>
7:03 am - Wednesday December 7, 2022

በወያኔ ሕገ መንግሥትም ቢሆን ሕጋዊው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ፣ ቢጫና፣ ቀይ ሶስት ቀለማት ያሉት ሰንደቅ ዓላማ ነው!  (አቻምየለህ ታምሩ)

በወያኔ ሕገ መንግሥትም ቢሆን ሕጋዊው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ፣ ቢጫና፣ ቀይ ሶስት ቀለማት ያሉት ሰንደቅ ዓላማ ነው! 
አቻምየለህ ታምሩ
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሶስት ቀለማት ናቸው። የሰንደቅ ዓላማው ሦስቱ ቀለማት እኩል ሆነው አግድም የተቀመጡ ሲሆን ምሳሌያቸውም አረንጓዴው ተስፋ፣ ልምላሜና ሀብት፤ ቢጫው ሃይማኖት፣ አበባና ፍሬ፤ ቀዩ ደግሞ ፍቅር፣ መስዕዋትናነትና ጀግንነት ነው። አንዳንድ ሲባል የሰሙትን ሳይመረምሩ የሚደግሙ ካድሬዎች ይህንን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ «ልሙጡ ሰንደቅ ዓላማ» ወይም «የድሮው ሰንደቅ ዓላማ» እያሉ ይጠሩታል። ይህ ግን የደጋሚዎቹን አጥልቆ ያለማሰብ ችሎታና አለማንበባቸውን እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማን  ትናንትና ዛሬ የሚያሳይ አይደለም።
ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እስከ ወያኔ ዘመን ድረስ ያለውን ጊዜ ብንወስድ እንኳ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አንድም ቀን ቢሆን  በተለያየ ደረጃ ይሁን እንጂ ከፍ ብሎ ሳይውለበለብ የዋለበት ቀን የለም።  ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. አዲስ አበባ ሲገቡ  በብሔራዊ ቤተ መንግሥት  የሰቀሉት፤ በደርግ ዘመን የወራሪው የዚያድ ባሬ ጦር ድል ከተመታ በኋላ ሌተናት ኮሎኔል ደሳለኝ አበበ የካቲት 26  ቀን 1970 ዓ.ም. ካራማራ ተራራ ላይ ያውለበለበው፤ በኢትዮጵያውያን ከባድ መስዋእትነት በሻዕብያ  ተወርሮ ለሁለት አመታት ቆይቶ የነበረው የባድመ መሬት ሲለቀቅ የባድመን ድል ለማብሰር በባድመ ምድር የካቲት 19 ቀን 1991 ዓ.ም ከፍ ብሎ የተውለበለበው  የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ምንም አርማ ያልተደረተበት አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያሉት  የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ  ብቻ ነው።
በመሆኑም ካለማሰብ ካልሆነ በስተቀር አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ «የድሮው ሰንደቅ ዓላማ» የሚያስብል ነገር የለውም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት፣ በደርግ የአገዛዝ ዘመንም ሆነ በወያኔ የመከራ ዘመናት ሲያውለበልበውና ባባቶቹ ታሪክ መኩራቱን ሲገልጽ የኖረው አያት ቅድመ አያቶቹ በነገድ፣ በሃይማኖትና በጾታ ሳይወሰኑ በዱር በገደሉ የተዋደቁለትን የኢትዮጵያ ጀግኖች ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ ነው።  አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩን  የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ «የድሮው ሰንደቅ ዓላማ» እያሉ የሚጠሩ ካድሬዎች ይህን ሰንደቅ ዓላማው በወያኔ ዘመን ያልተውለበለበ አድርገው የሚያስቡ አላዋቂዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ሌላው ቢቀር  በወያኔ ዘመን በአካል ተገኝተው  ባድመ ላይ የካቲት 19 ቀን 1991 ዓ.ም ከፍ ብሎ  የተሰቀለውን  አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩን  የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ ባያዩ እነ ደራርቱ ቱሉ፣ ኃይሌ ገብረ ሥላሴና ጌጤ ዋሜ አይነት የኢትዮጵያ አትሌቶች በአለም መድረክ ከፍ አድርገው እንዲውለበለብ  ሲያደርጉትና በደስታ ሲያለቅሱበት በቪዲዮ የተመለከቱትን አለማስተዋላቸውና  የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማውን  እስካሁን ድረስ ያለማቋረጥ የሚያውለበልበው ሰንደቅ ዓላማው እንደሆነ አለማወቃቸው የሚታዘልናቸው ያደርጋቸዋል።
በሕገ ደረጃም ቢሆን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥትም ሆነ የደርግ አገዛዝ በጻፏቸው ሕገ መንግሥቶች ውስጥ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ  ሆኖ የተደነገገው አረንጓዴ፣ቢጫ፣ ቀይ ቀለማት ያሉት ሰንደቅ ዓላማ ብቻ ነበር።
የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 120 ስለ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሚከተለውን ደንግጓል
______________________
«[የኢትዮጵያ] ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ ቀለም ካላይ ከመጀመሪያው አረንጓዴ፤ መካከለኛው ቢጫ፤ ከታች መጨረሻው ቀይ ሆኖ በአግድም የሚደረጉ ሦስት ቀለማት ናቸው»
______________________
ሲባል የሰሙትን የሚደግሙ  ካድሬዎች በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበረው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ  «ሞአ አንበሳ» ያለበት ነው  እያሉ  «ያ ትውልድ» የፈበረከውን የፈጠራ ታሪክ ሲያስተጋቡ ቢውሉም  ንጉሠ ነገሥቱ ግን በየሚጎበኙት አገር ሁሉ የሚያውለበልቡት ሞአ አንበሳ የሌለበትን፣ በሕገ መንግሥታቸው የተደነገገውንና ከላይ ከመጀመሪያው አረንጓዴ፤ መካከለኛው ቢጫ፤ ከታች መጨረሻው ቀይ ሆኖ በአግድም የሚደረጉ ሦስት ቀለማት ያሉትን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ ነው። ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብና አርበኞች ያውለበልቡት የነበረው ይህን ንጉሡ በሕገ መንግሥታቸው ያሳወጁትን አረንጓዴ፣ ቡጫ፣ ቀይ ሰንደቅ አላማ ነው።
በደርግም ዘመን እንደዚያው ነው። በኢሕዲሪ ሕገ መንግሥት የታወጀው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ኮሎኔል  ደሳለኝ አበበ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በዚያድ ባሬ ወራሪ ጦር ላይ ድል ከተቀዳጀ በኋላ  ካራማራ ተራራ ላይ የካቲት 26  ቀን 1970 ዓ.ም. የሰቀለውን  አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ ነው።
የደርግ ወይም የኢሕዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 113  ስለ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሚከተለውን ደንግጓል፤
______________________
«የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሰንደቅ ዓላማ  ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሐሉ ቢጫና ከታች ቀይ ቀለም ያለው ባለ አግድም ቅርጽ ነው።»
______________________
ቀደም ሲል ከቀረበው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ሕገ መንግሥት የሰንደቅ አላማ አንቀጽና  ከፍ ብሎ ከቀረበው የደርግ ዘመን የሕገ መንግሥት የሰንደቅ ዓላማ  ድንጋጌ  መረዳት  የምንችለው ነገር ቢኖር በንጉሡ ዘመን  የነበረው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሞአ አንበሳ አርማ ያለበት ነበር፤ በደርግ ዘመን ደግሞ ሰንደቅ ዓላማው መሐል ላይ  የኢሕዲሪን አርማ  የነበረው ማረሻና ሞፈር በምልክትነት የተቀመጠበት ነው እየተባለ ሲወራ የምንሰማው የፈጠራ ታሪክ መሆኑንና  በሁለቱም  ዘመናት ሕገ መንግሥቶች ላይ ግን ሕጋዊ የነበረው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ  አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ  ቀለማት ያሉት ባለ አግድም ቅርጽ  የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ ብቻ መሆኑን ነው።
የወያኔ  ዘመን ሕገ መንግሥት አንቀጽ ሶስትም  ስለ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሚከተለውን ደንግጓል፤ 
______________________
አንቀጽ ፫
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ
1. የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሐል ቢጫ፣  ከታች ቀይ ሆኖ በመሐሉ ብሔራዊ ዓርማ ይኖረዋል። ሦስቱም ቀለማት አኩል ሆነው በአግድም ይቀመጣሉ።
2. ከሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ የኢ ትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች ፣ ሕዝቦች አና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንጸባርቅ ይሆናል ።
3. የፌዴራሉ አባሎች የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማና ዓርማ ሊኖራቸው ይችላል። ዝርዝሩን በየራሳቸው ምክር  ቤት ይወስናሉ።
______________________
ይህ የወያኔ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ሶስት ንዑስ አንቀጽ አንድ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሐል ቢጫ ከታች ቀይ ሆኖ ሦስቱም ቀለማት እኩል ሆነው በአግድም የተቀመጡ እንደሆነ ከደነገገ በኋላ በሰንደቅ ዓላማው ላይ ስለሚጨመረውና  ለጊዜው ግልጽ ስላልተደረገው አርማ ያትታል። የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ሶስት ንዑስ አንቀጽ ሁለት ደግሞ በሰንደቅ ዓላማው ላይ ስለሚቀመጠው ብሔራዊ አርማ ይዘት ያብራራል።  ይህ የሚያሳየው  ሰንደቅ ዓላማውና  በሰንደቅ ዓላማው መሐል ላይ የሚቀመጠው አርማው ሁለት የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን ነው። «የፌዴራሉ አባል ክልሎች የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማና አርማ ሊኖራቸው ይችላል» የሚለው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ሶስት ንዑስ አንቀጽ ሦስት ደግሞ  የበለጠ ግልጽ በማድረግ  ሰንደቅ ዓላማና አርማ ሁለት የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን ያሳያል።
በመሆኑም በወያኔ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ሶስት መሰረት እንኳን ብንሄድ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለማት ያሉት ሲሆን የአንቀጹ ሶስቱም ንዑስ አንቀጾች በተለይ ንዑስ አንቀጽ ሁለትና ሶስት  አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ ዓላማውና  ሰንደቅ ዓላማው መሐል ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ አርማው የተለያዩና ለየቅል ናቸው።
የወያኔ አገዛዝ ባለፉት አስርት ዓመታት አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩን  የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ  የሚያውለበልቡ የአርበኛ ልጆችን «የድሮው ሰንደቅ ዓላማ» አውለበለባችሁ እያለ ሲያስርና ሲያሳድድ የኖረው የጻፈውን ሕገ መንግሥት ምን እንደሚል  እንኳ ሳያውቅ  የራሱን ሕገ መንግሥት በመጣስ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን  ወያኔ ሰለ ሰንደቅ ዓላማ ባወጣው  አዋጅ «ብሔራዊ አርማ» የሌለበትን  አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩን  የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ  ያገደው  ራሱ የጻፈውን ሕገ መንግሥት ጥርስ በማርገፍ  ነው።
ወያኔ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መሐል ላይ ያስቀመጠውን የርዕዮተ ዓለሙን ምልክት የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች ፣ ሕዝቦች አና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ ለሚያንጸባርቅ  ነው ይላል። ሆኖም ግን  አያት ቅድመ አያቶቻችን በነገድ፣ በሃይማኖትና በጾታ ሳይወሰኑ በዱር በገደሉ የተዋደቁለት አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያሉትን  የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ይዘው ስለሆነ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያሉት  የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ  ዓላማ በነገድ፣ በሃይማኖትና በጾታ ሳይወሰን ኢትዮጵያውያንን ሁሉ የሚወክል   የኢትዮጵያውያን ሁሉ ሀብትና ብሔራዊ ምልክት ነው።
በማናቸው አገር ውስጥ ሰንደቅ ዓላማ  ከጥንት ጀምሮ የየሀገራቱ ሕዝብ ሀብትና ብሔራዊ ምልክት እንጂ የሥርዓት መግለጫ ምልክትና የርዕዮተ ዓለም አርማ ወይም የፖለቲካ ፕሮግራም ማራመጃ  አርማ  ሆኖ አያውቅም። ወያኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማን  የሚገባውን ክብር እንዳይጎናጸፍ ያደረገው የኢትዮጵያውያን አርበኞች  የጋራ ሀብትና ብሔራዊ ምልክት ሆኖ ከኖረው ሰንደቅ ዓላማ ይልቅ የርዕዮተ ዓለሙ ምልክት ያደረገውን አርማውን  የበለጠ አጉልቶ የርዕዮተ ዓለም ማራመጃ መሣሪያ  ለማድረግ ነው።  በርግጥ ወያኔ ቅድመ አያቶቻችን በነገድ፣ በሃይማኖትና በጾታ ሳይወሰኑ በዱር በገደሉ በተዋደቁለት የኢትዮጵያ ጀግኖች ሰንደቅ ዓላማ  ላይ የርዕዮተ ዓለም ምልክቱ  የሆነውን ኮከብ በመደረት  ሰንደቅ ዓላማን ለርዕየተ ዓለሙ [የፖለቲካ ፕሮግራሙ] ማራመጃ አድርጎ  መጠቀም  የጀመረው ሻዕብያን ተከትሎ አዲስ አበባ እንደገባ በሊቀመንበሩ በፊት በኩል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ «ጠባችን ከጨርቁ ሳይሆን ከበስተጀርባው ባለው ድርጊት ነው፡» ብሎ ገና ከማወጁ ዓመታት በፊት   በሰንደቅ ዓላማው ላይ የፖለቲካ ፍልስፍናውን በአርማነት አስቀምጦ የርዕዮተ ዓለም ማራመጃ በማድረግ ከፈጸመው ማዋረድ የከፋ አሳፋሪ ድርጊት  ሲፈጽምበት  በነበረበት የጫካ ዘመኑ ጭምር ነው።
የሆነው ሆኖ  በወያኔ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ሶስት መሰረት እንኳ ብንሄድ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሐል ቢጫ ከታች ቀይ ሆኖ ሦስቱም ቀለማት እኩል ሆነው በአግድም የተቀመጡበት ብቻ ነው። የወያኔ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ሶስት የሚያወራው ስለ ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ አርማ ነው። ወያኔ በፊት ከነበሩት የደርግም ሆነ  የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ሕገ መንግሥቶች የተለየ ነገር የተደነገገው ነገር ቢኖር ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሐል ቢጫ ከታች ቀይ ሆኖ ሦስቱም ቀለማት እኩል ሆነው በአግድም የተቀመጡ ቀለሞች ባሉት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ አርማ መጨመሩ ነው። ይህም ሆኖ  አርማው  በሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጥ ብሔራዊ ምልክት እንጂ የሰንደቅ አላማው አካል እንዳልሆነ የሕገ መንግሥት ተብዮው አንቀጽ ሶስት በተለይም ንዑስ አንቀጽ ሁለትና ሶስት በግልጽ ያሳያሉ።
ስለዚህ የዛሬዎቹ ባለጊዜዎችም አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩን  የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ አውለበለብህ ብለው ሊያስሩህ ወይም ሲቀሙህ ሲመጡ ካላከበርነውና ካላስከበርነው ሞተን እንገኛለን የምትሉትን ሕገ መንግሥት አክብሩ በላቸው። ካላከበርነው ሞተን እንገኛለን የሚሉት ሕገ መንግሥት  አንቀጽ 106 «የሕገ መንግሥቱ  የአማርኛ ቅጂ የመጨረሻው ሕጋዊ እውቅና ያለው ሰነድ ነው» በሚል የደነገገውን  ጠቅሰህ  በአማርኛ ቋንቋ አርማና ሰንደቅ አላማ የተለያዩ መሆናቸው በማሳት በሕገ መንግሥታችሁ አንቀጽ ሶስት ሕጋዊ የተደረገው ሰንደቅ ዓላማ  አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለማት ያሉት ሰንደቅ ዓላማ መሆኑን፤ ሰንደቅ ዓላማውን እንጂ  የርዕዮተ ዓለም አርማቸውን የመሸከም ግዴታ እንደሌለብህ በማሳወቅ  ሕገ መንግሥት ተብዮውን  ሌላውን አክብሩ ከማለታቸው በፊት ራሳቸው  በቅድሚያ  ያከብሩት ዘንድ አስተምራቸው።
Filed in: Amharic