>
11:50 pm - Wednesday November 30, 2022

መደመር በየአዳራሹ ስትምነሸነሽ፤ መቀናነስ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ዱላ ስታማዝዝ ዋለች!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

መደመር በየአዳራሹ ስትምነሸነሽ፤ መቀናነስ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ዱላ ስታማዝዝ ዋለች!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
 
ዛሬ በአዲስ አበባ ሁለት ትላልቅ ስብሰባዎች በመንደር ጎረምሶች ተደናቅፈዋል። ንብረትም ላይ ጉዳት ደርሷል። ወጣቶችም በግራ ቀኝ ተሰልፈው ለዱላ ተገባብዘዋል። በማህበረሰባችን ውስጥ የመደመርን ጽንሰ ሃሳብን ማስረጹ ተገቢም፤ አስፈላጊም ነው። ግን የአንድ ጀንበር ሳይሆን ጊዜ የሚወስድ ሰፊ ሥራ ነው። ሕግ የማስከበሩ ሥራ ግን ጊዜ የሚሰጠው አይደለም። ይች ባቄላ ካደረች ከርማለች፤ መቆርጠሟን እንጃ።
 
መጽሐፍ ምረቃ እና ስልጣን! ሁሉ በጅሽ ሁሉ በደጅሽ!!
ዛሬ የዶ/ር አብይ አህመድ “መደመር” የተሰኘው መጽሃፋቸው እጅግ ከፍተኛ ዝግጅትና ከፍተኛ ወጪ ተደርጎበት መመረቁን የመንግስቱ አፍ ከሆነው ኢትቪ መሰኮት ሙሉውን ተከታትያለሁ። በእውነት ለመናገር በመንግስት ደረጃ የተደረገው እና ከፍተኛ ወጪ እንደተደረገበት የሚገመተው ይህ የምረቃ ዝግጅት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ግዜ ኖቤል ሽልማት ብቻ ሳይሆን ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሐፍ ያሳተመችም ጭምር ነው የሚመስለው።
መጽሐፉን ገና እጄ ስላልገባ እና ስላላነበብኩት ከመጽሐፉ ይዘት ጋር በተያያዘ ምንም አይነት አስተያየት ከመስጠት እቆጠባለሁ። ግሩም መጽሐፍ ሊሆን እንደሚችል ግን ከወዲሁ ለመገመት ይቻላል። ለጌዜው ቀልቤን የሳበው ግን የመጽሐፉ ምረቃ ግርግር፣ ሆይ ሆይታና የአፋሽ አጎንባሹ ያዙኝ ልቀቁኝ ነው።
በመጽሐፉ ምረቃ ላይ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ንግግር የግል መጽሐፋቸውን የሚያስተዋውቁ ሳይሆን የአዲሱ በወህደት የሚመሰረተውን እና ኢህአዴግን የሚተካው ፓርቲ ማኒፌስቶ ማስተዋወቂያ ነው የሚመስለው። እንደዛ ከሆነ ነገርየው ይህ ሁሉ ሽር ጉድ እና እርብርብ ከመጽሐፍ ምረቃ ያለፈ እና ምርጫ ተኮር የሆነ ፋይዳ ያለው እንቅስቃሴ ነው የሚሆነው። የአብይ ንግግርን በጥሞና ላደመጠ ሰው መልክታቸው የቅድመ ምርጫ ቅስቀሳ ይዘት ያለው እና የአገሪቱ መጻዒ እድል በመደመር ጽንሰ ሃሳብ ብቻ ከአብይና ከአዲሱ ፓርቲያቸው ጋር ወደፊት የሚል ነው። እስቲ እነዚህን ቀላል ጥያቄዎች ላንሳ፤
የኢቲቪ እና ሌሎች የመንግስት ሚዲያዎች በማን ወጪ ነው በቀጥታ ስርጭት ይህን የመጽሐፍ ምረቃ ለሰዓታት ሲያስተላልፉ የዋሉት?
ከአዳራሽ ወጪ አንስቶ ለጠቅላላ ዝግጅቱ የተደረገውስ ወጪ በማን ነው የተሸፈነው? ከዶ/ር አብይ ኪስ? ከፓርቲያቸው ካዝና? ወይስ ከዚችው ከፈረደባ ድሃ አገር?
መጽሐፉን ለማስተዋወቅ የተሄደበት እርቀት እና የተደረጉት ዲስኩሮች ሕዝቡ ገዝቶ እንዲያነበው እና ሃሳቡን እንዲሞግት ብቻ ሳይሆን እንደ ቅዱስ መጽሐፍም እንዲቆጥረውም ከአፋሽ አጎንባሹ አንስቶ ደራሲውም በንግግሮቻቸው መካከል የተጠቀሙዋቸው አንዳንድ አገላለጾች በደንብ ያሳያሉ።
ህውሃት አቢዮታዊ ዲሞክራሲን የኢትዮጵያን ሕዝብ አፍንጫውን ሰንጋ ልትግተው ያልቧጠጠችው ሰማይ፣ ያለውጣችው ዳገት እና ያልወረደችው ቁልቁለት የለም። ነገሩ ሁሉ የእሟይ ካብ ሆነና ተናደ እንጂ። ዛሬ ደግሞ የአብይ አስተዳደር የመደመርን ጽንሰ ሃሳብ በድግስ፣ በስብከት እና ስልታዊ በሆነ የመንፈስ ተጽዕኖ ለማሳደሪያ እየሞከረ ይመስላል። ለነገሩ ሃሳቡ ቀና እና የሚደገፍ ስለሆነ ክፋት የለውም። ግን ተወዳዳሪ ሃሳቦች በእኩል ደረጃ እንዲፈተኑ ግን እድል የሚፈጥር አይደለም።
እንዳልኩት መጽሐፉን አላነበብኩትም። በመጽሐፉ ላይ ትሽተ ሃሳብ ላቀርብ አልችልም።    በመደመር ደረጃ ግን ከራሳቸው ከዶ/ር አብይ ቀድሜ ከአመታቶች በፊት መደመሬን ግን ጠንቅቄ አውቃለሁ። ብዙዎቻችንን ላለፉት ሃያ አመታት ከህውሃት መራሹ ኢህአዴግ ጋር አይጥና ድመት አድርጎ አሳዳጅ እና ተሳዳጅ ያደረገን መሰረታዊው ነገር በመደመር እሳቤ ዙሪያ በተነሱት አንኳር ጭብጦች ላይ በነበረን ሰፊ ልዩነት ነው።
የሁሉም ዜጎች ሰብአዊ መብቶች የተከበሩባት፣ ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባት፣ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የተገነባባት፣ የብሔረሰቦች መብት የተረጋገጠበት፣ የሃይማኖት እኩልነት እና አገራዊ አንድነት የተንጸባረቀባት ኢትዮጵያ ትኑረን ብለን ስለጠየቅን፤ ህውሃት ደግሞ በተቃራኒው መንገድ ሁሉንም እየቀነሰች እና እየከፋፈለሽ ስለተጓዘች ነው። ለእነዚህ መርሆዎች በኢትዮጵያ ውስጥ መስፈን ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት ከልባቸው የታገሉ እና ከእስር አንስቶ እስከ ስደት፣ ከአካል ጉዳት አንስቶ እስከ ህልፈተ ህይወት መስዋትነት የከፈሉ ዜጎች ሁሉ ቀድመው የተደመሩ እና የመደመር ጽንሰ ሃሳብ በጠዋቱ የገባቸው ሰዎች ናቸው። ያ ብⶫም ሳይሆን ዛሬ ዶ/ር አብይ በመጽሃፍ ለሰደሩት ሃሳብም ጊዜያቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ህይወታቸውን ጭምር ሰውተው የተግባር ተሳትፎ ያደረጉ እና መስዋትነት የከፈሉ ናቸው።
ሰዎች ለአመታት የሞቱለትን የመደመር እሳቤ በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ግን እንዲህ ጥልቅ እና በረቀቀ መንገድ ሸክኖ በመጽሐፍ አሳትሞ ለትውልድ መማሪያ ማድረግ እጅግ መልካም ነገር በመሆኑ እና ለዚህም ግንባር ቀም በመሆናቸው ዶ/ር አብይ ሊመሰገኑ ይገባል። ይሁን እና ይህ ሁሉ መንግስታዊ ሽር ጉድ ግን ዛሬም አገሪቷ ከካድሬዎች እና አጃቢዎቻቸው ፖለቲካዊ ዳንኪራ አለመውጣቷን ነው የሚያሳየው።
ለማንኛውም ከፊታችን የሚመጣው ምርጫ የቅስቀሳ እና እጩዎችን የማስተዋወቁ ሥራ በገዢው ፓርቲ በኩል በሰፊው እየተሰራበት መሆኑን ይህ የዛሬው ድግስ እና ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲኖ ትራክ መኪና እየነዱ ችግኞችን ውኃ የማጠጣት ትሪኢት ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። አማራጮቻችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከወዴት አላችው? የእናንተስ መጽሃፍ መቼ ነው የሚመረቀው? እንዲህ ባማረ እና በተቀናጀ መልኩ ማኒፊስቶ መጽሐፋችውን ለማስመረቅ አቅሙስ አላችው ወይ? ሚዲያውስ ቀኑን ሙሉ የናንተን የመጽሐፍት ምረቃ ለሕዝብ ያደርስላችሁ ይሆን? የኪነጥበብ ባለሙያዎቹና የመንግስት ተሿሚዎቹስ እንዲህ ጠብ እርግፍ ይሉላችው ይሆን?
አንድ ዶ/ር አብይ ያደረጉትን መልካም ነገር ጠቅሼ ጽሁፌን ላብቃ!!!
 
የመጽሐፉ ገቢ ለበጎ አድራጎት ሥራ እንዲውል መወሰናቸው እጅግ ያስመሰግናቸዋል። እንዲህ ያለው መንግስታዊ ሥልጣንን እራሳቸው ላሳተሙት መጽሐፍ ማስተዋወቂያነት ማዋላችው በገጽታ ግንባታ እና የፓርቲን ሃሳብ በመንግስት ወጪ በማስተዋወቅ እንደተፈጸመ ሙስና ሊያስቆጥርባቸው ቢችልም ገቢውን ለድሃ የአገሪቱ ነዋሪዎች ድጋፍ ማድረጊያ ማዋላቸው የጎለ ጠቀሜታ ስላለው ክፋት አይኖረውም። ሌሎች የተለየ ሃሳብ ያላቸው ሰዎችም ወይም ፓርቲዎች ወይም ድርጅቶች ተወዳዳሪ ሃሳባቸውን በመጽሐፍ ቢያሳትሙ እና ገቢውንም ለተመሳሳይ በጎ አድራጎት ሥራ ቢያውሉ ማን እንዲህ ያለውን መድረክ ይፈጥርላቸዋል? ያ ካልሆነ የሃሳብ ገበያው ሥልጣን እና አቅም ባላቸው ጥቂት ሰዎች ብቻ ይያዛል። በቅርቡ “የተጠለፈው ትግል” በሚል ርዕስ መጽሃፍ ያሳተመው ሰው፣ አታሚዎቹ እና ሌሎች የህትመቱ ተባባሪዎችን ለቃቅመው እስር ቤት ያጎሯቸው ለምን ይሆን? ዛሬም ሳንሱር አለ ማለት ነው? ያልተደመሩ ሃሳቦች ይታፈናሉ ማለት ነው? የእነ  ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩን እስር ደግሞ ሳስብ ሳይለንሰር የተገጠመለት አፈና እየተጧጧፈም ይመስላል።
ድንቅ እሳቤዎችዎን በመጽሐፍ አሳትመው ስላቀረቡልን አዕምሮ ያለምልም ብያለው! መጽሐፍዎትን ካነበብኩ በኋላ ደግም ውስጡ ባሉት ጭብጦች ላይ ያሉኝን ሃሳቦች ይዤ ብቅ እላለው።
ቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic