>
1:16 pm - Thursday December 8, 2022

ኦሮሞ ሆይ! ልጆችህን አድን! ነገን አድን! Oromoo ljoole Kee Olchii! Borru Kee Olchii! (እዩማ ሙሉ)

ኦሮሞ ሆይ! ልጆችህን አድን! ነገን አድን!!
Oromoo ljoole Kee Olchii! Borru Kee Olchii!
እዩማ ሙሉ
የፖለቲካችን ጦስ ከአዋቂው ይልቅ በሕጻናትና በወጣቶች ላይ እያደረሰ ያለው ተጽዕኖና በነገው ተስፋቸው ላይ የደቀነው አደጋ ቀላል አይደለም። ስንቶቻችን በማወቅም ይሆን ባለማወቅ በቃልም ይሁን በድርጊት መጥፎ አርአያና ሳንካ እየሆንን ይሆን?
እንደሀገር  በልጆችና  በወጣቶች ላይ እያደረስን ያለውን ጉዳት በፍጥነት ማረም ካልቻልን፣ የዘራነውን ክፉ ዘር እየነቀልን ካልሄድን፣ ፍርሃቶቻቸውን አስወግደን ተስፋቸውን ማለምለም ካልቻልንና ከተያዝንበት አዚም በፍጥነት ካልወጣን ነገችን ያስፈራል።  የዚህ አደጋ መነሻ በአመዛኙ በግልብ ስሜት የሚነዳ በግለኝነትና ነገን አሻግሮ ማየት ያልቻለ ‘ፖለቲካችን’ ነው። የወደፊቱንና የሕልውናችንን ምስሶ እያፈረስ የሚሄድ ሆኗል- ፖለቲካችን!
ምንም እንኳን እንደማሕበረስብ አደጋውና ኪሳራው በሁላችንም ላይ  ያንዣበበ ቢሆንም እንደ ኦሮሞ ሕዝብ ብዙ ዋጋ እየከፈለና የሚከፈል ሕዝብ ያለ አይመስለኝም።
ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ዘመናት ያስቆጠረ የጥላቻ ዘር በወጣቱ ላይ በመዘራቱ ነው። እነዚህ ጥቂት ግን ብዙ ድምጽ ያላቸው ወገኖች አሁንም በተደራጀ ሁኔታ የጥፋት አጀንዳቸውን በግልጽ እያስኬዱት ነው።
እነዚህ እድሜ ያላሰከናቸው፣ ትምህርት ያልቀየራቸው፣
ይሉኝታ የማያወቁ፣ ሳይመረጡ ራሳቸውን በሕዝብ ላይ የሾሙ  ወኪልን ነን ባዮች ልጆች በጥላቻ እንዲሞሉ፣ ሌላውን ሕዝብ እንዲጠራጠሩ፣ የገዛ ሀገራቸውን እንዲክዱ፣ ስርዐተ አልበኛ እንዲሆኑ፣ የተሸናፊነትና የተጠቂነት ስሜት እንዲያድርባቸው ዘወተር የሚሰብኩት እነዚሁ ፖለቲከኞችና አክቲቪስት ነን ባዮች ናቸው።
ዛሬ ዛሬ ይህን አጥፊ ፖለቲካ ለሰዉ ቤቱ ድረስ በሚዲያዎቻችና ወጣቶቹ በያዟቸው ተንቀሳቃሽ ስልኮች እየጋቱት ነው።
እስቲ ሐሜት አንዳይመስል ጥቂት ተጨባጭ ምሳሌዎች ልጥቀስ፦ ቋንቋችን ያላደገው ከብሔርህ ውጪ ስለተጋባህ ነው እያሉ በተዘዋወሪ ከሌላው ጋር እንዳይጋባ የሚመክሩ፣ ተማሪን በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት F በማምጣቱ እንኳን እግዜር ገላገል የሚሉ፣ ባንዲራን የአማርኛን ፈደል እንዲፈቀፍቅ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ሰዎች፣ ግለሰቦች ክልልህ  እንዳይገባ እያሉ ወጣቶችን ወደፍጹም ስርአተአልበኝነት የሚነዱት በቅርብም በሩቅም የተቀመጡት አክቲቪስቶች ናቸው።
ከሁሉ የከፋው ኦሮሞ በኢትዮጵያውያኑ ሁሉ የተጠላና ሁሉም የርሱ  ጠላቱ እንደሆነ አድርገው የሚያቀርቡት  ዘመቻ ነው። በነርሱ ፍረጃ ‘ሚዲያው፣ ስነጥበቡ(ስነጹሑፉ፣ ፊልሙ ቲያትሩ…) አርቲስቱ፣ ታዋቂ ሰው፣ ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲው ወዘተ ወዘተ  ሁሉ ጸረ ኦሮሞ ነው። ይህ የጅምላ ፍረጃ አጅግ አደገኛ ነው። እንደዚህ አይነት ሠላማዊ ትግል በምድር ላይ የለም።  እውን ኢትዮጵያ የኦሮሞ ጠላት ናትን? የሴረኞችን እንቅስቃሴ መቃወም ‘ጸረ ኦሮሞ’ ያስብላልን? ለሕሊና ፍርድ እተወዋለሁ።
ለማንኛውም የአጥፊዎቹ ዋነኛ እስትራቴጂ ኦሮሞን በተለይ ወጣቱን ከሌላ ሕዝብ ጋር ያለው መስተጋብር በመበጠስ በሕዝቦች መካከል የልዩነት ግንብ መገንባት ነው።
ይህም መሰሪ አጀንዳ ፍሬ እያፈራ መሆኑ የማይታበል ነው።
በሰላማዊ መንገድ ለመንግስት ጥያቄን በማቅረብ የሚታወቁት ወጣቶች የተወሰኑት በጥላቻ ተመርዘው በጥቅምና በሴራ ተጠልፈው  ለመናገር የሚቀፉ፣ ፍጹም ኢሰበአዊ ወንጀሎችን አብሮ በሚኖር ንጹሓን ላይ እየፈጸሙ የኦሮሞንም ሆነ ሰላማዊወን ቄሮን ስም እያጠለሹት ከሌላው ሕዝብ እያጋጩትና የኃላ ኃላ ኦሮሞ እርስ በእርስ እንዲጋጭ ከጀርባ እያሴሩ ነው።  ታላቁ ሕዝብ ሆይ! የወጣቶች ሕይወት አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። የት ይደርሳሉ ያልካቸው ልጆችህ ከትምህርትም ከሥራ ርቀው ሰላማዊ ሰልፈኛና ጎዳና ለጎዳና ድንጋይ ወርዋሪ ሆነው ቀርተዋል። ምናልባት አውቀዋለሁ የምትለውና  መልካም ስብእና ያሳደከው ልጅህ ደንገት ተነስቶ አውሬ ቢሆንብህ አትጠራጠር ምክንያቱ የነኚ ሰዎች አጥፊ ፖለቲካ ነው።
እናማ በአጭሩ፦ ኦሮሞ ሆይ ልጆችህን ተዘርፈሃል፤ ተነጥቀሃል። በልጆችህ የደረሰውን ኪሳራ ለማወራረድ በትንሹ 50 አመታት ሁሉ ሊወስድብህ ይችላል።
ታላቁ ሕዝብ ሆይ! ልጅህን ከራሱ፣ ከሌላው ሕዝብና ከሀገሩ ጋር አስታርቀው። ተሰፋውን አለምልም።  ከገባበት ወጥመድ ታደገው። ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ለዘመናት አብሮ በሠላምና በፍቅር የመኖር አኩሪ ታሪክህን ንገረው።  ወደ ሠላማዊና ወደ ተረጋጋ ኑሮ መልሰው። ከየትኛውም አጥፊ ሕብረት አላቀው። ልጆህን አድን!! ነገን አድን!! የተጋረጠብህን ፈተና በድል ተወጥተህ  የጀግነነት ታሪክ እንደምታስመዘግብ ተስፋ አደርጋለሁ። መልካሙን እመኛለሁ!! Gaarii Nan Hawwa!
ከታላቁ የኦሮሞ ሕዝብ ጎን እቆማለሁ!!!
Uummata Saba Guddaa! Bira Nan dhaabaadha!!
Filed in: Amharic