>

የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓለም አደባባዮች የሃፍረት ሸማ እንዲላበስ ተደርጓል። (የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት )

የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓለም አደባባዮች የሃፍረት ሸማ እንዲላበስ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት 
(ኢትዮ 360 ) የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓለም አደባባዮች የሃፍረት ሸማ እንዲላበስ ተደርጓል ሲል የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት አስታወቀ።
ሕብረቱ “በማራቶን ደጋግመን ያሸነፍነውን ያህል፣ ሰሞኑን በጭካኔ ሬከርድ ሰብረናል!” በሚል ርዕስ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ተከስቶ ከ80 በላይ የሚሆኑ ንጹሃን ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ የቀጠፈውን ክስተት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
ሕብረቱ ለኢትዮ 360 በላከው መግለጫ እንዳለው ኢትዮጵያ ሃገራችን ፈታኝ ወቅት ላይ ትገኛለች።
ሕወሃትን ለማውረድ ብዙ መስዋእትነት የተከፈለበት ለውጥም በመቀልበስ ላይ መሆኑ ሃሜት ሳይሆን ሃቅ ነው ብሏል ሕብረቱ በመግለጫው።
ጁሃር መሃመድ ጥበቃዬ ሊነሳ ነው ድረሱልኝ ብሎ በደረቅ ለሊት ለተከታዮቹ ያደረገው ጥሪ ንፁህና ሰላማዊ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን እንደበግ በገጀራና በቆርቆሮ እንዲታረዱ፣ ቤንዚን ተርከፍክፎ እንዲቃጠሉ፤ በድንጋይ እንደእባብ ተቀጥቅጠው እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል ይላል።
የጀዋር መሐመድ ተከታዮች የገደሏቸው በአብዛኛው “ነፍጠኛ” ከሚሉት የአማራ ወገን ቢሆኑም ይላል መግለጫው ከጋሞ፣ ከጉራጌ እና ከዶርዜ ማህበረሰብ፣ እንዲሁም ሙስሊምም ክርስቲያንም ይገኙበታል ሲል ያስቀምጣል።–ቀሳውስት ታርደዋል፣ ቤተክርስቲያንና መስጊድ፣ የመኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ተቋማት መቃጠላቸውም እንዲሁ።
ሕብረቱ የተከሰተው ጭካኔ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን የዓለምን ሕዝብ ድንጋጤ ላይ ጥሎት ከርሟል ብሏል።
ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሰላም የኖቤል ሽልማት ማሸነፍ አገራችን በዓለም ጋዜጦች በአድናቆት ሲዘገብላት እኛ ኢትዮያውያኖች በያለንበት አንገታችንን ቀና አድርገን የነበርነውን ያህል ሰሞኑን በተከሰተው ጭካኔ ደግሞ አንገታችንን እንድንደፋ ተደርገናል ሲል ይናገራል።
ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብም በቀየው በተከሰተው ኢሰብአዊ ድርጊት ከሌላው ወገኑ ጋር እንደተሸማቀቀና በእጅጉ እንዳዘነ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም ሲል ተናግሯል።
 አንድ መረሳት የሌበትና ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ቢኖር ይላል ንቅናቄው በመግለጫው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትናንት የልጆቹን ደም ገብሮ ሕወሃትን ያስወገደው የባሰ ዘመን ለማስተናገድ አይደለም።
ሌላው አሳዛኝና አሳፋሪ ክስተት ደግሞ ይላል ሕብረቱ የወገኖቻችን እልቂት ሳይቆምና እሬሳቸው ስይነሳ፣ የአንዳንድ ድርጅት መሪዎች ጀዋር መሐመድን በቪላው ውስጥ ተገኝተው እጅ ሲነሱትና ሲያባብሉት ማየት ነው።
ሕብረቱ አሁንም ቢሆን ይላል ሕዝብን በማበጣበጥ ሕግ የሚጥሱትን መንግሥት ፈጥኖ በመያዝ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ካላደረገ የዜጎቹን ክብርና እምነት ያጣል።- ሌሎች ሕግ እንዳያከብሩ ያበረታታል ሲል ገልጿል።
ሕዝብ ለመንግሥት ሃላፊነት የሰጠው ከሁሉም በላይ የሕግን የበላይነት እዲያስከብርለት ነው። ስለዚህ አጥፌዎች ያላቸው ጡንቻ ተፈርቶ ፍትህ መዘግየትና መጓደል የለባትም ሲልም ያስጠነቅቃል የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት ።
ስለሆነም በአሁኑ ሰዓት መንግሥት ጀዋር መሐመድንና ሕዝቡን የፈጁትን ተከታዮቹን ለቃቅሞ ለፍርድ ከማቅረብ ሌላ አማራጭ የለውም ብሏል መግለጫው።
 እንዲሁም በየጊዜው ከፋፋይ ዘር ተኮር መልዕክቶችን በማስተጋባት ሕዝቡን ለማናቆር በስፋት ቅስቀሳ የሚያደርጉትን አቶ በቀለ ገርባን፣ ሕዝቅኤል ጋቢሳን፣ ፀጋዬ አራርሳን፣ “ፕሮፌሰር” ገመቹን መንግሥት በሕግ አብሮ ተጣያቂ እንዲያደርጋቸው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት በመግለጫው አሳስቧል።
ሊሰመርበት የሚገባው ሕዝቡ በማንነቱ ምክንያት ካደገበት ቀዬው መፈናቀል አንገፍግፎታል፤ በየጊዜው መታረድ በቅቶታል።
በማንነቱ ምክንያት በቡራዩ፣ በናዝሬት፣ በአምቦ፣ በዶዶላ፣ በሰበታ በሲዳማ እና በሌሎችም የሃገሪቱ ክፍሎች የታረደው ህዝብ ዛሬ ላይ መንግሥት ይደርስልኛል በሚል እሳቤ እንደገና በዝምታ የሚታረድ አይደለም ይላል ሕብረቱ።
ሕዝቡ በሚመስለውና በእጁ ባለው እራሱን መከላከል ከጀመረ አሸናፊው በውል የማይለይና ማቆሚያ የሌለው እልቂት ሊከሰት ይችላል ሲል ሕብረቱ ስጋቱን ገልጿል።
ይህ ቃል ካልተጠበቀና ለፍርድ መቅረብ ያለባቸው ካልቀረቡ ሕዝቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ያለው እምነት በይበልጥ እየተሸረሸረ ከመሄዱም በላይ በወገንተኛነት እንዳይፈርጃቸው ሊያግደው የሚችል ምክንያት ሊኖር አይችልም።-ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ የሚመለከተው አካል አስቸኳይ የሚባለውን ርምጃ ወስደው ሃገሪቱን የማረጋጋት ሃላፊነት አለባቸው ብሏል።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት በመግለጫው ማጠቃለያ ለሞቱና ለተጎዱ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝቶ፣ ፍትህ ለታረዱ ወገኖቻችን ይሁን ሲል ጥሪውን አቅርቧል።
Filed in: Amharic