>

አዲስ አበቤ የዶዶላን ህዝብ ጩህት ስማ ነግ በእኔ በል!!! (ያሬድ ጥበቡ)

አዲስ አበቤ የዶዶላን ህዝብ ጩህት ስማ ነግ በእኔ በል!!!
ያሬድ ጥበቡ
 
* ወንድሞቻችን ተቆራርጠው ተገለዋል!
* ሀብት ንብረታችን ወድሟል ተቃጥሏል!
* አንድም የመንግስት አካል መጥቶ አላየንም!
 
በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያንና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የዶዶላ ን ህዝብ ለቅሶ ማድመጥና ነግ በእነፀ ማለት አለባቸው። ያልነቃና ያልተደራጀ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እጣው እንደ ዶዶላ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል። ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይና አስተዳደራቸው ለዚህ ግፍ ቋሚ መእትሄ እስኪደረግለት ድረስ በኦሮሚያ ክልል ባሉ ከተሞችን የገጠር ቀበሌዎች፣ ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን በርከት ብለው በሚገኙባቸው ቦታዎች ሁሉ፣ ከኢትዮጵያውያኑ አብራክ የተመለመሉ የፖሊስ ሃይሎች እንዲቋቋሙ መፍቀድ፣ ማሰልጠንና ማስታጠቅ ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባው ጉዳይ ነው። ህዝቡም መንግስት መጥቶ ያድነኛል ብሎ ከመዘናጋት ራሱን ሊያስጥሉት የሚችሉትን አደረጃጀቶች መጠቀም እንዳለበት ከዶዶላ መማር ይኖርበታል። የዶዶላ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው የሚገኙት ኢትዮጵያውያን እንደተናገሩት እስካሁንም የክልሉም ሆነ የወረዳና ዞን አስተዳደሮች ያልደረሱላቸው ከመሆኑም በላይ፣ ፖሊስ የወንጀሉ ተባባሪ ሆኖ የተገኘባቸው አጋጣሚዎች የተብዛዙ በመሆናቸው፣ የአካበቢው አስተዳደርና የፖሊስ ሃይል በአፋጣኝ መለወጥ እንዳለበት የሚያስረዳ ነው። ሺመልስ አብዲሳ ተፈናቃዮችን ሄዶ ባለማፅናናቱና ለችግራቸውም ባለመድረሱ ከክልል አመራርነቱ መነሳት ይኖርበታል። የክልሉ የፖሊስ መዋቅር በፅንፈኞች እንዲጠለፍ በመፍቀዱ ወይም ባለመቆጣጠሩ ሺመልስ አብዲሳ ከሥልጣኑ መልቀቅ ይኖርበታል። ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የኦሮሚያ ፖሊስን በፅንፈኞች መሰረግ አደጋ ወደፊት የሚያስከትለውን ጥፋት በመረዳት፣ ተቋሙ ውስጥ የማጥራት እርምጃዎች እንዲወሰዱ፣ የኦሮሚያ ፖሊስና ልዩ ሃይል ከአዲስ አበባ እንዲወጣ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ በየወረዳዉ ከሚኖሩ የአዲስ አበባ ዜጎች የተውጣጣና የተመለመለ ሆኖ በአዲስ እንዲዋቀር ማድረግ አለባቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ለማድረግ ዳተኛ ሆነው የኦሮሞ አክራሪ ብሄርተኞች ለሚያደርሱት ጥፋትና ወንጀል ጠቅላይ ሚኒስትሩንና አስተዳደራቸውን ተጠያቂ እንደምናደርግ ማወቅ አለባቸው። የሚኒስቴሮች ካቢኔ አባላትም ተገቢውን አመራር ባለመስጠታቸው  በታሪክ ተወቃሽ ከመሆን በላይ በህግ የሚያስጠይቃቸው መሆኑን ሊያውቁ ይገባል። ወይ ተገቢውን አመራር መስጠት ነው፣ አለበለዚያ ሥራቸውን በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቅ ይኖርባቸዋል።

https://youtu.be/TJxdqZ3Zd68

Filed in: Amharic