>

አረንጓዴ ቢጫ ሰንደቅ ዓላማ፤ የ600 ዓመት የታሪክ ማስረጃዎች!!! 

አረንጓዴ ቢጫ ሰንደቅ ዓላማ፤ የ600 ዓመት የታሪክ ማስረጃዎች!!! 
ኤፍሬም
ከዛሬ 400 ዓመት ፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና የኢትዮጵያውያን መለያ ( national banner)  አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ነበረች፡፡ በዚያን ዘመን ዓለም ያውቀው የነበረው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማም ይሄንን ነበር፡፡ ማስረጃ ላቅርብ
በ16ኛው ክፍለዘመን የተወለደው ፣ ሆላንዳዊው ፒተር ቫንደር አ ( Pieter Vander)  ፣ በዓለም ከታወቁ የካርታ ሥራ ባለሙያዎችና ጆግራፈሮች አንዱ ነበር፡፡ ይሄው ሰው 28 ቮልዩምና ከሶስት ሺህ በላይ ገጽ ያለውን የዓለም ካርታና አትላሶች አዘጋጅቷል፡፡ ይሄው ካርቶግራፈር ታድያ የያንዳንዱን ሀገር ካርታ ከሳለ በኋላ፣ የዛን ግዜ በነበረው አካዳሚካዊ ደንብ፣ ከካርታው ሥሩ የሀገሩን ሰዎች ማንነት ፣ ቀለምና የሚወክላቸው የሰንደቅ ዓላማ ቀለም ያስቀምጥ ነበር፡፡
ይሄ ምሁር የሳለውና ያሳትመው የኢትዪጵያ ካርታ ላይ ፣ ኢትዮጵያውያዊ እናትና አባትን አረንጓዴ ፣ ቢጫ ፣ ቀይ ልብ አልብሶ ስሏቸዋል፡፡ ከደራሲው ኦርጅናል ሥራ ላይ የተወሰደው ኮፒ ካርታና ስዕል  እዚህ ላይ ይገኛሉ፡፡
ይህ ሰው ዜግነቱ ደች( ሆላንዳዊ) ነው፡፡ስራውም የካርታ ሥራ ባለሙያና ጆግራፈር ነው፡፡ በደች ዩንቨርስቲዎች ውስጥ ሳይቀረ የካርታ ሥራን ያትም የነበረ ትልቅ ባለሙያ ነበር፡፡ በግዜውም ተወዳዳሪ ያልነበረው የካርታና የሀገራት ማንነት ሊቅ ነበር፡፡
ይህ ሊቅ  ሀገራችንን ካርታው ላይ ሲጠቅሳት ስያሜዋን ያላት “ አቢሲንያ “ አይደለም፡፡ኢትዮጵያ ነው ብሎ የጠራት፡፡ ኢትዮጵያውያንንም ( መልካቸውን ጥቁር) ልብሳቸውን ግን አረንጓዴ፣ ቢጫ ፣ ቀይ አልብሶ ነው የሳለቸው፡፡
የመጽሃፍቶቹን ጥቁና ነጭ ኮፒ እዚህ ሊክ ላይ ያገኙታል
አሜሪካዊው ዋልት ዊትማን (1871)
************
እንግሊዞች ሼክስፒርን በባለቅኔነት እንደሚጠሩት ሁሉ፣ አሜሪካኖች አሉን ከሚሏቸው አንዱ ባለቅኔና ጸሐፊ በ1819 ዓ.ም የተወለደው ዋልት ዊትማን ነው፡፡
ዋልት ዊትማን እጅግ በርካታ ቅኔዎችንና ሌሎች መጻሕፍትን የጻፈ አሜሪካዊ ባለቅኔ ና ደርሲ ነው ፡፡ ከዛ ውስጥ አንዱ በ በ1860ዎቹ ተጽፎእ በ1871 የታተመው Ethiopia Saluting the Colors የሚለው ቅኔ ነው፡፡ ይህ ወቅት እንግሊዞች አጼ ቴዎድሮስን( 1855-1868) እየተተናኮሉ የነበረበት ወቅት ነበር፡፡ ለአሜሪካኖች ደግሞ ፣ እንግሊዝ ላይ የበላይነታቸውን እያሳዩ የነበረበት ውቅት ነበር፡፡ የተለያዩ የዓለም ሀገራትንም ፣ ከንግሊዝ ወጥተው ከአዲሷ ገናና ሀገር አሜሪካ ጋር እንዲወዳጁ ይሰብኩ ነበር፡፡ የቅኔ ደምቡ ሆኖ ይህ ቅኔም ሰምና ወርቅ ፣ ብዙ እማሬና ፍካሬ ቢኖረውም ፣ አንዱ ውትወታ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ትብብር ትፍጠር አይነት ነበር፡፡ ታድያ ዋልት በዚህ በ 1871 በታተመው Ethiopia Saluting the Colors የተሰኘው ቅኔው ላይ እንዲህ ይላል ( ዊትማን በ187አ ያሳተመውን መጽሃፍ ኮፒ እዚህ ላይ ያገኙታል
“What is it, fateful woman–so blear, hardly human?
Why wag your head, with turban bound–yellow, red and green?
Are the things so strange and marvelous, you see or have seen?”
ዋልት በግጥሙ ኢትዮጵያን በአንዲት ወይዘሮ ነው የገለጣት፣ ራስዋ ላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሪባን ሻሽ ያስረች ጥቁር ቆንጆ ሴት ብሎ ይገልጻታል፡፡ ዋልት አሜሪካዊ ነው፡፡ ይህንንም ግጥም የጻፈው በአጼ ቴዎድሮስ ዘመን ነበር ( ያሳተመው በአጼ ዮሃንስ ዘመን ቢሆንም) ፡፡ በአጼ ቴዎድሮስም ዘመን ፣ በአጼ ዮሃንስም ዘመን ፣ ኢትዮጵያ የምትታወቀው በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለሟ ነበር፡፡ ይህችን ሰንደቅ መልበስ ፣ ራስ ላይ ማሰር የተጀመረውም አሁን ያለመሆኑንና ያኔም ኢትዮጵያ ስሟ በዓለም ዘንድ ኢትዮጵያ እንደነበር ያጤኗል፡፡መቀሌ በሚገኘው የአጼ ዮሃንስ ቤተ መንግስትም የሚታየው የአጼ ዮሃንስ ሰንደቅ ዓላማ ይሄው አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩ ነው፡፡
የትግራዩ ራስ ወልደሥላሴና አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማቸው ( 1736_1816)
*****************************************
በኢትዮጵያ ታሪክ ከሚጠቀሱት ጠንካራ መሳፍንት ውስጥ ፣ የትግራዩ ራስ ወልደሥላሴ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ትግራይን 25 ዓመት በገዙት ጠንካራው መስፍን ራስ ወልደሥላሴ ዘመን ፣ በርካታ የውጭ ዲፕሎማቶች ትግራይ ድረስ ሂደው በወቅቱ ስለነበረው የትግራይ ሕዝብ ባህልና ኑሮ ጽፈዋል፡፡ ከነሱ ውስጥ አንዱ በሳቸው ዘመን የትግራይ ሕዝብና የራስ ወልደሥላሴ ወታደሮች ራሳቸው ላይ አረንጓዴ ፣ ቢጫ ፣ ቀይ [ጥለት ሻሽ] ያስሩ እንደነበር እንዲህ ሲል ይገልጠዋል   Voyages and travels to India Ceylon, the Red Sea and Abyssinia and Egypt  By  George, Viscount Valencia  pp 132
“ Round their heads, they wore bandages formed of Yellow , green red satin tied behind long and streaming loosely as they rode”
ከላይ እንዳየናቸው ፣ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ሆላንዳዊ የካርታና የጂኦግራፊ ሊቅ ኢትዮጵያውያን መለያቸው አረንጓዴ፣ ቢጫ ፣ ቀይ እንደሆነ ካርታው ላይ ስሎ ነግሮናል፡፡ አሜሪካዊው ባለቅኔ ዋልት ዊትማንም ኢትዮጵያን በሴት ወይዘሮ መስሎ ሲገልጣት ራስዋ ላይ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ያስረች ወይዘሮ አድርጎ ገልጿታል፡፡ ትግራይን በራስ ወልደ ሥላሲ ግዜ የጎበኘው  ቪስካውንት ጆርጅ ደግሞ የትራዩ መስፍን የራስ ወልደ ሥላሴ ወታደሮች ራሳቸው ላይ አረንጓዴ ፣ ቢጫ ና ቀይ ሪባን ያስሩ እንደነበር ግልጽ አድርጎ ይነገረናል፡፡
መጽሃፉን እዚህ ያገኙታል
አጼ ሚኒሊክ ( 19ኛው ክፍለ ዘመን) 
********************
በዘመነ አጼ ሚኒሊክም የተለየ ነገር አልነበረም፡፡ አረንጉዴ፣ ቢጫ ፣ ቀይ የሀገሪቱ አርማ ( national Banner)  ነበረ፡፡ ይሄንንም ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ ፣ ታሪክ ዘመን ዘዳግማዊ አጼ ምኒልክ በሚለው መጽሃፋቸው ብዙ ቦታ ላይ ገልጸውታል፡፡ ለምሳሌ በ1882 ዓ.ም ሥርዓተ መንግስት ሲያደርጉ የነበረውን ሁነት ጸሐፌ ት ዕዛዝ ከላይ በተጠቀሰው መጽሃፋቸው ገጽ 157 ላይ እንዲህ ሲሉ ይገልጹታል
“በዙፋኑም በኋላ፣ ወደ ትልቁ ሰገነት የሚያስወጣ ባለሟሎችና መኳንንቶች የሚመላለሱበት ያ ዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ያየውን የመሰለ መሰላል ነበረ፡፡ መሰላሉም በአረንጓዴ ፣ ቢጫ ፣ ቀይ የተሸለመ ነው” ሲሉ ይገልጡታል፡፡
የአድዋ ጦርነት ሲደረግም ፣ የአክሱም ካህናት ይዘው ወደ አጼ ሚኒሊክ የመጡት ስዕለ ማርያምንና የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማን ነበር፡፡( ገጽ 262) ፡፡ ዳግማዊ አጼ ምኒሊክም ከጣልያኖች ጋር የነበራቸው ጥያቄ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ነበር፡፡ ለምሳሌ ማጆር ሳልሳን እንዲህ ነበር ያሉት
“ አጼ ምኒሊክም ሲመልሱ ፣ እኔም የመጣሁት የተተከለውን ባንዲራ ላስነሳ ነው፡፡ … ባገሬ በኢትዮጵያ መንግስት ባንዲራ እንጂ የሮማን ባንዲራ አላስተክልበትም ብለው መለሱለት” ገጽ 253
ይህንን ለግዜው እዚህ ላይ ገትተን እጅግ ወደኋላ ወደ 14ኛው ክፍለ ዘመን ስንጓዝ ደግሞ ፣ በዚያ ዘመንም የኢትዮጵያ መለያ ቀለም አረንጉዴ ቢጫ ቀይ መሆኑን በማስረጃ እንመለከታለን፡፡ ለምሳሌ በአስራ አራተኛው ክፍለዘመን የተጻፈውንና መጽሃፍ ስንመለከት ልክ አቡን እንደምናደርገው ያኔም በመጽሃፍት ዙርያ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለምን መሳል የተለመደ እንደነበረና በማስረጃ እናያለን፡፡
https://www.metmuseum.org/en/art/collection/search/317618 ( ከስምንተኛው ገጽ ጀምሮ ይመልከቱ)
እንግዲህ ከላይ በማስረጃ እንዳየናቸው፣ ከ14ኛው ክፍለዘመን የብራና መጽሃፍ ጀምሮ፣ የተለያዩ የውጭ ሊቃውንት የመሰከሩት ነገር ተመሳሳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ነው፡፡ ቢያንስ ለዚህ የስድስት መቶ አመት ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ትውፊታችን እንደሚለን ደግሞ ይህ ሰንደቅ ዓላማ ከኖህ ዘመን ጀምሮ እኛ ኢትዮጵያውያን ስንጠቀምበት የነበረው መለያችን ነው፡፡
ጣልያን ኢትዮጵያን ሁለተኛ ከመውረሩ በፊት፣ የጣልያን ወታደራዊ ሊቃውንት  ስለ ኢትዮጵያ ብዙ ጥናት አስጠንተው ነበር፡፡ በተለይም የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድ አድርገው የያዙት ነገሮች ማለትም ሃይማኖት ( ኦርቶዶክስ)፣ ሰንደቅ ዓላማ እና ዘውድ አስተዳደሩን ካላፈረሰ ኢትዮጵያን መያዝ ከባድ እንደሚሆን ና እነዚህ ነገሮች ከወደሙ ግን ኢትዮጵያን መቆጣጠር ቀላል እንደሆነ የጣልያን ሊቃውንት ባሳሰቡት መሰረት እነዚህ ሶስቱ የኢትዮጵያ እሴቶች ላይ የኮሎኖያሊስት ዘመቻ ተጀመረ፡፡ በዋነኛነትም ሚሲዮናውያን( በሃይማኖት ስብከት ሽፋን የገቡ ሰላዮች) የኦርቶዶክስን ሃይማኖት ፣ ሰንደቅ ዓላማን እና  አማራን ጥላሸት እየቀቡ በማስተማርና መጻሕፍትን በመጻፍ የህዝቡን ስነ ልቦና ማሸፈት ጀመሩ፡፡ ቀስ በቀስም ሙያ እናስተምራለን በሚል ሰበብ በከፈቷቸው ትምህርት ቤቶች ፣ አዳጊ ሕጻናትን ጸረ ሰንደቅ ዓላማ ሆነው እንዲወጡ ያስተማሯቸው ኢትዮጵያኖች የገዛ ሰንደቅ ዓላማቸውን ማዋረድ ጀመሩ፡፡ አልፎ ተርፎም እነዚሁ ወገኖች ስልጣን ሲይዙ የገዛ ሰንደቅ ዓላማቸውን “ ህጋዊ ያልሆነ “ እስከማለት ተደረሰ፡፡
( ይቀጥላል)
Filed in: Amharic