>

ጥቃትን እንደ ግጭት ማቅረብ የግፉአንን ጩኸት መቀማት ነው!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ጥቃትን እንደ ግጭት ማቅረብ የግፉአንን ጩኸት መቀማት ነው!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች የተከሰተውን ጥቃት መነሻ በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከርመው የሰጡትን መግለጫ እና በ OMN ቴሌቪዥን በተከታታይ እየተሰራጩ ያሉትን ነገሮች የተበዳይን ጩኸት መንጠቅ፣ የድርጊቱን ትርክት ማንሻፈፍ እና ከወዲሁ ፍትሕን የማዳፈን እንቅስቃሴ ስለሆነ ይህን ጉዳይ በዝምታ ማለፍ አይገባም። በሕግ አምላክ ማለት ይገባል።
+ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ ላይ ደጋግመው ክስተቱን “ግጭት” እያሉ መግለጻቸው ፍጹም አግባብነት የሌለው እና መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር የሚጣረስ ለመሆኑ ከበቂ በላይ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል። በአንዳን አካባቢዎች ሰዎች እራሳቸውን ለመከላከል ሲሉ በቡድን ተንቀሳቅሰው ለጥቃት የመጣባቸውን የተደራጀ እና ሜጫ እና ዱላ ይዞ ይንቀሳቀስ ከነበረውን ቡድን ጋር ተጋጭተዋል። ከዚያ ውጭ ግን በአብዛኛዎቹ ሥፍራዎች የተከሰተው ነገር የጅዋርን ጥሪ ሰምተው የተንቀሳቀሱ ወጣቶች በሰነዘሩት ጥቃት የደረሰ ጉዳት ነው። በዚህ ጥቃት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የተለያዩ ብሔሮች ተወላጅ የሆኑ ሰዎች የጥቃቱ ሰለባዎች ሆነዋል። ክስተቱን በሁለት ተደራጅተው ፍልሚያ በገጠሙ ቡድኖች መካከል የተደረገ ግጭት አድርጎ መግለጽ ግን እውነታውን ማዛባት ብቻ ሳይሆን የፍትህ ሂደቱንም ከወዲሁ እንዲዛባ ትርክቱን የማስተካከል ተግባር ነው።
+ በቡራዩ እልቂት የተጎዱት ሰዎችን ጩኸት ለማፈን እነ ጃዋር ልክ ዛሬ እንዳደረጉት ሁሉ የጥቃት ሰለባዎች የነበሩትን የሕብረተሰብ ክፍሎች ለክ እንደ ተፋላሚ ኃይል በመቁጠር ድርጊቱን ከማውገዝ ይልቅ በእኛ በኩል ይህን ያህል ሰው ሞቷል በማለት መንግስት ከሚያውቀው መረጃ እና የሟቾች ቁጥር ውጭ የተዛባ መግለጫም በመስጠት ፖሊስን እና የመንግስት አካላትን በአደባባይ ሲያስፈራሩ ነበር። ጉዳዩም እንደተዳፈነ ቀረ። መንግስትም ፍትሕን ከማስከበር ይልቅ በሚዲያዎቹ ጉዳዩን በጋሙ ሽማግሌዎች እና በኦሮሞ አባገዳዎች እንደተፈታ አድርጎ በማሳየት በጠራራ ጸሀይ የተፈጸመ ግፍ ተድበስብሶ ቀርቷል። ጉዳዩም ገለልተኛ በሆነ አካል እስከ አሁን አልተጣራም። ለምን?
+ ይህንኑ ተከትሎም ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት እና ጃዋር መሃመድ ዋና የአመጹ ቀሰቃሽ ስለሆነ በሕግ ይጠየቅ የሚል ሰፊ እንቅስቃሴ መከሰቱን ተከትሎ እሱ በሚመራው ሚዲያ እየተላለፈ ያለው ዘገባ ችግሩን እጅግ የሚያባብስ፣ የዘር ጥላቻን የሚያንጸባርቅ፣ ሌሎች ግጭቶችን የሚጋብዝ እና በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ለበለጠ ስጋት እና ጥቃት እንዲዳረጉ እሳት የሚያቀጣጥሉ ናቸው። የዛሬውን የOMN የቀን አማርኛ ዜና መመልከት ብቻ በቂ ነው። ሚዲያው በተለያዩ ከተሞች እየዞረ አንዳንድ የኦሮሞ ተወላጆችን እያናገረ ለቅስቀሳ እና ጥላቻ አዘል ለሆኑ ንግግሮች ሙሉ የአየር ሰዓቱን ሰጥቶ የዜና ዘገባውን ጨርሶታል። ሚዲያው በብሮድካስቲን ኤጀንሲ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው ቢሆንም ማሳሰቢያውን ወደ ጎን በመተው ተመሳሳይ ቅስቀሳዎችን እያደረገ ነው።
+ በዚሁ ሚዲያም ከሁለት ቀን በፊት ጀነራል ከማል ገልቹ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር እና እሳቸው በጥላቻ በፈረጇቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ግልጽ የሆነ ዛቻ፣ ማስፈራሪያ እና ጥሪም ጭምር አስተላልፈዋል።
መንግስት እና ሕግ ባለበት አገር እንዲህ ያሉ ነገሮችን ችላ እያሉ ማለፍ ሌሎች እልቂቶችን ይጋብዛል። መንግስት አሁንም ሕግ እንዲያስከብር ሁላችንም ማሳሰብ ይኖርብናል። በተፈጸመው አሰቃቂ የጥቃት እርምጃ በቀጥተኛም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ እጃቸው ያለበት የጀዋር አይነት ሰዎች በሕግ ሊጠየቁ ይገባል።
ፍትሕ ለተገደሉ እና ጥቃት ለደረሰባቸው ሰዎች!
Filed in: Amharic