>
11:25 pm - Wednesday November 30, 2022

ያልተዘመረላቸው የስሜኑ ጀግና — ደጃዝማች ነጋሽ ወርቅነህ!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

ያልተዘመረላቸው የስሜኑ ጀግና — ደጃዝማች ነጋሽ ወርቅነህ!!!
አቻምየለህ ታምሩ
ዛሬ የማካፍላችሁ ሽራፊ ታሪክ  ዝርዝር ሀተታ «የወልቃይት ጉዳይ» በሚል ባለፈው ሳምንት ለአንባቢ ተደራሽ በሆነው መጽሐፌ ውስጥ ይገኛል። ስለታሪኩ ምንጮችና ባለታሪኩ አርበኛ ከወልቃይት ጉዳይ ጋር ስለሚያስተሳስራቸው ታሪክ ሙሉ ዝርዝር  መጽሐፉን ስታነቡ ትደርሱበታላችሁ።
ያልተዘመረላቸው የዛሬው ባለታሪክ  በፎቶ የምትመለከቷቸው መልከ መልካሙ አርበኛ ሲሆኑ ስማቸው  ደጃዝማች ነጋሽ ወርቅነህ ይባላሉ። ደጃዝማች ነጋሽ ወርቅነህ  የዝነኛ፣ አገር አውልና ስመ ጥር አርበኞች መፍለቂያ የነበረው የታሪካዊው የስሜን አውራጃ ተወላጅ ናቸው። በታሪክ ስሜን  የሚባለው የኢትዮጵያ ክፍል እስከ 1933 ዓ.ም. ድረስ  ከባምብሎ እስከ ተከዜ  ድረስ ያለውን አካባቢ የሚሸፍን ነው። ከአክሱም ዘመን ጀምሮ እስከ 1928 ዓ.ም. ድረስ  በስሜን የሚሾሙት አገረ ገዢዎች  ይዞታዎች «ባምብሎ በመለስ ተከዜ በፈሰስ» ይባል ነበር። ባምብሎ ከጎንደር ከተማ በስተ ሰሜን አቅጣጫ 30 ኪሎ ሜትር  ርቀት ላይ የሚገኝ ሸለቆ ነው። ስሜን አውራጃ  እስከ 1933 ዓ.ም. ድረስ በስሩ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሑመራ ወረዳዎችን የያዘ ነበር።
ከ1934 ዓ.ም. በኋላ ግን የአገር ግዛት ሚኒስቴር ባወጣው የመጀመሪያው አዋጅ  መሠረት ከወረራ በፊት  የነበሩት 42 አውራጃዎች በ12 ጠቅላይ ግዛቶች [ከ1950 በኋላ 14 ሆነዋል] ሲጠቃለሉ ስሜን አውራጃ  የስሜንና በጌምድር ጠቅላይ ግዛት አካል ሲሆን  ስሜን  አውራጃ  የነበረው ወገራና ስሜን በሚል በሁለት አውራጃዎች ተከፍሏል።
ደጃዝማች ነጋሽ ወርቅነህ  የሚወለዱት ከመሳፍንት ወገን ነው። አባታቸው ደጃዝማች ወርቅነህ የራስ ገብረመድኅን ኃይለማርያም ገብሬ ተስፋ ልጅ ሲሆኑ የአባታቸው የደጃዝማች ወርቅነህ ገብረ መድኅን  አጎት  ዝነኛው የስሜን  አገረ ገዢ ደጃዝማች ውቤ ኃይለ ማርያም ገብሬ ተስፋ ናቸው። ደጃዝማች ውቤ ኃይለ ማርያም የዘመነ መሣፍንትን  ዘመን ፍጻሜ ለማድረግ ቆረጠው ከተነሱ አገረ ገዢዎች መካከል ቀዳሚው ነበሩ። ከሳቸው በኋላ የተነሱት የቋራው ልጅ ካሳ ኃይሉ፣ የጎጃሙ ደጃዝማች ተድላ ጓሉና የሸዋው ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ  ተቀናቃኞቻቸውን በመጠቅለል ያለ አንጋሽ ለመንገሥ የተነሱ ቢሆንም የተሳካላቸው የቋራው ልጅ ካሳ ኃይሉ ብቻ  ነበሩ።
የቋራው ባለራዕይ ልጅ ካሳ ኃይሉ በለስ ስለቀናው ደራስጌ ላይ በዋለው ጦርነት ደጃዝማች ውቤን ድል አድርጎ ሲነግሡ  ዘውድ ለመጫን ባሰሩት ደብር በደራስጌ ማርያምና  ዘውዱ ሲጭኑ እንዲቀቧቸው ባስመጧቸው አቡን በአቡነ ሰላማ እጅ ተቀብቶ «ግርማዊ፡ ዳግማዊ፡ ዐፄ፡ ቴዎድሮስ፡ ሞዓ፡ አንበሳ፡ ዘእምነገደ፡ ይሁዳ፡ ንጉሠ፡ ነገሥት፡ ዘኢትዮጵያ፡ ሰዩመ፡ እግዚአብሔር» ተብሎ ነገሠ።
ከዐፄ ቴዎድሮስ በኋላም ዐፄ ተክለ ጊዮርጊስ ዐድዋ ላይ ድል ሆነው ዐፄ ዮሐንስ ነግሠው የተከዜን ወንዝ ተሻግረው እሳቸው እንዳሉት አማራው አገር እስኪገቡድ ድረስ  «የዐፄ ቴዎድሮስ መንበር ተረካቢና የዙፋኑ ወራሽ በመሆን ነግሻለሁ» በማለት ለግብጹ ገዲቭ እስማኤል ይጽፉ የነበሩት ወልቃይቴው የአማራ ተወላጅ ርዕሰ መኳንንት ራስ ወረኛ ወልደ ኪዳንም የደጃዝማች ነጋሽ ወርቅነህ አጎት ናቸው።  ከደጃዝማች ነጋሽ ታሪኮች ቀዳሚው በፋሽስት ጥሊያን የወረራ ዘመን ያደረጉት አስደናቂ ተጋድሎ ነው። ኢትዮጵያ በፋሽስት ወረራ ስር በነበረችበት ወቅት አብዛኞቹ አገረ ገዢዎች፤
በሰማይ በራሪ ምድር ተሽከርካሪ፣
ሞሶሎኒ መጣ በገንዘቡ አዳሪ፤
እያሉ ለፋሽስት ሲገቡ እሳቸው ግን ከባምብሎ እስከ ተከዜ ያለውን የአባቶቻቸው ግዛት «ስሜን ስሙ ታውቆ፣ ክብሩ ተጠብቆ መኖሩ ሲታወቅ፡ ባሁኑ ጊዜ በጠላት ውስጥ ሁኖ እንዲተዳደር ባደርግ የሐገሩ ታሪክ ሲጠፋ ቁሜ አላይም» ብለው የቀረበላቸውን ሁሉ መደለያ ገፍትረው ለአርበኛነት የተሰማሩ ጀግና አርበኛ ነበሩ። አንተ በመባያ እድሜያቸው አንቱ የሚያስብል ስራ የሰሩ የጀግኖች ቁና ናቸው።
በአርበኛነት ዘመናቸውም በሰማይ በራሪና  በምድር ተሽከርካሪ ከሆነው የፋሽስት  ጦርና ባንዶች  ጋር አይበገሬነትን  ብቻ ታጥቀው  ከአስር ሺህ በላይ  የነበረውን ጦራቸው  በመምራት አምስቱን አመት ሙሉ ከወረራ ነጻ ለመሆን የቻለ ነጻ ግዛት ለማቆየት ችለዋል። በአምስቱ የፋሽስት የወረራ ዘመን  በመላው አገሪቱ ወድቆ የነበረው የኢትዮጵያን ሰንደቅ አለማ  ከፍ ብሎ ሲውለበለብባቸው ከነበሩት ጥቂት  የአገራችን አካባቢዎች መካከል በደጃዝማች ነጋሽ ወርቅነህ  ነጻ ወጥቶ ይተዳደር የነበረው ከባምብሎ እስከ ተከዜ የነበረው  የስሜን አውራጃ ቀዳሚው ነበር።
ከዚህ በተጨማሪ በደጃዝማች ነጋሽ  የተመራው  የአርበኛ ጦር ነጻ ያወጣው ስሜን በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል ንቅናቄ ያደርጉ የነበሩ አርበኞች ከለላ የሚያገኙበትም  ምድር ነበር። በግራዚያኒ ላይ ቦንብ  የወረወሩት  እነ አብርሐም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም  ከአዲስ አበባ አምልጠው ሕይወታቸውን  ለማትረፍ ለመጀመሪያ ጊዜ  የተደበቁት  ደጃዝማች ነጋሽ ወርቅነህ  የሚመሩት የስሜን አርበኞች ባወጡት በወልቃይት ምድር ነበር።  ደጃዝማች ነጋሽ ነጻ ካወጡት ምድር በሚሰበስቡት ግብር ሌሎች አካባቢ የሚካሄደውን የአርበኛነት ተጋድሎ ይደግፉ፣ ስልጠናም ይሰጡ ነበር።
ደጃዝማች ነጋሽ የፋሽስት የወረራ አልቆ ኢትዮጵያ  ሙሉ በሙሉ ነጻ ስትሆን በንጉሠ ነገሥቱ ተሹመው የስሜን አውራጃ አስተዳዳሪ ሆነው አገልግለዋል። በኋለኛው የሕይወት ዘመናቸው  ደግሞ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ነበሩ። የደጃዝማች ነጋሽን ሌሎች ታሪኮችና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባነ በነበሩበት ወቅት የተነሱትን   ታሪካዊ ፎቶ፤ በፋሽስት ዘመን ስለነበረው የባምብሎ በመለስ ተከዜ በፈሰስ የአስተዳዳርና ወሰን ታሪክ፤ በወረራው ዘመን ስለነበረው የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራ አርበኞች ተጋድሎና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ስለከፈሉት መስዕዋትነት  በዝርዝር ለማግኘት «የወልቃይት ጉዳይ» ውስጥ የቀረበውን ታሪክ ታነቡ ዘንድ በድጋሜ  እጋብዛለሁ።

Amazon’s link:  https://www.amazon.com/Wolkait-Affairs-Achamyeleh-Tamiru/dp/1513653806/ref=sr_1_1?keywords=achamyeleh&qid=1573496481&sr=8-

Filed in: Amharic