>

በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ እየደረሰ ስላለው ጥቃት ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ:-

በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ እየደረሰ ስላለው ጥቃት ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ:-
****
የኢትዮጵያ ህዝብ ለፍትህ፣ ለእኩልነትና ለአንድነት ያደረገው መራራ ትግል ተቋማዊ ለውጥን በተሳካ ሁናቴ ማምጣት ባለመቻሉና “የለውጡ መሪዎች” ኃላፊነት በማይሰማቸው አካላት ተጽዕኖ ስር በመውደቃቸው ምክንያት የለውጥ ተስፋው ውጤት አልባ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ያ ሁሉ ዋጋ ተከፍሎም ጭምር ዛሬም ጅምላ ጭፍጨፋ፣ ዘር ለይቶ ማጥቃት፣ መንግስታዊ ሽብርተኝነት እና ሥርዓታዊ መድሎ አልቀረም፤ ይልቁንም ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ በተለይም በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰው ጥቃት፣ ማሳደድና ሁለንተናዊ ጫና እጅጉን አሳሳቢ ሆኗል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን በተመለከተ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ችግሮቹ የሚረግቡበትን መንገድ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጅ አንዳንድ የፖለቲካ፣ የጸጥታ፣ የሀሳብ (opinion) እና የባህል መሪዎች በአማራ ህዝብ ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ እንዲደረግ በግልጽና በአደባባይ በማወጃቸው ጉዳዩን ከዛሬ ይልቅ ለነገ ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡
ከሳምንታት በፊት የተፈጸመ ማንነትን መሰረት ያደረገ ነውረኛ ጥፋት በወጉ እልባት ሳያገኝ፣ ግጭቱን የቀሰቀሱት፣ ያስተባበሩትና በድርጊቱ የተሳተፉ አካላት በአግባቡ ለህግ ባልቀረቡበት ሁኔታ አሁን ደግሞ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የደረሰውን የተማሪዎች ግድያ ሰበብ በማድረግ አንዳንድ ሚዲያዎችና ግለሰቦች ባራገቡትና ባደረጉት ጥሪ መሰረት በኦሮሞ ክልል በሚገኙ የአማራና ሌሎች ብሔር የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ ታፍኖ መሰወርና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ይገኛል፡፡ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተው ድርጊት አስነዋሪ በመሆኑ የአካባቢው ህዝብ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ኃላፊነት ያላቸው አካላት ሁሉ በግልጽ ያወገዙት ጉዳይ ነው፡፡  የግጭቱን መነሻ ምክንያት በጥልቀት መርምሮ ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ ይገባል፡፡
ይሁን እንጅ ይህንን በኳስ ድጋፍ መነሻነት ተከስቶ የነበረን ግጭት የብሔር መልክ ያለው ለማስመሰልና ከልክ በላይ እንዲራገብ የተደረገበት መንገድ ጉዳዩ ከፍትህ ያለፈ ነገር እንዳለው በግልፅ ያመላክታል፡፡ ወልድያ ዩኒቨርሲቲ የተፈጠረውን ድርጊት ሲያራግቡ የነበሩ አካላት ሁሉ (ድርጊቱ የሚወገዝ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ) የአማራና የሌሎች ብሔር ተማሪዎች ሞት በስፋት በቀጠለበት ወቅት ዝምታን መምረጣቸው ሀቀኛ የፍትህ ወገንተኞች አለመሆናቸውን ያሳያል::
በአሁኑ ሰአትም በኦሮሞ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በአማራ ተማሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው መጠነ ሰፊ ጥቃት እንደቀጠለ ነው::
ስለሆነም፡-
1ኛ) መንግስት አሁን ጥቃት እየተፈጸመባቸው ባሉና በሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የጸጥታና የደህንነት መዋቅሩን በፍጥነት በማሰማራት ጉዳዩን በቁጥጥር ሥር በማዋል ተማሪዎቹን ከጥቃት እንዲከላከል እና ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ መንግስታዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን፡፡
2ኛ) በወልድያ፣ በደንቢዶሎ፣ በመደወላቡ፣ በአለማያ፣ በጅማና በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በደረሰው የተማሪዎች ግድያና የአካል ጉዳት ጉዳዩን በፈጸሙ፣ በሀሳብ በተባበሩ፣ የፕሮፖጋንዳ ሥራ በሠሩና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ አካላት ላይ አስተማሪ የሆነ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ወስዶ ለህዝቡ እንዲገልጽ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
3ኛ) መንግስታዊ ሥርዓትንና ሕግን አምነው ለትምህትር ሄደው ውድ ህይወታቸውን ላጡ ተማሪዎች መንግሥት ለቤተሰቦቻቸው ይቅርታ እንዲጠይቅ፣ ካሳ እንዲከፍል እና የሌሎቹንም
ተማሪዎች ደህንነት እንዲያረጋግጥ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
4ኛ) በኢትዮጵያ ውስጥ ከሕጋዊ ሥርዓት፣ ከእኩልነት፣ ከፍትሕና ከዴሞክራሲ ውጭ ያለው አማራጭ ሁሉ የጋራ ጥፋት የሚያመጣ እንደሆነ እና ከሚነደው እሳት ማንም መትረፍ እንደማይችል ሁሉም ኃይሎች በአግባቡ እንዲገነዘቡና ከዚህ አንፃር አፍራሽ ሚና የሚጫወቱ አካላት በድጋሚ ቆም ብለው እንዲያስቡ፣ ከጥፋት መንገዳቸውም እንዲመለሱ እናሳስባለን::
ህዳር 4 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ: ሸዋ
አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፣ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
Filed in: Amharic