>

በግፍ ለተገደሉት ኦርቶዶክሳውያን ጸሎተ ፍትሐት ተደረገ!!! (ሀራ ዘ ተዋህዶ)

በግፍ ለተገደሉት ኦርቶዶክሳውያን ጸሎተ ፍትሐት ተደረገ!!!
ሀራ ዘ ተዋህዶ
 
* “እግዚአብሔር የሚጠብቀንን አንድ ኀይል ይላክልን! 
* እንባዋ አስፍሳ ለህዝቧ ያማለደችውን  ራሔልን ይላክልን! 
* ጸሎታቸው የሚሰማውን ይላክልን!” 
• “አገራችን ነው፤ ቤታችን ነው፤ ኢትዮጵያ ናት፤ መንግሥት አለ ብለው፣ ታክስ እየከፈሉ፣ ልጆቻቸውን እያሳደጉ፣ እያስተማሩ ባሉበት፣ አዝመራቸውን በሚሰበስቡበት ወቅት፣ ያልታሰበ አደጋ የደረሰባቸውን ነው አሁን የምናስበው፤”
• “ከሰዎች ጋራ ነው እየኖርን ያለነው ብለው እያሰቡ ሳለ ለካስ ከአራዊት ጋራ ይኖሩ ነበር፤ ሳያስቡት፣ ተኩላዎች የበሏቸውን ነው አሁን የምናስበው፤”
• “ፈረንጆቹ አራዊትን አለማምደው ከእነርሱ ጋራ እንዲኖሩ ባደረጉበት ወቅት፣ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያውያንን፣ ኢትዮጵያውያትን እንደ በጎች በሏቸው፤ በቃ፣ ሌላ ቃላት አይኖረውም!”
• “እኛን ወደ አውሬነት የለወጠን ማን ነው? ሁሉም ይህን ጥያቄ ሊጠይቅ ይገባል፡፡ ክፉ፣ መጥፎ ነገር የዘራው ማን ነው? ምን ዐይነት ሰይጣን ነው? ሠራዊት ያለው መንግሥት ባለበት አገር ይህ ሲታይ ምንድን ነው?”
• “ነጠላ ጫማ የሌለው ያስከበራትንና የጠበቃትን አገር፣ ባለጫማ አስገደለን፤ ባለጫማ ገደለን፤ እግዚአብሔር አምላክ የሚጠብቀንን ይላክልን! አንድ ኀይል ከላይ ይላክልን!”
• “የአንዲት ሴት እንባ ነው ያን ሕዝብ ከ430 የባርነት ዘመን በኋላ ነፃ ያወጣው፤ አሁንም፣ ያችን ራሔልን ይላክልን! ጸሎታቸው የሚሰማውን ይላክልን!”
/ብፁዕ አቡነ ኤልያስ፤ የስዊድንና አካባቢው አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ/
***
ባለፉት ቀናት በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች፣ በሃይማኖታቸው ምክንያት በአክራሪዎች የግፍ ጥቃት ለተገደሉ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን፣ በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ፍትሐት ተደረገ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ትላንት ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት የተካሔደው ጸሎተ ፍትሐቱ፣ በብሔራዊ ደረጃ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተከናወነ ሲኾን፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት እና በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል፡፡
በሥነ ሥርዐቱ ላይ የስዊድንና አካባቢው አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ በእንባ እየታጠቡ በሰጡት፣ ብፁዓን አባቶችና ምእመናን በከፍተኛ ሐዘን በተከታተሉት ትምህርት፣ አገር እና መንግሥት አለን ብለው ዜግነታዊ ግዴታቸውን እየተወጡ የሚኖሩ ንጹሐን የተፈጸመባቸው የግፍ ግድያ፣ የሰማዕታትን ዘመን እንደሚያስታውስና የምንገኘውም በሰማዕትነት ዘመን እንደኾነ አስገንዝበዋል፡፡ “ሠራዊት ያለው መንግሥት ባለበት አገር ይህ ሲታይ ምንድን ነው?” በማለት፣ የጸጥታ አካላት አስከፊውን ጥቃት እያወቁና እየሰሙ ተገቢውን ጥበቃና ከለላ አለማድረጋቸውን ተችተዋል፡፡
የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት በአግባቡ የሚጠብቅ የሚታመን መንግሥት፣ እንዲሁም ጸሎቱ ተሰሚና ግዳጅ ፈጻሚ የኾነ አባት እንደሚያስፈልገን አመልክተዋል፤ “እግዚአብሔር አምላክ የሚጠብቀንን አንድ ኀይል ይላክልን፤ በእንባዋ ሕዝብን ከዘመናት ባርነት ነፃ ያወጣችውን ያችን ራሔልን ይላክልን፤” ያሉት ብፁዕነታቸው፣ በግፍ ለተገደሉት ስማቸው ለሚታወቁትም ገና ለማይታወቁትም፣ እግዚአብሔር ዕረፍተ ነፍስን እንዲሰጥ አማፅነዋል፡፡(የብፁዕነታቸው ትምህርት ከፊል ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል)
‡‡‡‡‡‡‡‡
… አባት ልጁን ምንህን ነው ብሎ ሳይጠይቀው፣ ልጅ አባቱን ሰላም ሳይል፤ እናት ለልጇ ያቀረበችውን ሳይበላላት፣ ልጅም እናቱን ደኅና ኹኚ ሳይላት ኹሉም የተገደሉትን፤ አገራችን ነው፤ ቤታችን ነው፤ ኢትዮጵያ ናት፤ መንግሥት አለ ብለው፣ ለመንግሥት ታክስ እየከፈሉ፣ ልጆቻቸውን እያሳደጉ፣ እያስተማሩ ባሉበት ወቅት፣ አዝመራቸውን በሚሰበስቡበት ወቅት፣ ያልታሰበ ድንገተኛ አደጋ የደረሰባቸውን ሙታን ነው አሁን የምናስበው፡፡
ከሰዎች ጋራ ነው እየኖርን ያለነው ብለው እያሰቡ ሳለ ለካስ ከአራዊት ጋራ ይኖሩ ነበር! “ተኩላዎች እንደ በጎች ሳያስቡ በሏቸው፤” ተብሎ የተጻፈውን ሳያስተውሉ፣ ሳያስቡት፣ ተኩላዎች የበሏቸውን ነው አሁን የምናስበው፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ፣ ከ1ሺሕ 700 ዘመን በፊት በግፍ የነበረውን እያሰበች ነው፡፡ እኛ ዘመነ ሰማዕታትን እያነበብን ስንኖር፣ ከ1ሺሕ 700 ዘመን በኋላ፣ ኢትዮጵያ ዘመነ ሰማዕታትን ኾነች፡፡ ዛሬ ዘመነ ሰማዕታትን ነው፡፡
ይህ የሚያስገርም ነው፤ ፈረንጆቹ አራዊትን አለማምደው ከእነርሱ ጋራ እንዲኖሩ ባደረጉበት ወቅት፣ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያውያንን፣ ኢትዮጵያውያትን እንደ በጎች በሏቸው፤ በቃ፣ ሌላ ቃላት አይኖረውም! ዘመነ ሰማዕታትስ የተለየ ነበር?
ኢትዮጵያ፣ እስላም ክርስቲያኑን በፍቅር በሰላም እንግዶችን እየተቀበለች የኖረች፣ የሰላም፥ የፍቅር፥ የአንድነት አገር ነበረች! እንዴት ነው? ለምን ተለወጠች? ለምንስ ይኼ ኾነ? ማን ነው በንጹሕ ስንዴ ላይ እንክርዳዱን የዘራበት? ማን ነው? እኛ ተኝተን ሳለን ነው? በድንገት ነው? ሳናስበው ይኾን? ይህን ችግር አስበነው፣ ጠብቀነው ነበርን? እኔ አይመስለኝም፡፡
አባቶቻችን፣ እናቶቻችን በየዋህነት ቤታቸውን ከፍተው፣ ኹሉንም አክብረው እንግዳ ተቀብለው የኖሩባት፣… ሆሜር ታላቁ ፈላስፋ፥ “ባሕሩን ተንተርሳ የተኛች” ያላትን ልዩ ሀገር ማን ነው የለወጣት?… እኛን ወደ አውሬነት የለወጠን ማን ነው? ሁሉም ይህን ጥያቄ ሊጠይቅ ይገባል፡፡ ክፉ፣ መጥፎ ነገር የዘራው ማን ነው? ነገራችኹ፥ እውነት እውነት፣ አዎ አዎ ይኹን ተብለናል፤ ከዚህ የወጣ የሰይጣን ነው ብሏል፤ ምን ዐይነት ሰይጣን ነው? ድሮ ቤተ ክርስቲያን በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብላ ታስወግደው ነበር፤ ዛሬ ይህን ሊያስወግድልን የሚችል ማን ነው? መንግሥት ባለበት አገር፣ ሠራዊት ያለው መንግሥት ባለበት አገር ይህ ሲታይ ምንድን ነው?
በዚህ ሰዓት እግዚአብሔርን የማመሰግንበት አንድ ነገር አለኝ፤ [ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት]ገሚሶቻችን በማዶ፣ ገሚሶቻችን በዚህ ኾነን ቢኾን ኖሮ፣ እናንተ ምን ትናገሩ ነበር? እኛስ ምን እንናገር ነበር? እንዴት ይኾን ነበር? በአንድነት፣ ስለ አገራችንና ስለ ቤተ ክርስቲያናችን እንድናለቅስ ስላደረገን አመሰግነዋለኹ፡፡
አሁንም፣ ነጠላ ጫማ የሌለው ያስከበራትንና የጠበቃትን አገር፣ ባለጫማ አስገደለን፤ ባለጫማ ገደለን፤ ወታደሩ እያየ ነውኮ የተገደሉት የተባለው፤ እግዚአብሔር አምላክ የሚጠብቀንን ይላክልን! አንድ ኀይል ከላይ ይላክልን! የአንዲት ሴት እንባ ነው ያን ሕዝብ ነፃ ያወጣው፤ ከ430 የባርነት ዘመን በኋላ ነፃ ያወጣው፤ አሁንም፣ ያችን ራሔልን ይላክልን! … አሁን እንደዚያ ዘመን፣ ጸሎታቸው የሚሰማውን ይላክልን! ኀይል የጌዴዎን ነው፤ ድል የእግዚአብሔር ነው!! ለኹሉም ልብ ይስጥልን!!
ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ሰላሙን፣ ፍቅሩን፣ አንድነቱን ይላክልን፤ በሰላም፣ በፍቅር፣ በአንድነት ይጠብቅልን፤ ሕዝቡን ከግድያ ይጠብቅልን፤ ዛሬ የምናስባቸው ብዙ ናቸው፤ ስማቸውን የምናውቃቸውንና የማናውቃቸውን በየስፍራው በየጥጋጥጉ የወደቁትን እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በመንግሥቱ ይቀበልልን፡፡
Filed in: Amharic