>
5:13 pm - Friday April 19, 1963

ለጊዜው በአጋች ታጋች ድራማው ዙሪያ ጥያቄ እናንሳ እስኪ!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ለጊዜው በአጋች ታጋች ድራማው ዙሪያ ጥያቄ እናንሳ እስኪ!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
+ ማነው የዋሸው? ጃዋር? የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ወይስ የኦዴፓ ም/ሊ/መንበር?
+ መንግስት በሕዝብ ገንዘብ ጥበቃ የሚያደርግለትን ጃዋርን በሌሊት የሚከብበት ምን ክምንያት አለ? ማለቴ ተከቦ የተቀመጠው በመንግስት ጠባቂዎች አይደለም ወይ?
+ ለምን ጃዋርስ ተፈጠረ የተባለውን ነገር ሆን ተብሎ በመንግስት የተቀነባበረ እና እኔን ለማጥቃት የተፈጸመ ድርጊት ነው አለ? ማለቴ ይህ አይነት ጥርጣሬ ካለው እንዴት በመንግስት ታጣቂዎች እየተጠበቀ እንቅልፍ ወስዶት ያድራል? እንዴት እንዲህስ ሊያስብ ይችላል? ወይስ ጠባቂዎቹን የራሱ አድርጓቸዋል?
+ ከመቼ ወዲህ ነው የመንግስት ታጣቂዎች በመንግስት ተመድበው ሳለ እራሱ መንግስት፤ ሊያውም እንደ ጃዋር አገላለጽ ዋናው ኮማንደር ለቃችው ውጡ ሲላቸው እንቢ ሊሉ የቻሉት? ከመንግስት ይልቅ ታዛዥነታቸው ለጃዋር ያደላ ነው ማለት ነው?በዚህ አይነት መንግስት በሌሎች ሥፍራዎች ያሉትንስ ወታደሮች ማዘዝ ተስኖታል? ከመቼ ወዲህ ነው መንግስት የመደበው ፖሊስ እና ወታደር ትዕዛዝ የሚቀበልበትን ሰዓት የሚመርጠው? ምነው ስንቱን በእኩለ ሌሊት ቤቱን ሰብረው እያዳፉ ይወስዱ የለም ወይ?
+ ይሄ ትእዛዝ ሰጠ የተባለው ዋና ኮማንደር ማን እንደሆነስ አይታወቅም ወይ? ከታወቀስ መንግስት እንዴት አላውቅም አለ?
+ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የግል ጥበቃዎችን ስናነሳ ቆይተናል በልው ቀድሞም የተወሰነ ነገር መሆኑን ገልጸዋል፤ በጅዋር ላይ ግን ይህ ትዕዛዝ አልተሰጠም ካሉ ታዲያ ማን አዘዘ? ለምንስ ከተወሰነ በጃዋር ላይ ቀድሞ ሳይፈጸም ቀረ? ወይስ ትዕዛዝ ተላልፎለት ጭለማን ተገን ለማድረግ አድፍጦ ይጠብቅ የነበረ የመንግስት አካል ነበር?
+ አንድ ስማቸው ንዳይገለጽ የጠየቁ የመንግስት የደህንነት ባለሥልጣን ድርጊቱ በሌሊት መፈጸሙ ልክ ባይሆንም ትእዛዙ ግን ቀድሞ መሰጠቱን ከተናገሩ ክፍተቱን የሚጠቀም ድብቅ ኃይል በመንግስት ውስጥ መኖሩን አያሳይም ወይ?
+ የአቶ ሽመልስ ይቅርታስ መነሻው በመንግስት የተወሰደው እርጃ ስህተት ነው ከሚል ነው ወይ? ወይስ በሌሊት መፈጸሙ? ጥበቃው ይቀጥልልሃልን ምን አመጣው? እንዲያ ከሆነ ለምን የመንግስት አካላት እርስ በርሱ የሚጋጭ መግለጫ መስጠት አስፈለጋቸው?
+ ጃዋርስ የተፈጠረውን ነገር ለመንግስት ባለሥልጣናት በተለይም ከኦዴፓ ሰዎች ጋር ካለው ቅርበት አንጻር ችግሩን በውስጥ መስመር ከእነሱ ጋር መነጋገር እና መፍታት እየቻለ ለምን በማህበራዊ ድህረ ገጽ ለደጋፊዎቹ የድረሱልኝ ጥሩ አቀረበ? አቅሙን ሊያሳይ? ወይስ በፍርሃት ከመደናበር?
+ ጃዋር ቤት አካባቢ ደረሰ የተባለው ከበባ ምሽቱን ከሆነ የተፈጸመው ለምን ፖሊስ እና የመንግስት አካላት ሌሉቱን ሁኔታውን በማረጋጋት ሕዝቡ ወደ አደባባይ ሳይወጣ በፊት አፋጣኝ ምላሽ አይሰጡም ነበር? የአቶ ሽመልስ ካመሻሸ መግለጫ መስጠት ምን ይሉታል? ከተበጠበጠ በኋላ ማንን ሊያረጋጉ ነው?
+ በሕዝቡ መካከል የእርስ በርስ ግጭት እንዲነሳ፣ በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት ማነው ተጠያቄው?
+ መንግስት በምን ምክንያት ነው ኪሱ በዶላር ላበጠ ሰው ከድሃ ሕዝብ በተገኘ የግብር ገንዘብ ደሞዝ እየከፈለ ለጅዋር ለዚህን ያህል ጊዜ ጥበቃ የሚመድበው?
+ ጃዋር በቅርቡ ለህውሃት ያቀረበው የአጋርነት ጥያቄ፣ በLTV ቀርቦ አብይ ላይ ያንጸባረቀው አቋም እና ድንፋታ፣ የጃዋር የድረሱልኝ ጩኸት እንዳሰማ ህውሃት በመግለጫ አለሁልህ ማለቷ ብዙዎች እንደሚሉት የተጠነሰሰ ነገር ይኖር ይሆን? ክስተቱ ከአብይ የውጭ ጉዞ ጋርስ ይገናኙ ይሆን? ተደጋግሞ እንደተስተዋለው በአገሪቱ የተከሰቱ ዋና ዋና ሰበር ዜናዎች አብይ እግሩ ወጣ ማለቱን ተከትለው የሚመጡ ስለነበሩ ነው።
እንግዲህ የእኔ አዕምሮ ውስጥ እነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ እየተንገዋለሉ አብረውኝ ያድራሉ። ለተጎዱት ሰዎች ከማዘን ባለፈ ምን ለማለት ይቻላል።
ከላይ የተዘረዘሩት ጥያቄዎች ምላሻቸው ምንም ይሁን ምን መንግስት ግን በአገሪቱ ውስጥ የሕግ የበላይነት ለማስፈን የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ ይገባል። ሕዝቡም ለመብቱ ብቻ ሳይሆን ለሕግ አክባሪነትም አብሮ ሊቆም ይገባል።
መልስ ያላችው ወዲህ በሉ፤ እንደ እኔ በጥያቄ የተዋጣችው አብረን እንጠይቅ።
Filed in: Amharic