>
10:06 pm - Sunday August 7, 2022

ገዳዮች ተክሰው፣ ተገዳዮች ይረገማሉ! ይህ የወደቀ መንግስት አይነተኛ መገለጫ  ነው!!! (የሺሀሳብ አበራ)

ገዳዮች ተክሰው፣ ተገዳዮች ይረገማሉ! ይህ የወደቀ መንግስት አይነተኛ መገለጫ  ነው!!!
የሺሀሳብ አበራ
ስራዓት በአንድ ግለሰብ ፍትህ ማግኘት ላይ ብቻ አይመጣም፡፡ በእርግጥ አንድ ሂደት ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው መንግስታዊ ሽባነት ምክንያት ፍትህ ሩቅ ስለሆነ አሸናፊው እውነተኛ ነው፡፡ በሰኔ 16 ቀን 2010 ዓም ጌታቸው አሰፋ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሊያስገድሉ ቦንብ አስወረወሩ ብሎ ጠቅላይ አቃቢ ህግ በይፋ መግለጫ ሰጥቶ ነበር፡፡ ግን ጌታቸውን ከመያዝ ይልቅ ቱባ ቱባ ባለስልጣናት ጌታቸውን በክብር እየጠሩ  ያማክሩት ይዘዋል፡፡
 ከሰሞኑ የተነሳውን ግጭትም ለአንድ ግለሰብ የመስጠት አዝማሚያ አለ፡፡ ነገር ግን ግለሰቡ በቤተመንግስት አካባቢ  ሰዎች ተጠርቶ ይቅርታ ተጠይቆ አጃቢ እና እንክብካቤ እንዲጨመርለት ተደርጓል፡፡ ገና ተጨማሪ የሞራል ካሳ ሊሰጠው ይችላል፡፡
 ዋናው ለምን እንዲህ ሆነ የሚለው ጥያቄ ነው?!
1) ሀገሪቱ መንግስት አልባ ናት፡፡ የፍትህ፣የፀጥታ፣የሰላም፣የሴቶች እና ወጣቶች ሚኒስተር …ወዘተ ጉዳዮ ቢመለከታቸውም ባላየ አልፈውታል፡፡ ሴቶች ያላግባብ   ያሰሩ፣ጡት የቆረጡ፣የደፈሩ ዜጎች ባሉበት ሀገር የሴቶች ሚኒስትር መግለጫ እንኳን አያወጣም፡፡
2) ኢ- መንግስታዊ ተቋማት መንግስት ናቸው፡፡
መንግስት ሲዝል ኢ- መንግስታዊ ተቋም መፈጠሩ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ሶሪያ ልዮ ልዮ ፍላጎት ያላቸው ወደ 5 ኢ -መደበኛ መንግስቶች ሲኖሯት፣የጋዳፊዋ ሊቢያዋሞ 3 ኢመደበኛ መንግስታት አላት፡፡ በ1994 ሩዋንዳም በሁቱ ፖለቲከኞች የሚመራ ኢንተርሃሚዊ የሚባል የጦር ሀይል ነበራት፡፡ ይህ ኢ-መደበኛ መንግስት ነው፡፡ መንግስት ስራውን በአግባቡ  ባልሰራበት ጊዜ ኢ-መደበኛ አደረጃጅቶች ይፈጠሩና  ደካማው መንግስታዊ ቡድን  ሀሳቡን በኢ-መደበኛው አደረጃጅት ያስፈፅማል፡፡ የሰሞኑ ነውረኛ ክስተትም ድርጊቱ የተፈፀመው በኢ-መደበኛው ሀይል ቢሆንም በይዘቱ ግን መንግስታዊ ድጋፍ አለው፡፡ ድርጊቱ የኢ-መደበኛው ሲሆን፣ፍላጎቱ ግን የመንግስት ነው፡፡ ስለዚህ ፍትህ ሩቅ ነው፡፡ ትክክለኛ ፍትህ አይገኝም፡፡ የተጀመረው እስር እንኳን መብታቸውን ለማስከበር የወጡትን ይሆን ካልሆነ በስተቀር ገዳዮችን የመሆን ዕድሉ ለዜሮ የቀረበ ነው፡፡ ገዳዮች ተክሰው፣ተገዳዮች ይረገማሉ፡፡ ይህ በወደቀ መንግስት ውስጥ የሚኖር ባህሪ ነው፡፡
 ታዲያ ምን ይደረግ?”
 ለሀገራዊ ጉዳይ ቅርብ የሆነውን ህዝብ የሚመራው አዴፓ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁልቁል እደተጓዘ ነው፡፡ በድርጅታዊ ይዘቱ ከነ በረከቱ እና ከእነአቶ አለምነው ብአዴን ሁሉ የዛሬው ይደክማል፡፡ የእነ አቶ በረከቱ ብአዴን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ እስረኛ ሆኖ ከአማራ ጥቅም በተቃርኖ የቆመ  ፀረ አማራ ድርጅት ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ግን በድርጅታዊ ቁመናው ጠንካራ ነው፡፡ መጠንከሩ ግን ለአማራ አይጠቅምም ነበር፡፡ ምክንያቱም ከጅምሩ ብአዴን አማራ አይደለም፡፡
የዛሬው አዴፓ በድርጅታዊ ቅርፁ ከእነ አቶ በረከቱ ያነሰ እና የተልፈሰፈሰ ነው ፡፡ፖለቲካ አይተነትንም፡፡ ዓላማ የለውም፡፡ በሰሞኑ ከጅምላ ግድያ እስከ መፈንቀለ መንግስት በተሴረው ሴራ ጉዳይ እንኳን አልመከረም፡፡ አልተነተነም፡፡ የራሱን አቋም አልወሰደም፡፡ ከዚህ ትንታኔ አንፃር አዴፓ መንግስት ከመሆኑ ሌላ መኖሩ እና አለመኖሩ ለአማራ ህዝብ የሚኖረው ጥቅም ብዙ ልዮነት የለውም፡፡
 ..
አዴፓ ከብአዴን የሚለየው ውስን ግለሰቦች የአማራነት ስሜት አላቸው፡፡ አማራ የሚለው ቃል አንደበታቸውን አይሻክረውም፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በተናጠል ለአማራነት የቆሙ ቢሆኑም ግለሰብ እንጂ ስራዓት አልፈጠሩም፡፡ አዴፓ እንደ ስራዓት የአማራን  ጥቅም ማስከበር አይችልም፡፡
 ዛሬም አዴፓ ለመሆን ከአማራ ብሄርተኝነት እና ከአብን እሳቤ መራቅ፣ለአሸናፊ ለሚመስለው ማደር ህሌናዊ መስፈርቶች ናቸው፡፡ አብን አዴፓን መሞገት አለመቻሉ ለአዴፓ ስንፍና ችሮታል፡፡ አብን በብአዴን መስመር ተጉዞ  ብአዴን መምሰሉ ለአዴፓ ስንፍናን፣ለአብን መቀዛቀዝን  አስከትሏል፡፡
እና፡
1) አዴፓ ከኢህአዴግ  አጋሮች እና ግንባሮች ሁሉ የተሻለው ለአማራ አጋር ስለሆነ እንጂ አዴፓ እንዲስተካከል ግፊት ያስፈልጋል፡፡ አዴፓ ሲገፉት የሚጓዝ እንጅ በራሱ የሚጓዝ አይደለም፡፡ በተደራጀ እና በተናበበ መንገድ አዴፓን መወጠር ያስፈልጋል፡፡
2) የሲቪል ማህበራትን ማጠናከር(የአማራ ወጣቶች ማህበርን በሁሉም ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ማንቃት፣የአማራ ተማሪዎችን፣ሀኪሞችን፣መምህራን …ወዘተ አንቅቶ በየሳምንቱ በጋራ እየተወያዮ ወቅቱን የሚመጥን ተጨባጭ ስራ መስራት
 3)  ከደቦ ፍርድ እና ከመንጋነት ርቆ አካባቢን መጠበቅ፣ኬላዎችን ከፀጥታ ሀይላት ጋር ሆኖ መጠበቅ
4) ትምህርትቤቶች እና መስሪያ ቤቶችን አዘግቶ የአርሶአደሪን ምርት ማሰብሰብ፡፡ የአማራ ወጣቶች እንደ አማራ ልዮ ሃይሎች ሀላፊነት ወስደው ምርት ቢያሰበስቡ አርሶአደሩን በዚያው ማንቃት ይቻላል፡፡
5)  ከማህበራዊ ሚዲያ ጫጫታ ወጥቶ ውጭ ያለው እየደረሰ ያለውን ውድመት ለየዓለም አቀፉ ማህበረሰቡ ማድረስ፣በሀገር ውስጥ ያለው የተጨበጠ የመሬት ላይ ስራ መስራት ያስፈልጋል፡፡
አሁን ያለው ሁኔታ በተግባር በመሬት ስራ እንጂ በማህበራዊ ሚዲያ ጫጫታ እና በአንደበት አይመለስም፡፡ ጥሩ አንደበትማ  መንግስትም አለው፡፡ አንደበት መፍትሄ አይደለም፡፡
Filed in: Amharic