>
5:18 pm - Monday June 16, 8487

የዩኒቨርሲቲያችንን ወቅታዊ መረጃ በተመለከተ!! (ወልድያ ዪኒቨርሲቲ)

የዩኒቨርሲቲያችንን ወቅታዊ መረጃ በተመለከተ!!
ወልድያ ዪኒቨርሲቲ
በቅድሚያ ከትናንት ወዲያ ጥቅምት 29/2012 ዓ.ም ምሽት 5:00 ስዓት ላይ በወልድያ ዪኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ግጭቱ የሁለት ተማሪዎቻችንን ህይወት የቀጠፈና በሌሎች 13 ተማሪዎችቻን ላይም ቀላል የሚባል ጉዳት መድረሱን የህክምና ምርመራ ውጤታቸው ላይ መረዳት ተችሏል፡፡ በመሆኑም ድርጊቱ መላውን የዩኒቨርሲቲያችንን ማህበረሰብ መምህራንን፡ ሰራተኞቻችንና ተማሪዎቻችንን ከዛም አልፎ የአካባቢውን ማህበረሰብ ያሳዘነ ድርጊት በመሆኑ ክስተቱን እያወገዝን በደረሰው ጉዳት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን አንገልፃለን::
 የሟቾቹን ነፍስ ፈጣሪ እንዲምር ፡ጉዳት የደረሰባቸው የተማሪ ወላጆችና በተሰቦችም መፅናናቱን እንዲሠጣቸውና ህክምና በመከታተል ላይ ያሉ ተማሪዎችም በቶሎ እንዲያገግሙ እንመኛለን ፡፡በመቀጠል ከትናንት ወዲያም ሆነ ትናንት የነበረውንና አሁን ተቋሙ ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ መረጀዎችን ለመስጠት እንወዳለን ፡፡
ከትናንት ወዲያ ምሽት 5:00 ላይ ምክኒያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ በተማሪዎች መካከል ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ ግጭቱ እንደተፈጠረ ወዲያውኑ የሰሜን ወሎ ዞንና የከተማ አስተዳደሩ ፀጥታ አካላት እንዲሁም የክልሉ አድማ በታኝ በተጨማሪም ሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ ም/ሰብሳቢ አቶ ወልደትንሳኤ መኮንን ጨምሮ የዞን አመራሮችና የዩኒቨርሲቲው ተ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስረስ ንጉስ ችግሩ ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ ችግሩ እንዳይባባስ የመከላከል ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል ፡፡ ተጨማሪ የፀጥታ አካላት እንዲመጣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም የመወያየት ስራ ተሰርቷል ፡፡ የግጭቱን መስኤ ለማጣራትም የምርመራ ቡድን ተቋቁሟል ፡፡
በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው የዲኖች ስብስብ ያለበት ግብረ ሀይል አቋቁሙ ተማሪዎችን የማረጋጋትና ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎችን በመከታተል በወቅቱ ህክምና እንዲያገኙ የማስተባበር ስራ እየሰራ ነው ፡፡ በአሁኑ ስዓትም በወልድያ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን ጉዳቱ ከደረሰባቸው መካከል 11ተማሪዎች ዛሬ ከሆስፒታል ወጥተዋል ፡፡ ህይወታቸው ያለፋ ተማሪዎቻችን የቀበሌም ሆነ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ መሆናቸውን የሚገልፅ ምንም አይነት መረጃ በኪሳቸው ባለመገኘቱ እንዲሁም ህንፃ ቁጥሩንና የዶርም ቁጥሩን መለየት ባለመቻሉ የተማሪዎቹን ማንነት ለመለየት ጊዜ የወሰደ ቢሆንም የተቋቋመው ግብረ ሀይል ሌሎች ተማሪዎችን በማፈላለግ የመለየት ስራ ተሰርቷል ፡፡ የወልድያ ከተማ ነዋሪዎችም በሆስፒታሉ በመገኘት ጉዳት የደረሰባቸውን ተማሪዎች በመጠየቅና በማፅናናት፡ ህይታቸው ያለፉ ተማሪዎችን ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሸኘትና በግቢው ውስጥ ያሉ ተማሪዎችንም እያረጋጉ ይገኛል ፡፡
በትላንትናው ዕለት ጧት ላይ ቅሬታ የነበራቸው ተማሪዎች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ከዞኑ፡ከከተማ አስተዳደሩና ከዩኒቨርሲቲ ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂደዋል ፡፡ በውይይቱ የፀጥታ ሀይል እንዲገባ በጠየቁት መሠረትም ማምሻውን የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ ገብተዋል ፡፡ ትናንት ወዲያ ከተፈጠረው ክስተት ወጭ ትናንት ቀንም ሆነ ለሊት የተፈጠረ አንዳችም የፀጥታ ችግር አልተከሰተም፡፡
በአሁኑ ስዓት የግቢው የፀጥታ ሁኔታም አየተረጋጋ ይገኛል፡፡
አጠቃላይ ዩኒቨርሲቲው የነበረውን መረጃ በማሰባሰብ በትላንትናው እለት ከስዓት በፊት ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ ም/ሰብሳቢና በኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር በኩል ለተለያዩ ሚዲያዎች መረጃዎችን በስልክ የማሳወቅ ስራም እየተሰራ ነው ፡፡ በቀጣይም ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የምናሳውቅ ይሆናል ፡፡ ይሁን እንጅ በተለያዩ የመረጃ ማሰራጫ መንገዶች ስለ ዩኒቨርሲቲው እየተለቀቁ ያሉት መረጃዎች ከላይ ከተገለፁት በተቃራኒው መሆኑን ስንገነዘብ አንዳንድ ሚዲያዎች፡አክቲቪስቶችና ግለሰቦች ፍላጎታቸው ምን አንደሆነ የአደባባይ ሚሥጥር ነው ፡፡ በዩኒቨርሲቲው ያልተፈጠሩ የሀሰት ምስሎችንና ቁጥሮችን በማሰራጨት ለተጠመዳችሁ ሁሉ ልቦና ይስጣችሁ ፡፡
ለማንኛውም ለተማሪዎቻችን፡ ለተማሪ ወላጆች፡ የአካባቢው ማህበረሰብ የተፈጠረው ሁኔታና መረጃ ይሄው ነው ፡፡ መረጃው የደረሳችሁ የማህበራዊ ሚዲያ ተከታታዮቻችን ይሄንን አውነታ ለሌሎች በማስተላለፍ አንድትተባበሩን በአክብሮት እንጠይቃለን ፡፡ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ተሳታፊና ተባባሪዎች ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ 13 ተማሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው ፡፡ በአሁኑ ስዓትም የወልድያ ከተማ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ከተማሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው ፡፡ በድጋሜ ህይወታቸው ያለፋ ተማሪዎቻችንን ነፍስ ይማር ፡ ቤተሰቦቻቸውንም ያፅናናልን ፡ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎችም በቶሎ እንዲያገግሙ አንመኛለን ፡፡
ህዳር 1 /2012 ዓ.ም
ወልድያ ዩኒቨርሲቲ
Filed in: Amharic