>

አርምሞ እና የጩኸት ግርግር (ከይኄይስ እውነቱ)

 

አርምሞ እና የጩኸት ግርግር

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

ኢትዮጵያ አገራችን በአራቱም ማዕዝናት እየተናጠች ትገኛለች፡፡ ንጠቱ ቅቤ መረጋጋትን÷ ቅቤ ሰላምን÷ ቅቤ አንድነትን ወዘተ ሳይሆን ‹ወተቱን› አጥቁሮና አምርሮ ኹከት÷ መለያየት÷ ኀዘን÷ ልቅሶ÷ ሰቈቃን ወዘተ የሚያወጣ ይመስላል፡፡ ባለቤቱ ከዚህ መአት ይሠውረን፡፡ በዕብደትና ድንቁርና ግቢ ነፍስ ውጪ ነፍስ ማለት ከጀመርን (የቅርቡን ብንወስድ) እነሆ የአንድ ጎልማሳ (30) ዘመን ተቈጥሯል፡፡ አየሩ ሁሉ በኹከት ተበክሏል፡፡ መላወሻ ጠፍቷል፡፡ ይህ የክፋት ዘመን ክፉዎችን በሚያስደነግጥ ቊጥር እየደመረ ማብቂያ ያጣ ይመስላል፡፡ የብዙዎች አርምሞም ሆነ የጥቂቶች አደንቋሪ ጩኸትና ግርግር ወደማይፈለግ ጥግ እየወሰደን ይመስላል፡፡ ቀደምት አበው እንደሚያስተምሩን አርምሞ የአፍ ዝምታ እንጂ የልብ አይደለም፡፡ የልብ ዝምታ ትዕግሥት ነው፡፡ ስለሆነም ያረመመው ሁሉ ውስጡ ሊሸሸው በማይችለው አንደንቋሪ ጩኸት የተሞላ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ሁላችን – መሪና ተመሪ ባንድነት – ተካክለን ታመናል፡፡ 

የዐቢይ አገዛዝ ባንድ በኩል የመናገርና የመጻፍ ነፃነትን አስከብሬአለሁ እያለ ከሱና በሱ ዙሪያ የተሰባሰቡ ዘረኛ ቡድኖች  በሃሳብ የተለዩትን በእስር አፍ ሲያዘጋ ይስተዋላል፡፡ በሌላ ወገን በመንግሥትና አገዛዙ በተቆጣጠራቸው ‹የግል› ብዙኃን መገናኛዎች፣በግል እና ማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛዎች የሚታመን ወሬና መረጃ ጠፍቶ ሕዝቡ በውዥንብርና ድንግርግር ውስጥ ይገኛል፡፡ እውነተኛ መረጃን በመዘገብ ረገድ ዛሬ በመደበኛውና በማኅበራዊው ሚዲያ መካከል እምብዛም ልዩነት የለም፡፡ ሙያውና የሙያው ሥነምግባር ባለመኖሩም ረገድ እንደዚሁ ተመሳሳይነት ጎልቶ ይታያል፡፡ ወገንተኝነቱና የተወሰኑ ቡድኖች ጥቅምና ዓላማ ማራመጃ መሣሪያና መታገያ መሆናቸውም የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ጊዜው ሐሰትና ነውር የክብር አክሊል የተቀዳጁበት ሆኗል፡፡ ለዚህም ይመስላል ምክራቸው÷ አሳባቸውና አስተያየታቸው ለአገር ለወገን እንደሚጠቅም የሚታመንባቸው ጥቂት የማይባሉ ባገር ውስጥም ይሁን በውጭው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውን ማዕምራን ሁኔታዎችን በዝምታ ለመታዘብ የመረጡት፡፡ ከነዚህም መካከል ጥቂቶች ጊዜውን ለመምሰል የፈቀዱ እንዳሉ አይካድም፡፡ አንዳንዶችም አቧራው ሰከን ይበል በሚል የሚታዘቡም እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እንደኔ እምነት ግን ምንቸቶች ጋን እንዲሆኑ መፍቀድ ብዙ ስለሚያስከፍለን ዝምታው ቢሰበርና ሰብሰብ በማለት ለዐቢይ አገዛዝ ጠንካራ ምክርና ተግሣፅ ማስተላለፍ መልካም ይመስለኛል፡፡ ዝምታ ወርቅ የሚሆንበት ጊዜ እንዳለ ሁሉ፣ ካለመናገርም ደጅ አዝማችነት እንደሚቀር ማሰቡ አይከፋም፡፡

ባንፃሩም አገዛዙና በዙሪያው የተኰለኰሉት መንደርተኞች ባንድ ወገን፣ ራሳቸውን አክቲቪስት ነን የሚሉ ግለሰቦች በሌላ ወገን አገርን እያመሱ ይገኛሉ፡፡ መጨረሻው ጥላቻና መለያየት በሆነ የማይረባና የማይገባ አተካራ/የቃላት ጦርነት እሰጥ አገባ ተጠምደው ነው የሚገኙት፡፡ መብቴ ነው ነፃነቴ ነው በሚል ስድ መሆን ተገቢ አይመስለኝም፡፡ የተፈቀደ ሁሉ አይጠቅምምና፡፡ የምንናገረውም ሆነ የምንጽፈው (እውነትም ቢሆን እንኳ) ጊዜን ካልዋጀ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ጊዜው ተመቸኝ፣ መድረክ አገኘሁ ብሎ ባልታረመ አንደበት መዘባረቅ ለራስም÷ ለቤተሰብም÷ለወገንና ላገር አሳፋሪ ታሪክ ትቶ ማለፍ ይሆናል፡፡ ዛሬ በዕብደት መንፈስ ብናደርገውም ነገ ወደ አእምሮአችን ስንመለስ ወይም ከተጣላነው ኅሊና ስንታረቅ እጅጉን ያስተዛዝባል፡፡ 

ሌላው ባገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ ያለው ጉዳይ ሳይገባው የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ እወስናለሁ ብሎ በጉልበት የተጫነብን የወያኔ አገዛዝ (4ቱም መንደርተኛ ድርጅቶች) የመግለጫና አፀፋ መግለጫ ጋጋታ ነው፡፡ ይሄ ድኩማን ድርጅት ሕዝባችንን እና አገራችንን ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁናቴ ወደ ዐዘቅት እየከተታት ነው፡፡ ከአፈጣጠራቸው ሁለንተናዊ ስንኩላን የሆኑት ድርጅቶች የተጣባቸው ነቀርሳ በሞት ካልገላገላቸው በስተቀር አገራችን እፎይታ አታገኝም፡፡ የውስጥ ሽኩቻው በፈለገው መንገድ ቢገለጽም በእኔ አመለካከት በኦሕዴድና በሕወሓት መካከል ያለው ልዩነት የተረኝነት ብቻ ነው፡፡ ለሦስት ዐሥርት የዘለቀውን እንደ አገርና ሕዝብ ያሽመደመደንን አገዛዝ እስከ መርዘኛ ‹ሰነዱ› ለማስቀጠል በመፈለግ ረገድ አሁንም ልዩነት የላቸውም፡፡ ዛሬ አገራችንን እገዛለሁ በሚለው ኦሕዴድና ኢሕአዴግ በሚሉት ግንባር መካከል ልዩነት የለም፡፡ ሕወሓት ለሽብር ባያንስም ህልውናው እያከተመ ነው፡፡ ብአዴንና ደሕዴን እንዲሁም አጋር ተብዬዎቹ በውድም ሆነ በግድ ለባለተረኛው ኦሕዴድ አድረዋል፡፡ ችግሮችን የበለጠ ለማክፋት በነዐቢይ ከለላ ‹‹በኅቡዕ መንግሥትነት›› (deep state) አገዛዙን የሚያሾሩት ኦነጋውያንና ጀዋራውያን አሉ፡፡ በዛሬዩቱ ኢትዮጵያ ለጊዜውም ቢሆን በተግባር የዚህ ኅቡዕ አካል ፈቃድ እየተፈጸመ ይገኛል፡፡ የዐቢይ አገዛዝ የሚወስዳቸው ማናቸውም ርምጃዎች የዚህ አሸባሪን ቡድን ቡራኬ ሳያገኝ እንደማይፈጸም ይታመናል፡፡ በተግባር እንደሚታየው ለማና ዐቢይ በፍላጎትም ይሁን በአቅም እጦት (ቃልና ተግባራቸው ስንኝት የሌለው በመሆኑ፣ በዚህ ረገድ ያልተነገረን ከሕዝብ የተሠወረ ምሥጢር ካለም በአገር ህልውና ደረጃ እያስከፈለን በመሆኑ፣ በውጤቱም ስም ያላቸውንና ለአገር ይጠቅማሉ የሚባሉ ግለሰቦችን አፍዞና አደንግዞ ከጥቅም ውጭ በማድረጉ) ኢትዮጵያን ባግባቡ ለመምራት የማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል፡፡ ወያኔ ክልል ብሎ የፈጠራቸው ክፍላተ ሀገራት የአገርን አንድነትና ሰላም በማይፈልጉ የመንደር ጉልበተኞች እጅ ወድቀዋል፡፡ ማዕከላዊው መንግሥት ሕግና ሥርዓት ማስከበር ተስኖት በአዲስ አበባ እንኳን ተሽመድምዶ ነው የሚገኘው፡፡ የቀረውንም ጉልበት እስክንድርና ባልደረቦቹ እንዲሁም ተመስገን ላይ ነው ሲፈትሽ የሚታየው፡፡ ዐበይት አገራዊ አጀንዳዎችን ለሕዝብ ግልጽ ከማድረግ እና በብሔራዊ ጣቢያ ከማስተላለፍ ይልቅ በጓዳ ጀምሮ ኢመደበኛ በሆነ መልኩ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እንዲወሩ በማድረግ ሕዝብን ሲያደናግር ይስተዋላል፡፡ በዚህ ሁሉ ወጀብ መካከል መጽሐፍ ለማዘጋጀት ጊዜውን ያገኘ ጠ/ሚር (ትልቅ ጥንካሬና ብርታት አድርጌ ነው የማየው) የሕዝብንና የታላላቆቹን ምክር ሰምቶ እንዴት የአብዛኛው ሕዝብ ፍላጎት ከሆነው ሥርዓታዊ ለውጥ ርእሰ ጉዳዮች መካከል ባይፈጽም እንኳን ለመጀመር ጊዜ አጣ? ይህም ባይሆን የሚመራውን ድርጅት ለውጦ ቢያንስ በትክክለኛው ሐዲድ ላይ ለመሆናችን ዋስትና ለመስጠት ለምን ተሳነው? ይሄን ከነአስተሳሰቡ የነቀዘ የወያኔ ድርጅት የአገራችን ህልውና አደጋ ላይ እስኪወድቅ ለማስታመም ለምን ፈለገ? አሁንም ፍቅር÷ ይቅርታ÷ ዕርቅ÷ ትዕግሥት ወዘተ እንደማይለን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እውነት ቢሆን እንኳ በየትኛውም አገርና መንግሥት ታሪክ ሕዝብና አገርን ያለ ሕግና ማስፈጸሚያው ሰይፍ ማስተዳደር አይቻልም፡፡ የመከላከያና የፀጥታ ኃይል፣ ፖሊስና ሕገ ወጥ ‹ልዩ ኃይል› የአገርና የሕዝብ ሳይሆኑ፣ እንዲሁም የአገዛዙ ደባል በሆኑ አሸባሪዎች የሚመሩ የመንደር ወሮበሎች ላንድ በዘር ለተደራጀ ቡድን (ቀድሞ ለሕወሓት አሁን ዐቢይ ለሚመራው ተረኛው ኦሕዴድ) ዓላማ ቆመው በአራቱም የአገራችን ማዕዝናት ሕዝብ እንደ ቅጠል ሲረግፍ፣ ሲሰደድ፣ ከቀየው ሲፈናቀል፣ ነፃነትና ንብረቱን ሲያጣ፣ አልፎ ተርፎም የውጭ አሸባሪ ኃይሎቸ ድንበር ጥሰው ዜጎቻችንን ሲገድሉና ሲያቆስሉ የመንግሥት አለመኖር ምልክት እንጂ ከፍቅርና ትዕግሥት ጋር ማያያዝ የለየለት ዕብደት ነው፡፡ በዚህ ትርምስ ውስጥ ስለ ምርጫ ማሰብም (ተግባራዊ የሚሆን አይመስለኝም) ሌላው የዕብደት መገለጫ ነው፡፡ 

በመጨረሻም ይህ አልገታ ያለ የጥፋት መንገድ የሚያሳስባችሁ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ጎራ ያላችሁ ከየትኛውም ነገድ/ጐሣ ቆጠራ ወጥተን አንድ በሚያደርገን ኢትዮጵያዊ ዜግነት ላይ አተኩረን ችግሮቻችንና ተግዳሮቶቻችንን እንጋፈጥ፡፡ እንደ አንድ ሕዝብ ዕጣ ፈንታችን ዕድል ተርታችን÷ ልማታችንም ሆነ ጥፋታችን በጋራ የተሳሰረ መሆኑን እንረዳ፡፡ በመሆኑም ዋኖቻችን ዝምታችሁን ስበሩ፤ በማይጠቅም አተካሮ የተጠመዳችሁትም (ማንም በሚወረውረው ጭፍጫፊ አጀንዳ ላይ የምታደርጉትን ብስለት የጎደለው የእልህና ብሽሽቅ እንኪያ ስላንቲያ በማቆም) ግርግሩንና ውዥንብሩን ገታ አድርጋችሁልን፣ መላ ኃይላችሁን ባገራችን መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ አገዛዙ ላይ በተደራጅ መልኩ ጫና ለማሳደር ብትጠቀሙበት መልካም ይመስለኛል፡፡ አገዛዙም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በያዛቸው ብዙኃን መገናኛዎች መንግሥታዊ ውሸቶችንና የፈጠራ መረጃዎችን ለሕዝብ ከማሠራጨት ካልታቀበ ውሎ አድሮ እውነት ቢናገርም አድማጭ እንደሚያጣ ማወቅ ይኖርበታል፡፡ ከወያኔ ትግሬ ዘመን ጀምሮ አሁንም ‹በአዲሶቹ/ተረኞች ወያኔዎች› በድንቁርናም፣ በአድርባይነትም፣ በሆዳምነትም፣ በዘረኝነትም የጋዜጠኝነትን ሙያ የምታራክሱ ሁሉ ኢትዮጵያ ወደ እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዳትሸጋገር ታላቅ እንቅፋትና የሕዝብ ጠላቶች መሆናችሁን ዐውቃችሁ አሁንም አልረፈደምና ራሳችሁን ብትመረምሩና ብታርሙ መልካም ነው፡፡

 

Filed in: Amharic