>

ዲ ፋክቶ ስቴት - ጉዞ ወደ ፈንጂ ወረዳ!!! (አብርሃ በላይ )

ዲ ፋክቶ ስቴት – ጉዞ ወደ ፈንጂ ወረዳ!!!

በአብርሃ በላይ 
ትህነግ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት እሱ ራሱ የማይቆጣጠረው ከሆነ ከኢትዮጵያ ተነጥሎ ለመሄድ አይኑን አያሽም ብዬ ነበር። የሆነውም እሱ ነው። የትህነግ የረጅም ጊዜ ባህርይ ለሚያውቅ – ይህ ክስተት እንግዳ አይሆንበትም።
የገረመኝ ነገር ግን፣ “ዴ ፋክቶ ስቴት ኦፍ ትግራይ” (de facto state) ብሎ ትህነግ ሲያውጅ፣ ትህነግ ትግራይን ወደ “ፈንጂ ወረዳ” ይዛ እየወረደች መሆንዋን ቢያንስ በውጭ ያለው ትግራዋይ ተቃውሞውን ከፍ አድርጎ ያሰማል ብዬ ነበር። አልሆነም። አንድ አብርሃ ደስታ “ዴ ፋክቶ ስቴት አደጋ ነው” በማለቱ ብቻ የትህነግ ጀሌ የለቀቀው የስድብ ናዳ ጉድ ያሰኛል።
ወገኔ ትግራዋይ – ኑሮ በ “ዴፋክቶ ስቴት” – የባርነት ኑሮ ነው። ግራ ሊያጋቡህ፣ “ዲ ፋክቶ” የሚል “ጃርገን” (ቴክኒካል ቃል) ቢጠቀሙብህ፣ ቀላል ትርጉሙ “አብሮ መኖር የማይወድ፣ የወንበዴ፣ የተገንጣይ መንግስት” ማለት ነው።” ቢያንስ በንግድ፣ በዲፕሎማሲ፣ በባንክ … ዘርፈ-ብዙ ችግር ያራውጥሃል። ውስብስቡን የንግድና ባንክ ጉዳይ ትተን፣ በትንሽዋ የፓስፖርት ነገር እንኳን እናንሳ። ከትግራይ ተነስተህ ወደ ውጭ ለመጓዝ ብትፈልግ “ዓለም ያወቀው ፓስፖርት” ስለማይኖርህ፣ ወይ አርፈህ መቀሌ መቀመጥ ነው፣ ወይም “ስፖንሰር” የሚያደርግህ ሀገር መፈለግ ነው። ምናልባት ሱዳን? መዋረድ ካልቀረ እንደዛ ነው እንጂ።
“ኢትዮጵያዊ” የሚለው ፓስፖርት የምታገኝ እንዳይመስልህ። “ትግራይኮ የኢትዮጵያ መሰረት ነች! ከአክሱም ስልጣኔ ጀምሮ…. ኢትዮጵያ የሚለው ስም ካለ ትግራይ አይሰራም። ስለዚህ የትግራይ መንግስት የኢትዮጵያ መንግስት ብሎ ራሱን ሰይሞ፣ ፓስፓርት መያዝ ማን ይከለክለዋል” ብትል የሚሰማህ አታገኝም። አለም አቀፍ ህጉ አይፈቅድልህም።
የኢትዮጵያ ፓስፖርት ባለቤት የተቀረችው ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው፣ አለም አቀፍ እውቅና ከተጎናፀፈ ዘመናት ያስቆጠረው በአዲስ አበባ የሚገኘው መንግስት (de jure state) እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው።
ታድያ መፍትሄው ምንድነው ካልክ፣ ኢትዮጵያዊነትህን እያሳጣህ ያለውን ትህነግ ታግለህ ጣለው! ‘ዲ ፋክቶ ስቴት’ ባርነት ነው! ኢትዮጵያዊነት ግን ክብር ነው!
Filed in: Amharic