>
5:18 pm - Friday June 15, 3860

የኢትዮጵያ ህዝብ  የኔ የሚለው መንግስት እስኪፈጠር ድረስ ትግሉ መቀጠል አለበት!!! (ሉሉ ከበደ)

የኢትዮጵያ ህዝብ  የኔ የሚለው መንግስት እስኪፈጠር ድረስ ትግሉ መቀጠል አለበት!!!
ሉሉ ከበደ
ሀዘናችንና ለቅሶአችን የሚቆምበት ምእራፍ የቱ ጋ እንደሆነ መተንበይም የማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ዛሬ ህዝባችን እንዴት ይሆን የዋለው? ነገ ምን ይመጣበት ይሆን? እያልን በስጋት እዚያችው ሲኦል ምድር ኢትዮጵያ  ውስጥ ካለው ህዝባችን ጋር እዚህ በብዙ ሺህ ማይልስ ርቀት ላይ ያለነው ኢትዮጵያውያንም ተሰቃይተናል።
ግንቦት 1983 አ•ም በፊት የኢትዮጵያ ህዝብ  የፈለገበት ጥግ ድረስ ሄዶ በሰላም የሚኖርባት ሀገር ነበረችው ። ዛሬ ግን ያችው የሚኮራባት ሀገር የሲኦል ምድር ሆናበት ፤ ባእድ ሀገር የተሰደደው ከባአድ የሚያገኘውን ሰላምና ፍቅር ደህንነት አገር ቤትያለው  በቤቱ አቶ የጭንቅ ኑሮ ለመኖር ተገዷል። ይባስ ብሎ በህይወት የመኖር ዋስትናም ተነፍጓል።  ዛሬ ነገ መንጋው ይመጣብኛል ፤እገደላለሁ እያለ በጭንቅ የሚኖር ዜጋ ለመሆን መብቃቱ ልብ የሚሰብር ሁኔታ ነው።
ከሁሉም  በላይ የከፋው ደሞ  ለህዝቧ ጥላ ከለላ መሆን የሚችል መንግስት መጥፋቱ ነው። ዘረኞች የተሳለ ገጀራ ይዘው ሲመጡበት  ፤ ሜንጫ ይዘው በመንጋ ሲሰማሩበት፥ ቀስት ታጥቀው ሲዘምቱበት፤፥ ለመናገርም በሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲጨፈጭፉት የሚደርስለት ፥ ገዳዮችን የሚያስቆምለት፤ ፖሊስ  ጦርሰራዊት ማጣቱ የኢትዮጵያን ህዝህ ሰቆቃ ከሌላው አለም የተለየ አድርጎታል።
መንግስት አለ በሚባልበት ሀገር ውስጥ አንድ ተራ ግለሰብ ተነስቶ ባደባባይ  ፤ መሬት ውረሩ ፤ ንብረት ዝረፉ፤  ቤተክርስቲያን አቃጥሉ፤ መስጊድ አቃጥሉ ፤መንገድ ዝጉ ፤ ሲል የተናገረውም ያለምንም ከልካይ ሲፈጸም መንግስት ነኝ የሚለው ቡድን ምንም ሲያደርግ አለመታየቱ የማያቋርጥ ጥፋት ተደግሶልናል ማለት ነው።ይህ ነገር አንድ ቦታ ላይ ካልቆመ ብዙ አደጋ ይገጥመናል። የሚድን ሰው አይኖርም።
ጃዋር የሚባል  ታዳጊ ሂትለር ጫቱን  ጠግቦ በጫራት ተከብቤአለሁ ተወርሬአለሁ የውሸት ወሬ እንደከብት የሚከተለው መንጋ ከየቅጣጫ ተግተልትሎ ዘር እየመረጠ፤ ሀይማኖት እየለየ፤ የጭካኔ ካራውን በህጻናት ላይ ሳይቀር አሳረፈ። አራስ እናት በድንጋይ ወግሮ ገደለ።ከ 86 በላይ ንጹሀን ወገኖቻችንን ጭዳ አደረገ። ቤተእምነቶችን አቃጠለ። የንጹሀን ዜጎችን ቤት ንብረት አቃጠለ። ይህንን የአጋንንት ሰራዊት ባፋጣኝ ሊያስቆምና ተጎጂውን ህዝብ ሊታደግ የሞከረ ባለስልን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ አልታየም። ትልቁ አሳዛኝ ክስተት ይሄ ነው። ባለስልጣናቱ ገዳዮቹንና ያሰማራቸውን እኩይ ሰው  በመደገፍ መግለጫ ይሰጡ ነበር። ጉዳያቸው በሱ በኩል የሚፈጸም መሆኑ ነው።
የደቡብ አፍሪካ ዜጎች ድንገት እየተነሱ የስደተኛውን ሀብትና ንብረት ሲዘርፉ፥ ኢትዮጵያውያንንና ሌሎችንም ዜጎች ውጡልን እያሉ በገጀራ እየከታተፉ በእሳት ሲያቃጥሉ የማይዘገንነው የአለም ህዝብ የለም። ባርባሪክ አክት ያላለ ነጭ የለም። እኛም በንዴትና በቁጣ ያልጮኽንበት ጎዜ የለም። ለካንስ ያ ጭካኔና ግፈኝነት  በራሳችንም ወገኖች ደም ውስጥ ሞልቶ ተርፎ ያለ  ደዌ ነው ።
2014 አይሲስ በሊቢያ ባህር ዳርቻ 38 ኢትዮጵያውያንን በጁ ገዝግዞ አይናችን ስር ሲያርዳቸው አውሬ እንጂ ሰብ አዊ ፍጡር የማይሰራው ጭካኔ ብለን ተቆጥተን ነበር። ውሎ ሲያድር  እኛም ከአይሲስ የባሰ ከደቡብ አፍሪካ የባሰ ከሩዋንዳ የባሰ አውሬ  በውስጣችን መኖሩን ጃዋርና አምላኪዎቹ ቄሮዎች አሳዩን።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ  እዚያው ለወሬ ከሄደበት ሞስኮ እንኳ ሰምቶ ማዘኑን አልነገረንም ነበር። ሰው መግደል አልፈልግም የሚለው ሰው እንዴት ለታረዱት ዜጎቹ በሀዘን ተፈንቅሎ ወደቤቱ አልመጣም? ይቅር ሊቆጣና ህግ ሊያስከብር ። ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ህዝብ  የሚተማመንበት መንግስት  የለውምና የኔ የሚለው መንግስት እስኪፈጠር ድረስ ትግሉ መቀጠል አለበት የምንለው።
እርግጥ ነው ዛሬ ለወደቅንበት አዘቅት ለገባንበት መቀመቅ ተጠያቂ የዘር ፖለቲካውን በሽታ ተሸክሞ የገባው ህውሀት ቢሆንም እኛም እንደህዝብ በመጠኑም ቢሆን ተጠያቂነት አለብን።አንዱ ሲቃወም ሌላው ዝም ማለቱ። አንዱ ሲጎዳ ሌላው እኔ ላይ አልመጣም ብሎ እንዳላየ መሆኑ። በትንሽ ጥቅማጥቅም እየተደለለ አንዱ ሌላውን አሳልፎ መስጠቱ የራሳችንን ስቃይ ከሚያባብሱ ችግሮቻችን ጥቂትቹ ናቸው።
ሌላው ደግሞ ለልጆቻችን የምናስተምረው ነገር ነው። ልጆች የቤተሰብና የማህበረስብ ውጤቶች ናቸው። ወላጆች የልጆቻቸውን ስብእና የመቅረጽ ሀላፊነትም እድልም ጊዜም አላቸው። ቢያንስ 14 አመት እስኪሆናቸው ድረስ እቤት ውስጥ የልጆቻችንን አስተሳሠብ በምንፈልገው አቅጣጫ መቅረጽ የምንችልበት ጊዜ ነው። የምናስተምራቸው ጥሩ ነገር ሁሉ በጭምቅላታቸው የሚቀርበት ጊዚ ነው ። የምንነግራቸው ክፉ ነገርም እንደዚያው። ህይወታቸውን ሙሉ ሊከተላቸው ይችላል። ሁላችሁም እራሳችሁን መርምሩ።
ባለፈው ሀያ ስምንት አመታት በሀገር ደረጃ በመንግስትነት አቅም ፥ በተጠናከረ ሁኔታ ሲረጭ የነበረው መርዝ  የጥላቻ የልዩነት የዘረኝነት የሀሰት ትርክትና ታሪክ ዛሬ የምናየውን ተምሮም ምንም ማገናዘብ የማይችል በጭካኔ የተሞላ ትውልድ ሊፈጥር ችሏል። ዩኒቨርስቲ ውስጥ አብረው ተቀምጠው መማር የማይችሉ ልጆች መፍጠር ተችሏል።ይህ እንዳይሆን ቤተሰብ በልጆቹ ላይ ማድረግ የሚችለው ነገር ነበር።በሬዲዮ በቴሌቪዥን በጋዜጣ በትምህት የሚሰራጨው በፈጠራ የተሞላ  የህዝባችን ግንኙነት ታሪክ ውሸት መሆኑን ያለመታከት በማስረዳት እውነተኛው ታሪክ ይህ ነው እያሉ ልጆችን ማስተማር መምከር ይገባል። የጥላቻ ወሬ የዘረኝነት ስበካ እንዳይሰሙ ማስተማር መምከር ያስፈልግ ነበር። ያን ግን አላደረግንም። የሆነው ነገር ምንድነው? አንድ ምሳሌ ላቅርብላችሁ።
ፌብሩዋሪ ወር 2017 ላይ አንድ ህጻን ልጅ በቪዲዮ በማህበታዊ መገናኛ ብዙሀን በስፋት ይሰራጭ ነበር።አይታችሁትም ሊሆን ይችላል። እድሜው ሶስት አመት አካባቢ የሚሆን በቅጡ አፍ ያልፈታ ኦሮሞኛ የሚናገር ልጅ የቁመቱን ግማሽ የሚያክል ትልቅ ቢላዎ ይዟል።
አንድ አዋቂ ሰው ይጠይቀዋል ” ሁል ጊዜ ቢላዎ ይዘህ አይሀለሁ ለምንድነው ቢላዎ የምትይዘው?’ህጻኑ ልጅ እየተኮላተፈ ይመልሳል።
” አርድበታለኋ” ይላል።
” ማንን ነው የምታርድርው?
“ወያኔን ነው የማርድበት”
” ለምንድነው ወያኔን ምታርዳት?”
“የኦሮሞን ደም ትጠጣለቻ”
“የማታርደውስ ማንን ነው?”
” የኦሮሞ ነጻነት ግንባሮችን አላርድም”
“የወያኔ ሰዎችና የኦነግ ሰዎች እቤትህ ቢመጡ የትኛውን ነው ግባ የምትለው?
” ኦነጎችን እቤት ውስጥ እተዋቸውና ወያኔዎቹን አርዳቸዋለሁ “
ትልቁም ይስቃል ትንሹም እየሳቀ ቪዲዮው ያቆማል። ይህ ልጅ ይህንን አስተሳሰብ በናቱ ሆድ  ተምሮ አይደለም የወጣው  እቤት ውስጥ ሰፈር ውስጥ በጡጦ የተጋተው በሽታ ነው። ትምርቱ በዚያ መልክ ከቀጠለ አስራ ስድስትና አስራሰባት አመት ሲሞላው በገጀራ ሰውን ቢቆራርጥ  ምን ይደንቃል?  አሁን እየሆነ ያለው ይህ ነው። እግዜብሄር ያጥናን።
Filed in: Amharic