>

የአይጥ ጉድጓድ የማሱ ጸበኞች እና የሰላም ተሸላሚው አብይ!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የአይጥ ጉድጓድ የማሱ ጸበኞች እና የሰላም ተሸላሚው አብይ!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
ነገሩ የቶም እና የጂሪ ጉዳይ እንዳይሆን!?!
ዛሬ ጠቅላይ ሚንስትሩ ፓርላማ ቀርበው ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጡትን ምላች ተከትሉ የOMN ኃላፊና ባለቤት ምላሽ ሰጥተዋል። ጠ/ሚኒስትሩ በዛሬ ማብራሪያቸው ሕግን እየጣሱ እና በማህበረሰቡ ውስጥ ግጭት እየቀሰቀሱ ስላሉ ሚዲያዎች ይህን ብለዋል፤ “የውጭ አገር ዜጋ የሆናችሁ የሚዲያ ባለቤቶች የኢትዮጵያ ፓስፖርት የሌላችሁ የሚዲያ ባለቤቶች ስትፈልጉና ሰላም ሲሆን እዚህ ተጫውታችሁ እኛ ችግር ውስጥ ስንገባ ጥላችሁ የምትሄዱበት ሁለት አገር ያላችሁ ሰዎች ትግስት እያደረግን ያለነው አውዱን ለማስፋት ነው” ብለው ማስጠንቀቂያ አዘል ተግሳጻቸውን አስተላልፈዋል። ይህንንም ተከትሎ በደቂቃዎች ውስጥ የOMN ኃላፊ “እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል፤ አለች አይጥ።
ከንግዲህ ኑⶂዓችንም፤ ሞታችንም፤ ቀብራችንም ኦሮሚያ ላይ ብለን ጠቅልለን ገብተናል”።
ይህን ለውጥ በመቃወም እና ከሕግ ተጠያቂነት ለማምለጥ ጉድጓድ ከማሱት አካላት መካከል የOMN ኃላፊ አራተኛው መሆናቸው ነው። የመጀመሪያው ህውሃት ነው። ህውሃት የትግራይን ህዝብ እንደ መያዣ አድርጎ ክልሉን ከፌደራሉ መንግስት በነጠለ መልኩ መቀሌ ላይ የአይጥ ጉድጓዱን መሽኮ ለውጡን እየተገዳደረ ያለ እኩይ ድርጅት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ቀደም ሲል የኦነግ የነበረ እና በኋላ ደግሞ ስሙ ላይ ሽኔ የሚል ቃል የቀጠለው ኦነግ ሽኔ የሚባለውና አፍንጫው ድረስ የታጠቀው እኩይ ኃይል ነው። ሦስተኛው በትጥቅ ተደራጅቶ እራሱን የአማራ ሕዝብ ጠባቂ ለማድረግ እየተደራጀ ያለው ፋኖ የሚባለው ቡድን ነው። አራተኛው ደግሞ ዛሬ በይፋ የተናገረው እና ኦሮሚያ ክልልን እንደ መሸሸጊያ ጎድጓድ የቆጠረው እና የአይጥ ስልት የነደፈው የቄሮ መሪ እና የOMN ኃላፊ ጃዋር መሃመድ ነው።
+ የትግራይን ሕዝብ ያልደመረ ለውጥ አገራዊ ለውጥ ሊሆን ስለማይችል ትግራይን እና የትግራይን ሕዝብ ከህውሃት የአፈና መዋቅር ማውጣት የመንግስት እና የቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ እዳ ነው። ህውሃት የትግራይን ሕዝብ በ hostage ይዛ የቀጣይ የፖለቲካዊ እጣ ፈንታዋን መደራደሪያ አድርጋዋለች። የትግራይን ሕዝብ ከህውሃት መዳፍ ነጻ ማውጣት የመንግስት፣ የመብት ተሟጋቾች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የቀረው ሕዝብ ኃላፊነት ነው።
+ በቅርቡ ጎንደር ላይ በተካሄደ ስብሰባ የፋኖ ቡድን አመራሮች ወጣቱ እንዲታጠቅ፣ ጠመንጃውን አዘጋጅቶ እንዲጠብቅ፣ የተኩስ ስልጠናም እንዲወስድ፣ አንድ ለአምስት ተደራጅቶ ጠላትን በተጠንቀቅ እንዲጠብቅ የሚያሳስቡ መግለጫዎች በመድረክ መሪዎች እና በፋኖ አመራሮች ሲሰጥ ከተቀረጸው ቪዲዮ ላይ ለማየት ይቻላል። መንግስት ባለበት አገር በምንም መልኩ ይህ አይነት መሳሪያን የቀላቀለ አደረጃጀት ተቀባይነት የለውም።
+ በተመሳሳይ ሁኔታ የኦሮሞ አክራሪ ብሔረተኞች እንደ መሳሪያ ሊጠቀሙባቸው እየሞከሩ ያሉት ወጣት ቄሮዎች እንዲሁ በተሳሳተ ጎዳና እየሄዱ መሆኑን ከአመት በፊት ከታዩት ምልክቶች አንስቶ ከሰሞኑ ብቻ በቄሮ አባላት እየተፈጸሙ ያሉት አስነዋሪ እና ሕገ ወጥ ተግባራትን በማስረጃ ማሳየት ይቻላል። መንገድ መዝጋት፣ የሕዝብ ንብረት ማውደም፣ ከንግድ ቤቶች እና ከትራንስፖርት መገልገያዎች ላይ የተጻፉ ምልክቶችን እና ጽሑፎችን እየፋቁ የሰው ንብረት ማበላሸት እና መብት መግፈፍ፣ ስብሰባዎችን ማወክ እና በየመንደሩ አንባጓሮ መፍጠር ግልጽ የሕግ ጥሰቶች ናቸው።
የዶ/ር አብይ አስተዳደር አገሪቱ ከገባችበት ቅርቃር እንድትወጣ የሚጠበቅበትን ትልቅ ኃላፊነት በቀላሉ እንዳይወጣ ትልቅ እንቅፋት ከሆኑበት ነገሮች መካከል እነዚህ የአይጥ ጉድጓድ የማሱ ኃይሎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው። አንድ ሰው ወይም ቡድን ለሕግ እና ለሥርዓት አልገዛም ብሎ፣ ሽምግልናን ወደጎን ገፍቶ ከሰለጠነ የዲሞክራሲያዊ ትግል እና ሰላማዊ የውይይት መንገድ አፈንግጦና ይልቅም ወደ ጸብ እና ጦርነት የሚያመራ ከሆነ መንግስት እና ሕዝብ እነዚህን ኃይሎች ለሕግ ተገዢ እንዲሆኑ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
መንግስት ጉድጓድ የማሱትን እና የአይጥ ስልት የተከተሉትን ወገኖቻችንን ከሕግ በታች ሆነው እንደማንኛውም ዜጋ ሕግ እና ሥርዓት አክብረው እንዲኖሩ ከንግግር ያለፈ የተግባር እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል። ወጣቶችን በየጊዜው እያፈሱ በጦር ካምፑ እያጎሩ አሰቃይቶ መልቀቅ መፍትሔ አይሆንም። ይልቁንም ይበልጥ በማህበረሰቡና በመንግስት ላይ እንዲያቄሙ እና ለከፋ ጥፋት እንዲዘጋጁ ያደርጋቸው ይሆናል እንጂ። ያለፉት ልምዶች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። ወጣቶቹን እንደመሳሪያ ከሚጠቀሙባቸው ኃይሎች የማስጣሉ ሥራ እና የአይጦቹን ጉጓድ መድፈን ግን የግድ ይላል።
አገር በፍቅር እንዲደምቅ ለማድረግ የሕግ የበላይነትን ማጽናት የግድ ይላል። ሕግን ማጽናት እና አፈና ለየቅል መሆናቸውን ልብ ይለዋል።
ቄሮ እና ፋኖዎች ተመከሩ፤ ሕግ የሚባል ነገር አለ።
Filed in: Amharic