>
12:26 am - Thursday December 1, 2022

ዐብይና ዳኛቸው (መስፍን አረጋ) 

ዐብይና ዳኛቸው

 መስፍን አረጋ 

 

ዲባቶ (ዶክተር) ዳኛቸው አሰፋ ‹‹ኒኮሎ ማኪያቬሊ፣ ሊጋባ በየነና ዐብይ አህመድ›› በሚል ርዕስ በቅርቡ ባደረገው ንግግር ለዐብይ አህመድ ማኪያቬላው ምክር ለግሶታል፡፡  የምክሩ ዋና ይዘት ደግሞ ዐብይ አህመድ የኦሮሞ ሕዝብ ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛለት ከፈለገ፣ ስልጣን ላይ ያወጣሁህ እኔን ስለሆንኩ፣ ከፈለኩ በፈለኩ ጊዜ አወርድሃለሁ እያለ የሚታበይበትን ትዕቢተኛውን ጃዋር ሙሐመድን የፊጥኝ አስሮ፣ ባባገዳወች ፊት አጋድሞ፣ ምንትሴውን ገልቦ፣ ሙልጭ አድርጎ እንዲገርፈው ነው፡፡  

 

እንኳን ሰውንና እንስሳን መከርበጅ (torture) በጽኑ ሊወገዝ የሚገባው አረመኔያዊ ድርጊት በመሆኑ፣ የዳኛቸው ምክር በጥሬ ትርጉሙ ባይደገፍም፣ የምክሩ ፍሬ ሐሳብ አግባብነት ግን አያከራክርም፡፡  አያሌ ጦቢያውያንን በቆንጨራ የሚያስከትፈው ጃዋር ሙሐመድ (ጃሙ)፣ አርባ መገረፍ ቢያንሰው እንጅ አይበዛበትም፡፡  

 

ችግሩ ግን የዳኛቸው ምክር በተሳሳተ ምንሳብ (መነሻ ሐሳብ፣ premise) ላይ የተመነሰበ ምክር መሆኑ ነው፡፡  ስህተቱ ደግሞ ዐብይ አህመድን የጦቢያ ብሔርተኛ፣ ጃዋር ሙሐመድን ደግሞ የኦሮሞ ጽንፈኛ አድርጎ መመልከቱ ነው፡፡  ዐብይ አህመድንና ጃዋር ሙሐመድን የዓላማ ተቃራኒ አድርጎ የመመልከት አባዜ ደግሞ የዳኛቸው ብቻ ሳይሆን የአያሌ ጉምቱ ጦቢያውያን አባዜ መሆኑን ‹‹ዐብይና ጃዋር›› በሚል ርዕስ በቅርቡ በጦመርኩት ጦማር ላይ በስፋት አብራርቸዋለሁ፡፡ 

 

ዐብይ አህመድና ጃዋር ሙሐመድ ሁለቱም አስተሳሰባቸውን አለቅጥ በተጋነነ የኦሮሞ ቁጥርና ታሪክ ላይ የመሠረቱ ጽንፈኛ ኦነጋውያን ናቸው፡፡  በመሆናቸውም በዓላማ አንድ ናቸው፡፡ ዓላማቸው ደግሞ የኦሮሞን የበላይነት በጦቢያውያን ላይ ብቻ ሳይሆን በምሥራቅ አፍሪቃውያን ላይ መጫን ነው፡፡  የጽንፈኛ ዓላማቸው ዋና ተገዳዳሪ ደግሞ የአማራ ሕዝብ እንደሆነ ሁለቱም በደንብ ስለሚያውቁ፣ ወደ መዳረሻ ግባቸው የሚያመሩት እየተናበቡ ነው፡፡ 

 

የዐብይ አህመድ ዋና ኦነጋዊ ሚና ጦቢያውያንን (በተለይም ደግሞ አማሮችን) በቅቤ አፉ እየቀባባ በማዋዛት፣ ኦነጋዊ አላማውን ለማስፈጸም የሚያደርጋቸው ፀረጦቢያ ድርጊቶች፣  ፀረጦቢያ ሁነው እንዳይታዩዋቸም ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ የዐብይ አህመድ ዋና አጋዥ ጃወር ሙሐመድ ነው፡፡ 

 

ጃዋር ሙሐመድ ጦቢያውያንን የሚያስደነግጥ ጽንፈኛ ፍላጎቱን በግልጽ በመናገር ፊታችንን ሙሉ በሙሉ ወደሱ እንድናዞር ሲያደርገን፣ ዐብይ አህመድ ደግሞ ጃዋር ከገለጸው ጽንፈኛ ፍላጎት ያነሰ ፅንፈኛ የሆነውን ኦነጋዊ ድርጊቱን ያለ ምንም ተገዳዳሪ ያከናውናል፡፡  በመቀጠል ደግሞ ጃዋር ሙሐመድ የበለጠ ጽንፈኛ የሆነውን ኦነጋዊ ፍላጎቱን በይፋ ይለፍፍና አሁንም እንደገና ፊታችንን ሙሉ በሙሉ ወደሱ ስናዞር፣ ዐብይ አህመድ ደግሞ በፊት ያስደነገጠንን የጃዋርን ጽንፈኛ ፍላጎት ያለ ምንም ተገዳዳሪ ይተገብራል፡፡ በዚህ ዓይነት ጃዋር ሙሐመድ በንግግር እየቀደመ፣ ዐብይ አህመድ በተግባር እየተከተለ ወደ ኦነጋዊ መዳረሻቸው እየተናበቡ ያመራሉ፡፡  

 

ማናቸውም መሪ መጣር ያለበት በግዴታ ለመከበር እንጅ በውዴታ ለመፈቀር እንዳልሆነ ማኪያቬሊ አበክሮ ይመክራል፡፡  ዐብይ አህመድ ደግሞ ሲያስፈልገው ማረመንን በደንብ እንደሚያቅበት በነ ዲባቶ ዐምባቸው ላይ በፈጸመው የባሕርዳር አረመኔያዊ ጭፍጨፋው በግልጽ አስመስክሯል፡፡  ጃሙን ግን ሊያረምንበት ቀርቶ ዝንቡ እሽ እንዳይባልበት አለቅጥ በመስጋት ከፍተኛ በጀት በጅቶ 24/7 በጽኑ ያስጠብቀዋል፡፡ ዐብይ አህመድ ያለ ምንም ተገዳዳሪ ኦነጋዊ ግቡን መምታት የሚችለው በጃሙ ጥላ ሥር እስከተሸሸገ ድረስ ብቻ ነው፡፡ 

 

ጃዋር ሙሐመድ ከተወገደ የዐብይ አህመድ የበግ ለምድ ይገፈፍና ተኩላነቱ ገሃድ ይወጣል፡፡  የዐብይ አህመድ ተኩላነት ገሃድ ወጣ ማለት ደግሞ፣ ጦቢያውያንን በሽንገላ እያደነዘዙ በኦነግ ጅብ በማስበላት በጦቢያ መቃብር ላይ የኦሮሚያን አጼጌ (empire) የመመሥረቱ ሂደት ባጭር ተቀጨ ማለት ነው፡፡  የነቃን አንበሳ ጅብ አይበላውም፡፡  

 

ኒኮሎ ማኪያቬሊ ላንድ መሪ ከሚመክራቸው ዐበይት ምክሮች ውስጥ አንዱና ዋናው ካድርባይ አማካሪወች እንዲጠነቀቅ ነው፡፡  ዳኛቸው ደግሞ ዐብይን የሚመክረው ኤርምያስ ለገሰን ሳይሆን ሲሳይ አጌናን እንዲሰማ ነው፡፡ ሲሳይ አጌና እውነታውን የሚያድበሰብስ ዋሽቶአደር ሲሆን፣ ኤርምያስ ለገሰ ደግሞ እውነታውን የሚገላልጥ ወንቶአደር ነው፡፡  የዋሽቶአደርን ምክር የሚመርጥ ግለሰብ ደግሞ እሱ ራሱ ዋሽቶአደር የመሆኑ እድል የሰፋ ነው፡፡ ያይጥ ምሰክሯ ድንቢጥ፡፡  

 

    መስፍን አረጋ 

                mesfin.arega@gmail.com    

Filed in: Amharic