>

መንጋን በሕግ እንጂ በፍቅር መግራት አይቻልም! (ያሬድ ሀይለማርያም)

መንጋን በሕግ እንጂ በፍቅር መግራት አይቻልም!
ያሬድ ሀይለማርያም
 
አብዲ ኢሌን ከሕግ በታች ያዋለ መንግስት ጃዋርን እያሽሞነሞነ ይዞት ሊቀጥል አይችልም!!!
መንጋ ፍቅር አያውቅም፣ መንጋ ሰላም አያውቅም፣ መንጋ ክብር አያውቅም፣ መንጋ ሕግ አያውቅም፣ መንጋ ሽምግልና አያውቅም፣ መንጋ ነጻነትን አያውቅም፣ መንጋ ጉርብትና እና ወዳጅነት አያውቅም፣ መንጋ አገር አያውቅም፣ መንጋ ዲሞክራሲ እና መብት አያውቅም፣ መንጋ ዕራይ የለውም፣ መንጋ ዘር የለውም፣ መንጋ ኃይማኖት የለውም። መንጋ የውርጋጦች እና የሥርዓት አልበኞች ስብስብ ነው። ይህን ኃይል እንደ መሳሪያ ተጠቅሞ የፖለቲካ ፍላጎቱን ሊያሳካ የሚፈልግ ግለሰቡም ሆነ ቡድን ካለ ከመንጋው አይሻልም። ለመብት እና ለነጻነት የታገሉትን ቄሮዎች፣ ፋኖዎች፣ ዘርማዎች እና ሌሎች የወጣት ቡድኖች ሁሉ ከዚህ መንጋ ለይቼ ነው የማያቸው። እነሱ የሰላም፣ የነጻነት እና የመብት ዋጋ የገባቸው ሰዎች ናቸው።
ይህ ለውጥ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የመንጋ ኃይል በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ቀላል የማይባሉ አደጋዎችን በዜጎች እና በአገር ላይ አድርሰዋል። በኦጋዴን ከአንድ አመት በፊት በአብዲ ኢሌ ይመራ የነበርው መንጋ ክልሉን ወደ ጦር ቀጠና ቀይሮት ለተወሰነ ጊዜ የከፋ አደጋዎችንም ሲያደርስ ቆይቷል። ጅጅጋ ውስጥ በዚህ ሰው የሚመራ መንጋ በርካታ ንጹሃን ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል፣ አቁስሏል፣ የአይማኖት ቤቶችን አውድሟል፣ ዘርፏል፣ ተቋማት ላይ ጥቃቶችን ሰንዝሯል። ዛሬ ክልሉ በአንጻራዊ ሰላም ውስጥ የሚገኘው መንግስት መረር ያለና ሕግን መሰረት ያደረገ አቋም በአፋጣኝ ወስዶ ክልሉን ከእነዚህ መንጋዎች እና መሪዎቻቸው እጅ ነጻ ማውጣት ስለቻለ ብቻ ነው። ያ ባይሆን ኖሮ ዛሬ ሶማሊያ ክልል የደም መሬት ትሆን ነበር። ለሌሎች ብሔሮች ብቻ ሳይሆን ለክልሉ ተወላጆችም አትተርፍም ነበር።
ዛሬ ደግሞ ኦሮሚያ ክልል በተመሳሳይ ሁኔታ በመንጋዎች እየታመሰች ነው። እንደ አብዲ ሂሌ ገንዘብ እና የመንጋ ድጋፍ ያሰከረው ጃዋር መሃመድ እንደ ደጋፊ የሚቆጥራቸው፣ ሲጨንቀው ድረሱልኝ ብሎ የሚጠራቸው፣ ሲሻው መንጋድ ዝጉ፣ ሲሻው መንግስት ላይ አምጹ፣ ሲሻው ወደ ቤታችው ግቡ እያለ የሚያዛቸው የመንጋ ኃይሎች ባለፉት ሦስት ቀናት ክልሉን ወደ ቀውስ ቀጠና ቀይረውታል። እጅግ ለአይን የሚሰቀጥጡ እና ለመስማት የሚከብዱ የጭካኔ እና የአውሬ ተግባራት በክልሉ በሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ነው። ሰዎች አካላቸው እየተቆራረጠ በሚዘገንን ሁኔታ ተገድለው አስከሬናቸው በገመድ በየመንገዱ ሲጎተት የሚያሳዩ ምስሎች እና ቪዲዎች ደርሰውናል።
መንገዶች ተዘግተዋል፣ ቤቶች፣ ተቋማት እና የአምልኮ ቦታዎች ሳይቀር የጥቃት ኢላማ ተደርገዋል። ንንጹሃን ዜጎች ላይ አስነዋሪ የጥቃት እርምጃዎች ዛሬም እየተወሰዱ ነው። ይህ አይነቱ የመንጋ ንቅናቄ እና ወረራ እንዲካሄድ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ጀዋር መሃመድ ግን ምንም እንዳልተፈጠረ ያህል በተንጣለለ ቪላው ውስጥ ሆኖ ዛሬም ይፏልላል። ሲሻው ያስፈራራል፣ ሲሻው ትዕዛዝ ይሰጣል፣ እሱ ወደ ወረደበት አዘቅት ሌሎች አዛውንት ፖለቲከኞችንም ጎትቶ በመሳብ ከመኖሪያ ቤቱ ሆኖ ጋዜጣዊ መገለጫ ይሰጣል። ያሻውን በሚቆጣጠረው ሚዲያ ያስነግራል። ሕዝብን ያስፈራራል፣ መንግስት ላይ ይዝታል፣ መልሶም መፍትሔው እኔ እጅ ነው ያለው ይለናል።
ለእኔ በአብዲ ኢሌ እና በጅዋር መሃመድ መካከል ያለው ልዩነት አልገባህ ብሎኛል። ሁለቱም ደጋፊዎች አሏቸው፣ ሁለቱም የታጠቀ መንጋ ከቧቸዋል፣ ሁለቱም በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ከሕግ በላይ ናቸው። ሁለቱም የንጹሃን ደም እና የአገር ሰላም የሚገዳቸው ሰዎች አይደሉም። ሁለቱም በገንዘብ እና በጡንቻ ናላቸው የዞረ ግልገል አምባገነኖች ናቸው። አብዲ ኢሌን ከሕግ በታች ያዋለ የመንግስት ጅዋርን እያሽሞነሞነ ይዞት ሊቀጥል አይችልም።
+ ጃዋር ከቡራዩ ጭፍጨፋ ጀርባ ሆኖ ምን እንደሰራ መንግስት ጠንቅቆ ያውቃል። እሱም በማናለብኝነት አገር የሃዘን ማቅ በደፋበት ጉዳይ አደባባይ ወጥቶ ሲዘባበት የጠየቀው አካል አልነበረም። በተቃራኒው የቡራዩ እልቂት ተደፋፍኖ እውነቱ እና የጉዳቱ መጠን በገለልተኛ ወገን እንኳ ሳይጣራ በኦዴፓ እርብርብ ተሸፋፎ እንዲቆይ ተደረገ። በቡራዩ በግፍ የተሰዉ ዜጎች ደም ግን ዛሬም የፍትሕ ያለ ትላለች።
+  ጃዋር በአደባባይ ለአመጽ እና ለእልቂት ያደራጀው ኃይል የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ አስታኮ በአዋሳ እና ዙሪያዋ ባሉ ከተሞች ተመሳሳይ እልቂት አስከተለ። ግለሰቡ አደራጅቶ በአደባባይ ጃስ ያላቸው መንጋዎች እጅግ አሰቃቂ በሆነ መልኩ ንጹሃን ዜጎችን ከሆስፒታል አልጋ ላይ ሳይቀር እየጎተቱ አውጥተው ገደሉ። አባት እና ልጅን ከአንድ ቤት በሚሰቀጥጥ ሁኔታ ገደሉ። በሲዳማ የተፈጸመውም ዘግናኝ ድርጊት በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ድርጊት ፈጻሚዎቹ ብቻ ሳይሆን አስተባባሪዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ በቂ ሥራ አልተሰራም። መንግስት መንጋዎቹን ለቅሞ ዋናውን እልቂት መሪዎች ግን የጎሪጥ እያየ አለፈው።
+ ዛሬ ደግሞ ይሔው ግለሰብ በጠራው አመጽ እና ሁከት አገር እየታመሰ፣ ሕዝብ እያለቀ  እና ንብረት እየወደመ ነው። ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም መግባት አልቻሉም። በሦስት ቀናት ብቻ ከሃምሳ በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ቀላል ግምት የማይሰጠው ንብረት ወድሟል።
ጨዋውን የኦሮሞ ሕዝብ ከቀሪው ኢትዮጵያዊ ጋር ለማጋጨት እና ለማቆራረጥ ጀዋር እና ከጎኑ የቆሙ ኃይሎች ብዙ እርቀት ተጉዘው ዛሬ ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። የኦሮሞ ምሁራን ይህ አይነቱን አስነዋሪ ተግባር በሕዝባቸው ስም ሲፈጸም ገሚሶቹ ዝምታን መርጠዋል፣ ጥቂቶች ከጀዋር ጎን ቆመው አጋርነታቸውን እያሳዩ ነው፣ ሌሎቹም ነገሩ በሰላም እንዲፈታ የበኩላቸውን እየጣሩ እና ድርጊቱንም በይፋ ወጥተው እያወገዙ ነው።
በዝምታ ውስጥ ካሉት መካከል እጅግ አከብራቸው የነበሩ የመብት አቀንቃኞች እና ታዋቂ ሰዎች መኖራቸው ግን እጅግ እንዳሳዘነኝ ለመግለጽ እወዳለሁ። እስክንድር ነጋ ለምን ሰልፍ ጠራ ብላችው አበደ ፈረሴ ስትሉ የነበራችው የመብት ተሟጋቾች ዛሬ በአንድ ምራቁን ባልዋጠና በስሜት በሚጋልብ ጽንፈኛ ሰው አገር ሲታመስ፣ የኦሮሞን ሕዝብ ጨምሮ ዜጎቺ በአደባባይ ሲታረዱ፣ ንብረት ሲወድም እና ሰላም ሲጠፋ ምነው ድምጻችው ጠፋ?
በአገሪቱ ውስጥ ተመዝግባችው የምትንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች አገር በመንጋ ሲታመስ ምነው የእናንተስ ድምጻችው አይሰማ? በሕግ አምላክ አይባልም ወይ? መንግስትን ከጎኑ ቆማችው ሕግ እንዲያስከብር ድጋፋችውንም፣ ማሳሰቢያችሁም፣ ስጋታችሁም አትገልጹም ወይ? ሕዝብንስ አታረጋጉም ወይ? በተቃራኒው የጥፋት ኃይል ከሆነው ከጃዋር ጎን የተሰለፉ ድርጅቶች እና ግለሰቦችንስ መገሰጽ አይገባም ወይ?
አገር በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ እያለች ላለፉት ሦስት ቀናት ከጠ/ሚኒስትሩም ሆነ ከጽ/ቤታቸው ምንም ነገር አለመሰማቱ ግራ ያጋባል። ምናልባትም እነሱም እንደ እኔ ግራ ተጋብተው ይሆናል። ነገር ግን እንደ አንድ አገርን የሚያስተዳድር ኃይል ሕዝብን ማረጋጋት እና መንግስት በቀጣይ ስለሚወስዳቸው እርምጃዎች በፖሊስ እና በመከላከያ ሰራዊት ከሚሰጡት መግለጫዎች በተጓዳኝ የጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ለሕዝብ መግለጫ ሊሰጥ ይገባዋል። ምነው በእኩለ ሌሊት መፈንቅለ መንግስት መጣብን ብላችው መግለጫ ትሰጡ አልነበረም ወይ? መፈንቅለ አገር፣ መፈንቅለ ሕዝብ፣ መፈንቅለ ሰላም ሲካሄድ ድምጻችው መጥፋቱ አገባብ ነው ወይ?
መንግስት ነገሮች ሙሉ በሙሉ ከቁጥጥር ውጭ ከመውጣታቸው በፊት ጠመጣጣኝ እና ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ አገሪቱን ከመንጋ፣ ሕዝቡንም ከእልቂት እና ስጋት ሊታደግ ይገባል።
ለሞቱት ወገኖቻችን ሃዘኔን እየገለጽኩ፤ ለቤተሰቦቻቸው እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን እመኛለሁ።
Filed in: Amharic