አምባሳደር ዓለማየሁ አበበ ሸንቁጥ
የሰው ዘር መገኛ የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ ከቅድመ ታሪክ ጀምሮ ለሺ ዘመናት በአፍሪካ ቀንድ ግዛቱዋ ሲጠብና ሲሰፋ ወደር ያልተገኘለትን የስልጣኔ ቅርስ በአክሱም ፤በላሊበላ፤በጎንደርና በሌሎች አካባቢዎች የተገነቡት የሥራቸው ምጥቀት አኩሪ ገድል መሆኑን ማንም የማይክደው አንጸባራቂ ውጤት ነው፡፡
በዘመነ መሣፍንት ሁሉም በየአካባቢው ጉልበቱ የፈረጠመውን እያነገሠ ከየጎረቤቱ ጋር በጎሪጥ እየተያየ ያለበትን ዘመን ለአንድዬና ለመጨረሻ ጊዜ ለአገራቸው ብሩህ ራዕይ የነበረራቸው ብዙ ርቀት የሚያዩት መይሳው ከሣ በኢትዮጵያ ላይ የነገሡት አጼ ቴዎድሮስ ኃይላቸውን በመጠቀም አገሪቱን እንደገና በአንድ መስተዳደር ሥር በማቁዋቁማቸው እነሆ መተካካቱ ቢከፋም ቢለማም አንዲቱ አገራችን በነጻነት በየአንዳንድ መሪ እሰከሁን ዘልቃለች፡፡ አጼ ዮሐንስም ሆኑ አጼ ምኒልክ ሲመች በፍቅር ሳያመች በሃይል በዓለመ ዙሪያ ያሉት አገሮች በተጠቀሙበት ዘዴ በመጠቀም የአገራችንን ነጸነት አስጠብቀው ለተከታዩ ትውልድ አስተላልፈዋል፡፡
ከውጭ የተቃጣን ጥቃት በ1888 ዓ.ም. በአጼ ምኒልክ መሪነት ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ጭብጦውንና መሣሪያውን አንግቶ በባዶ እግሩ ሺ ኪሎሜትር ተጉዞ በመዝመቱ መስዋዕት ከፍሎ ነጻነቱን አስከብሮዋል፡፡ በእድሜያችን ያየነውና የተካፈልንበት የ1928 ዓ.ም. ጦርነትም የፋሽስት የኃይል ሚዛን በአየለበት አኩሁሃን አዋጪው የሽምቅ ውጊያ መሆኑን ሕዝቡ ተገንዝቦ በየአካባቢው የጎበዝ አለቃውን እየመረጠ ለአምስት ዓመት በዱር በገደሉ እየተነቃነቀ ጠላትን እንቅልፍ አሳጥቶ አባሮታል፡፡ በሺ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በየሸንተረሩ ረግፈው የአውሮ ሲሣይ ሲሆኑ እድሉ የገጠመን የድሉ ተካፋይ በመሆን እነሆ እድሜ ጠግበን እስከዛሬው ደርሰናል፡፡
ባሁኑ ወቅት እየተከሰተ ያለው “በእጅ የያዙት ወርቅ እንደመዳብ ይቆጠራል እንዲሉ” በዚች ታሪኩዋ የገነነና ድንቅ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ሃገር ይዘን ተከባብረን ፤ተቻችለንና ተደጋግፈን እንዳንኖር የተሸረበብንን የጥቂት ሴሬኞችን ጥንስስ ዓላማ በጣጥሰን ምትክ የሌላትን አገራችን ተጠናክራ ለዓለም የድርሻዋን ከማበርከት ይልቅ እንዴት የጥፋት ጎዳና እንመርጥላታለን፡፡ ለመሆኑስ ሌላ መሸሸጊያ ከየት እናመጣለን፡፡
የቀን ጅቦችና ጠባቦች አገራችንን እራቁቱዋን ቢያስቀሩዋትም ፤ እፍኝ የማይሞሉ ሊሂቃን ተብዬዎች ትርክት የኢትዮጵያን ገናና ታሪክ ዳዋ በማልበስ “ሁሉም የኛ” በማለት አገርን አተራመወሶ አዘቅት ለመጣል የሚደረገውን ፍሬ አልባ ሙከራ በዘምታ የሚመለከተው መሃል ሠፋሪ የእናት አገራችን አንድነት ተጠብቆ እንዲኖር ድምጹን ማሰማት ይጠበቅበታል፡፡ ዝምታውንም ሰብሮ “ኢትዮጵያን እናድን” በሚል መርህ የሲቪክ ንቅናቄ ተዋናኝ ሊሆን ይገባዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳና እንደ መምህር ታዬ ቦጋለ ያሉ የታሪክ ተመራማሪዎች እንደሚገልጡት የሥር መሠረታችን አንድነት የተረጋገጠና እስቶቻችንም ወደር የሌለው መሆኑ የማይታበለውን ሀቅ ታሪክ አጣቅሰው ለሚሰማ ሁሉ አሰምተዋል፡፡ ስለሆነም እጣ ፈንታችንም አንድ የሆንን ሕዝቦች እንዴት የመጠፋፋትን የሴረኞች ሴራ ሰማተን ለጥቂት ሴረኞች እንመቻለን፡፡ ቁጭ ብለን ያስቀመጥነውን ቆመን ማውረድ አልቻልንም እንዳሉት ፊታውራሪ ሓብተጊዮርጊስ እኛም ዝም ብለን ያሳለፍነው የቀውጢ ሰዓት ሁዋላ በእሪታና በሆታ ልናስተካክለው እንደማንችል ከወዲሁ ልንገነዘብ ይገባናል፡፡
በዛሬው በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዓለማችን ከሰባት ቢሊዮን በላይ ያቀፈችው ሕዝብ መንደርተኝነት እውን በሆነበት ወቅትና በሥልጣኔ የገፉት በሕዋ የሚገኙ ኩዋክብቶች ላይ መኖሪያ ለመመሥረት በሚሽቀዳደሙበት ዘመን ሠላማችንን ጠብቀን በአንድነትና በመተባበር የዕለት ጉርሱን ላጣው፤ ዘመኑ እንደሚፈቅደው ህዝባችን ንጹህ ውሃ ከደጃፉ እንዲያገ ባለማድረጋችን ከብዙ ኪሎሜትር በላይ ተጎዞ ከወራጅ ውሀ በመጠቀም የበሽታ መናሄራ ከመሆን ያላወጣነው፤ ለማገዶው የከብት እዳሪና ጭራሮ በመልቀም የተሰማራውን ዓለም ስትፈጠር በወቅቱ ህይወቱን ለማቆየት በተጠቀመበት ግኝት ላይ የሙጥኝ ብለን የያዝነውን ሳናዘምንለት፤
ልጆቻችን የትምህርትና የጤና አገልግሎት በየአካባቢያቸው ያልተዳረሳቸውን ሳንታደግ፤ ለሺ ዓመታት አብሮ የኖረውንና ተጋብቶና ተዋልዶ በሠላም የሚኖረውን ማፈናቀል፤ የዘር ሐረግ እየመዘዙ የራስን ብቻ ተጠቃሚ ማድረግና ሌላውን ማግለልና መጨፍለቅን መፈለጋችንና በዚሁ ጎዳና ከተራመድን ለልጆቻችን የምናስተላልፈው መልዕክት ብርሃን የተሞላበት ራዕይ ሳይሆን ድቅድቅ ጨለማን ይሆናል ብለን ማሰብስ እንዴትስ ይሳነን፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ወጣቱ ከስደት አዙሪት ጋር የተቆራኘው፡፡
አባቶቻችንና እናቶቻችን ለአገራቸው የሕይወትና የአካል መስወዕትነት ከፍለው ለአገራቸው ድልን ያተረፉ “ልጣቸው የተራሰና አንድ እግራቸው በመቃብር አፋፍ” የሚገኙ በአሁኑ ወቅት በአገራቸው የሚታየው አለመግባባትና ጎሳን መሠረት ያደረገ አካሄድ ሲመለከቱ ያ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለው ከንቱ እንደሆነና ይህንንስ ከማየት “ሞቴን ባሳመረው” እስከማለት አምላካቸውን የሚጨቀጭቁ አሉ፡፡ “ሞቴ ከሀገሬ በፊት” እያሉ የሚማፀኑ አሉ፡፡
በመታደል ሕዝባችን ሠላም ካገኘ ታታሪነቱ የተመሠከረለት ፤ በተፈጥሮ ፀጋ የታደለች አገርን ይዞ ፤ ሙሉ ትኩረቱን በአገር ልማት እንዲሰማራ ቢደረግ ከዳር እስከ ዳር ለአጠቃላይ ሕዝባችን ተደራሽ የሚሆን ብልጽግናን ለማስገኘት የሚገታን ምንም ሐይል አይፈጠረም፡፡ እንኩዋን ለአንድ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ይቅርና ለሁለትና ሦስት እጥፍ ሚሊዮኖች ልትተርፍ የምትችል አገር እንዳለን ልንዘነጋ አይገባንም፡፡
“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንዲሉ በአንድነት በመተሳሰብ እጅ ለእጅ ተሣስረን ለመጉዋዝ ካልወሰን ይህን ቀውጢ ቀን መሻገር ያቅተንና ሁላችንም ተጎጂዎች ሆነን መመለሻው እንዳያጥረን ቆም ብሎ በማሰብ ከየራሳችን የግል ጥቅም፤ ብሎም የጎሳ ጥቅም ብቻ ከማሰብ አገራችንን እናስቀድም ፤ሁሉም ወገኔ ነው፤ ሁሉም ተጠቃሚ ይሁን ፤ በማለት ብንንቀሳቀስ ሌላው ቀርቶ ሰማዩን መቡዋጠጥ እንደምንችል አቅሙ እንደለን መዘንጋት የለብንም፡፡
ኢትዮጵያ ክንዱዋን አስተባብራ ልጆቹዋን አቅፋ በብልጽግናና
በነጻነት እንድትኖር እግዚአብሔር ይርዳት፤
ኢትዮጵየ ዛሬም ነገም ተነገወዲያምበልጆቹዋ ታፍራ ለዘላለም ትኑር፡፡