>
9:59 am - Wednesday November 30, 2022

የዳንኤል ክብረት ኢወቅታዊ እውነታ (መስፍን አረጋ) 

የዳንኤል ክብረት ኢወቅታዊ እውነታ

 

መስፍን አረጋ 

 

ይህችን አጭር ጽሑፍ ለመጻፍ የተነሳሳሁት ሙሃዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት ‹‹ከዲሞክራሲ በፊት ፍትህ›› በሚል ርዕስ ያደረገውን ግሩም ንግግር ካዳመጥኩ በኋላ ነው፡፡  ዳንኤል በትክክል እንዳስቀመጠው የጦቢያ አንገብጋቢ ችግር የዲሞክራሲ እጦት ሳይሆን የጦቢያ የፍትሕ እመቤት (lady justice) በብሔር በሽታ መታወር ነው፡፡  ዳንኤል ለመናገር ያልፈለገው ወይም ደግሞ የፈራው ግን የፍትሕ እመቤታችንን ያሳወራት የየትኛው ብሔር በሽታ መሆኑን ነው፡፡  ቢፈራም ደግሞ አይፈረድበትም፡፡ ራሱን ዳኛ አድርጎ ልጁን ቀማኛ ያደረገው ማነው? የኦነጉ ጌታቸው አሰፋ (ብርሃኑ ፀጋየ) ዐቃቤ ሕግ በሆነበት አገር አቤት የሚባለው ለማን ነው?

የዳንኤል ሐሳብ ምንም የማይነቀስለት እንከን የለሽ እውነታ ነው፡፡  ችግሩ ግን ወቅቱን የጠበቀ እውነታ አለመሆኑ (ኢወቅታዊ እውነታ መሆኑ) ነው፡፡  ማናቸውም ነገር እሴት የሚኖረው በተገቢው መቸት (መቸና የት) ላይ ሲመቸት ብቻ ነው፡፡  ጥድ አለቦታው ብሳና ይሆናል፡፡ የዳንኤል ሐሳብ ላገራችን ችግር ዘላቅ መፍትሔ ቢጠቁምም፣ አንድ ሐሙስ ለቀራት አገራችን ግን ነፍስ አድን አይደለም፡፡

አንበስና ሌንጮ የሚባሉ ሁለት ሰወች አሉ እንበል፡፡  ሌንጮ መቸም የማላገኘው ምቹ አጋጣሚ ተፈጠረለኝ ብሎ አንበስንና የአንበስን ዘር ማንዘሮች በሜንጫ በመቆራረጥ፣ የተረፉትን ጥቂቶቹን ደግሞ በሞጋሳና በጉዲፈቻ የሱ የራሱ በማድረግ የአንበስን ቴሳ (ድራሽ) ለማጥፋት ቆርጦ ተነሳ እንበል፡፡  በዚህ ወሳኝ ሰዓት ላይ አንበስ መጨነቅ ያለበት ራሱንና ወገኖቹን ከጥፋት ስለማዳን ብቻና ብቻ ነው፡፡ ቀጥሎ መጨነቅ ያለበት ደግሞ ለሌንጮ የተፈጠረለት ምቹ የጥፋት አጋጣሚ ዳግመኛ እንዳይፈጠር ስለሚያረጋግጥበት መንገድ ነው፡፡ ከዚህ እፎይታ በኋላ ነው አንበስ ስለ ፍትሕና ርትዕ በተረጋጋ መንፈስ እያሰበ ሌንጮንም እንዲያሰብ ለማድረግ የሚሞክረው፡፡

 

  • እኔን፣ የእኔን ዘርና የእኔ ደጋፊ የምትላቸውን አልኦሮሞ (ኦሮሞ ያልሆኑ፣ non-oromo) ጦቢያዊ ወገኖቸን ለማጥፋት የሚያነሳሳህስ ምን፣ ማንና ለምንድን ነው?   ባዕድ የሚያነሳሳህ ከሆነ፣ የሚያነሳሳህ እኔን ጠልቶ እንጅ አንተን ወዶህ ይመስልሃል ወይ?
  • የእኔን ዘር ስታጠፋ የራስን ዘር እያጠፋህ አይደለም ወይ?  እኔ አንበስ አንተ ሌንጮ ከመባላችንና በተለያዩ ልሳኖች አፋችንን ከመክፈታችን በስተቀር ምን ይለየናል?  የባዕድ አገር ሰው ይቅርና የራሳችን አገር ሰው በመመልከት ብቻ እኔን አማራ አንተን ኦሮሞ ማለት ይችላል ውይ?  እንደ ሠርገኛ ጤፍ ቅይጥ ቀይጥይጥ የሆነው የጦቢያ ሕዝብ በወንፊት ቢነፋ ተንጓሎ የሚቀር አለ ወይ?   
  • ኦሮሞነት የስም እንጅ የደም እንዳልሆነ አታውቅም ወይ?  ጉበና፣ ጉዲሳ፣ ባልቻ፣ አጋ የተባለ ሁሉ በደሙ ኦሮሞ ነው ያለህ ማነው?  ኦሮሞነት ከኔ ወዲያ ላሳር የሚለው ወለጌ፣ የኦሮሞነት ምንጭ ነኝ ከሚለው ከቦረኔ ይልቅ በአካልም በባህልም ይበልጥ የሚመሳሰለው ከጎጃሜ ጋር አይደለም ወይ? 
  • የውሸት ትርክትህ ውነት የመሰለህ ስለደጋገምከው አይደለም ወይ?  ይህ የውሸት ትርክት ያዋጣኻል ወይ? ዓሣ እጎረጉራለሁ ሲሉ ዘንዶ ማውጣት፣ የቆጡን አወርዳለሁ ሲሉ የብብትን መጣል እንዳለ አታውቅም ወይ?  
  • ኤርትራዊ ፀራማራ በተረከተልህ (narrate) የገዳ ትርክት (narration) እየታበይክ፣ የገዳ ውጤት የሆነውን በጭፍጨፋ የመስፋፋትህን ታሪክ ለምን ትክዳለህ?  ከሃያ በላይ ነገዶችን በሜንጫ በመቆራረጥ ድምጥማጣቸውን አጥፍተህ፣ ኤርትራዊ ፀራማራ የጻፈልህን ልብወለድ እንደ ቁርዓን እየቀራህ ሚኒሊክ ቆረጠኝ፣ ፈለጠኝ እያልክ ዝንታለም ማላዘን ምፅትነቱ አይታይህም ወይ?  
  • አጼ ሚኒሊክ አንተ እንደምትላቸው ቆራጭና ፈላጭ ከነበሩ፣ በተስፋፋህበት ሁሉ (ባሌ፣ ሐረርጌ፣ አሩሲ፣ ወለጋ) እርጋ ከማለት ይልቅ ድምጥማጥህን አያጠፉህም ነበር ወይ?  ኦሮሚፋ፣ ኦሮሙማ እያልክ ለመታበይ የበቃኸው አንተ በሌሎች ላይ ያደረከውን እሳቸው ባንተ ላይ ባለማድረጋቸው አይደለም ወይ? የፈለጉትን ለማድረግ ሁሉ በጃቸው በደጃቸው አልነበረም ወይ?        
  • የኔ አብናቶቸ (አባቶችና እናቶች) በሠሩት ቤት፣ እኔን መጤ አንተን ቤተኛ ስትል አታፍርም ወይ?  የኔ ቤት ከፈረሰ ያንተ ቤት ያውሬ መውለጃ እንደሚሆን አታውቅም ወይ? አንተ ቤት ሜንጫ ካለ እኔ ቤት ነፍጥ እንደሚኖር አትገምትም ወይ?  እድሜ ልኩን የአስመራ መንገድ ጠራጊ የነበረው ኦነግ፣ የቁርጥ ቀን ሲመጣ የሚያዋጣህ ይመስልሃል ወይ?
  • የመቶ ዓመታቱን ያለፈ ጉዳይ ሆድ ይፍጀው ብለን የወደፊቱን ብንመለከት አይሻልም ወይ? ያለፈውን  ብንመለከትስ የምንመለከተው ለመማማር እንጅ ለመበቃቀል ነው ወይ? ባድዋ፣ በካራማራ፣ በናቅፋና በባድመ አብረን ተዋግተን አብረን ሙተን የለም ወይ?   
  • ወዘተ. ወዘተ.        

 

እየየም ሲደላ ስለሆነ የመኖር ያለመኖር ጥያቄ ከፊቱ ለፊቱ ለተደቀነበት የአማራ ሕዝብ የፍትሕ ጥያቄ የቅንጦት ጥያቄ ነው፡፡  ለምሳሌ ያህል አሕግ (የአሜርቃ ሕቡር ግዛቶች፣ USA) ባንጻራዊ ደረጃ ፍትሕ የሰፈነባት አገር ናት፡፡ ይህ ፍትሕ የሰፈነው ግን እልፍ አእላፍ ፈጅሬ አሜሪቃውያን (native americans) ያለ ርህራሄ ተጨፍጭፈው ዘር ማንዘራቸው ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ ከጠፋና የተረፉት ጥቂቶች ደግሞ በግዴታ ግድፈቻ (በግዴታ ጉዲፈቻ በማድረግ፣ forced adoption) ማንነታቸውን እንዲለውጡ፣ ወይም ደግሞ የመጠጥና የእጽ ሰለባ እንዲሆኑ ከተደረገ በኋላ ነው፡፡  

በተመሳሳይ ሁኔታ የአማራው ሕዝብ ከኦነግ ሜንጫ ራሱን በራሱ ታድጎ ቀጣይነቱን ካላረጋገጠ በስተቀር፣ ዳንኤል የሚመኘውን ፍትህ፣ ርተዕና፣ ዲሞክራሲ ሊያጣጥሙ የሚችሉት ኦሮሙሜወች ብቻ ናቸው፡፡  ያማራ ብሔርተኛ ድርጅቶች ሊደገፉ የሚገባቸውም አማራውን ከኦነግ ጅብ ለመከላከል የግድ ስለሚያስፈልጉ ነው፡፡ ስግብግቡ የኦነግ ጅብ አብንን መደገፍን አማራጭ የሌለው ምርጫ አድርጎታል፡፡  

ስለዚህም ዳንኤል በእኩል ዓይን ቢመለከታቸውም፣ ሳይወድ በግድ በቅርብ ጊዜ ያቆጠቆጠው ያማራ ብሔርተኝነትና አሠርት ዓመታትን ያስቆጠረው የኦሮሞ ብሔርተኝነት ዱባና ቅል ናቸው፡፡  ዐብይ አህመድን የኦሮሞ ብሔርተኝነት ቅንጣት ሳያሳስበው ያማራ ብሔርተኝነት እንቅልፍ የነሳው ሁለቱ ብሔርተኝነቶች እየቅል መሆናቸውን በደንብ ስለሚያውቅ ነው፡፡ ያማራ ብሔርተኝነት ዓላማ አልኦሮሞ ጦቢያውያንን ከኦነግ ጽንፈኞች በመታደግ የጦቢያን ቀጣይነት ማረጋገጥ ሲሆን፣ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ዓላማ ግን በጦቢያ ፍርስራሽ ላይ የኦሮሞን አጼጌ (empire) መመሥረት ነው፡፡   

ጠላት ምንግዜም ጠላት ስለሆነ፣ አስቀድሞ መወገድ ያለበት የጠላት አሾክሿኪ ነው፡፡   ከፀራማራ ኦነጋውያን ጋር የሚደረገው የሞት ሽረት ትግል ስኬታማ ሊሆን የሚችለው ደግሞ አማራ የለም የሚለውን ግንቦት ሰባትን ካማሮች መኻል በመመንጠር ነው፡፡  ባሁኑ ጊዜ ከኦነጋውያን ይልቅ አማራውን ይበልጥ የሚጨፈጭፉትና የሚያስጨፈጭፉት ይህ መሠሪ ድርጅት በአዴፓ (ብአዴን) አመራር ውስጥ የሰገሰጋቸው ፀራማሮች ናቸው፡፡

 

ስለዚህ ክቡር ዳንኤል ክብረት፣ ስለ ፍትሕ ለመወያየት መቀመጥ ስለሚያስፈልገን፣ በመጀመርያ የመቀመጫችንን እሾህ እንንቀል፡፡    

 

    መስፍን አረጋ 

    mesfin.arega@gmail.com

                   

Filed in: Amharic