንዳለው የጅምላ አፈሳው የተጀመረው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባላደራው የጠራው ሰልፍ እውቅና እንደሌለው ከማስታወቁ ቀደም ብሎ ነው።
የፖሊስ ኮሚሽኑ ይህን ቢልም ባላደራ ምክር ቤቱ ግን ቀጣይ ሂደቶችን በተመለከተ ያለውን  አቋም ግልጽ እንደሚያደርግ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከኢትዮ 360 ጋር ባደረገው ቆይታ አስታውቋል።
የኢትዮ 360 ዘጋቢዎች በየአካባቢው ተዘዋውረው እንደዘገቡት የአዲስ አበባ ፖሊስ ባላደራው የጠራውን ሰልፍ ለማስተጓጎል የጅምላ እስሩን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ከትላንት ጀምሮም ከአማራና ከኦሮሚያ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ ጉዞዎች መንገድ በመዝጋት መስተጓጎላቸውንም ገልጸዋል።
ሕገወጥ ድርጊቱ እስካሁን መቀጠሉ የታወቀ ሲሆን መንገደኞችም በቤተክርስቲያንና መንገዶች በተዘጉባቸው አካባቢዎች እንዲያድሩ መገደዳቸውን ዘግበዋል።
የመንገድ መዝጋቱም ሆነ ህገወጥ ድርጊቱን ቄሮ የሚባለው ቡድን እየፈጸመ ያለው  ከፖሊስ ጋር በጋራ በመቀናጀት መሆኑን የኢትዮ 360 ዘጋቢዎቹ ከስፍራው ያደረሱት መረጃ ያመለክታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የአዲስ አበባ ምክር ቤት ባልደራስ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኤርሚያስ ለገሰ ለኢትዮ 360 እንዳለው ፖሊስ ሰላማዊ ሰልፍ የማገድ ስልጣን የለውም።
በህግ የተሰጠው ስልጣን ካለም በግልጽ ለህዝብ ሊያሳውቅ ይገባል ሲል ገልጿል።
Filed in: Amharic