>

የኦሮሞ ሕዝብ የታገለው መብቱንና ጥቅሙን  ለማስረገጥ ወይስ የጃዋርን ፍላጎት ለማሳካት? (ብሩክ አበጋዝ)

የኦሮሞ ሕዝብ የታገለው መብቱንና ጥቅሙን  ለማስረገጥ ወይስ የጃዋርን ፍላጎት ለማሳካት?
ብሩክ አበጋዝ
የኦሮሞን ሕዝብ የዘመናት ጥያቄ እየመለሰ ያለው ጠሚ ዓቢይ ወይስ አክቲቪስት ጃዋር? የኦሮሞ ሕዝብ የዘመናት ጥያቄን ከመመለስ ባሻገር ተሻጋሪ ጥቅሞችን ለማስከበር የመሪ ክህሎትና በፈተና የማለፍና ብቃት ያለው ጠሚ ዓቢይ ወይስ አክቲቪስት…?
:
የኦሮሞ ሕዝብ ጭቆናን በማስወገድ እኩልነትን አረጋግጣለሁ እንዲሁም የአገር ባለቤትነት እሆናለሁ በማለት በተለያዩ ዘመናት ትግል አድርጓል። #በንጉሠ_ነገሥቱ_ዘመነ_መንግስት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከዚሁ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችና አገዛዙ ላይ ያነጣጠረ ተቃውሞ በተለያዩ የአገራችን ክፍል ተካሂዷል። የጎጃም ገበሬዎች፣ የራያ ገበሬዎች፣ የየጁ ገበሬዎች እንዲሁም የባሌ ገበሬወች አመጽ ጎልተው የሚጠቀሱ ናቸው። ኦሮሞው በተደራጀ መልኩ የንጉሡን አገዛዝ በተደራጀ መልኩ ተቃውሞውን ያሳየው በባሌ ገበሬወች አመጽ ነበር። እንደ አገሪ ቱሉ ዓይነት የሰላሌ ጀግኖችም በሽፍትነት ቢሆንም በተናጠል የንጉሡን አገዛዝ ፈትነውት ነበር። ከዚያ በኋላ ባለው ዘመን እንደ ሜጫና ቱለማ ዓይነቱ ማህበር መመስረትና የመገናኛ መድረክ በመሆኑ የማህበረሰቡን መብት፣ ጥቅምና የአገር ባለቤትነት መብት ለማስከበር እርሾ ሆኗል።
.
በንጉሠ ነገሥቱ መንግስት ቁልፍ ሚና የነበራቸው የእነ ጀነራል ታደሰ ብሩ ይፋዊ የሆነ ትግልና አርበኝነት በርካታ የማህበረሰቡን ልጆች ከዚያም በላይ ለመረረ ትግል እንዲነሳሱ ምክንያት ሆኗል። እንደ ኦነግ ዓይነት ድርጅቶችም በሂደት ተወልደዋል፤ በግለሰብ ደረጃም በርካታ የኦሮሞ ወጣቶች ፈር ቀዳጅ በመሆን በተለያዩ አደረጃጀቶች ሥር የንጉሠ ነገሥቱን መንግስትና ከዚያም በኋላ የነበረውን የደርግ መንግስት ታግለዋል። የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ከጽንሰቱ በኢትዮጵያ ውስጥ መብትን የማስከበር፣ እኩልነትን የማረጋገጥ፣ የአገር ባለቤት የመሆን እና የባህልና የቋንቋ መከበርን ማረጋገጥና ፍትህና እኩልነትን ከመሻት የመነጩ ናቸው። ይሁንና ከኦነግ ትግል እንቅስቀሴ በኋላ የትግሉ አቅጣጫ ከላይ ካስቀመጥኳቸው ጉዳዮች በተጨማሪ ከኢትዮጵያ በመገንጠል ኦሮሚያ የምትባል አገር ምስረታን እውን ወደ ማድረግ ተሸጋግሯል።
.
ኦነግ ከኢትዮጵያ የተገነጠለች ኦሮሚያ የምትባል አገር እመሰርታለሁ በማለት ሲያካሂደው የነበረው ትግል እንዲሁም ሌሎች በርካታ ድርጅቶች በኢትዮጵያና በዛሬዋ ኤርትራ ውስጥ የደርግ መንግስት ላይ ያነጣጠረ ተናጠላዊ ትግል አድርገዋል። በመጨረሻ ሻዕቢያ፣ ኢህአዴግ፣ ኦነግ፣ ኦብነግ ወዘተ ነጥረው በመውጣት የተዳከመውን የደርግ መንግስትን በመጣል ለሥልጣን በቁ። ሻዕቢያ ኤርትራን በመያዝ ራሱን ሲችል፤ ኢትዮጵያ በኢህአዴግና ኦነግ እንዲሁም ሌሎችም መዳፍ ሥር ወደቀች። ብልጡ ኢህአዴግ ሽግግር መንግስት ከመሰረተ በኋላ የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ኦነግን ከጨዋታ ውጭ በማድረግ ጭራሹን አዳክሞ አመራሩም በተለያየ መልኩ ከአገር ተሰደደ ቀሪው መሄጃ የሌለው ደግሞ በእስር፣ በእንግልት እንዲሁም በኦህዴድነት ቀጠለ።
.
የኦነግ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ሌንጮ ለታ በኢህአዴግ ተገፍተው ከወጡ በኋላ በጻፉት ሀተታ ለበርካታ ዓመታት ሲታገሉሉት የነበርው የመገንጠልና አገር የመመስረት ትግል የማያዋጣ እንደሆነ ልዩነታቸውን ገለፁ። የኦነግ የመገንጠል ፖለቲካ ከጊዜ ወደ ጊዜ የማያዋጣ እየሆነ ተሸናፊ የፖለቲካ አስተሳሰብ ለመሆን በቃ። ኦነግ ተሰነጣጠቆ በጣት የሚቆጠሩ ድርጅቶች ለመሆን ሲበቃ፤ እርስበርስ ፍትጊያውና ባላንጣነቱ አየለ። ይኼ የፈጠረው ክፍተት እንደ ጃዋር ዓይነት ጎረምሶች በስኮላርሺፕ የተገኘ የሀይስኩል ትምህርቱን በሲንጋፖር ተምሮ ወደ አሜሪካ በመሻገር ቀጣይ ትምህርቱን በመከታተል እግረ መንገዱን የኦሮሞን ፖለቲካ በኢትዮጵያ አውድ በመተንተንና የመገንጠል ጥያቄን በመቃወም የመገናኛ ብዙሀንን በተለይም አገራዊ ፖለቲካ አንቀሳቃሾቹን ትኩረት በመሳቡ ለእውቅና በቃ።
.
ጃዋር ከኢትዪጵያ አገራዊ ፖለቲከኞችና ደጋፊወቻቸው ጋር ከአውድ ውጭ በተተረጎሙ የእሱ ሀሳቦችና በቃላት ግድፈቱ ባጋጠመው ተቃውሞ የኦሮሞ ብሄረተኛው ቡድንን ድጋፍ በማግኘቱ ሜዲያ እስከ ማቋቋም ደረሰ። ከዚያም በመቀጠል የማህበራዊ ሜዲያ መስፋፋትን ተከትሎ በአክቲቪዝም ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲመጣ ትግል አድርጓል። ጃዋርና መሰሎቹ ይኼን ትግል ሲያደርጉ የነበረው የኦሮሞ ሕዝብ ጭቆናን በማስወገድ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚል ሲሆን የመገንጠል ጉዳይን ደግሞ ራስን በራስ የማስተዳደር ትግል በሚል በተደጋጋሚ ሲደሰኮር የምንሰማው ነው። እንግዲህ ጃዋር ለኦሮሞ ሕዝብ አደረግኩት የሚለው ትግል አሜሪካ በተመቻቸ ህይወት ውስጥ ሆኖ አክቲቪዝምና የኦ ኤም ኤን ኃላፊ መሆኑ ነው። እንደሚታወቀው ህወሓትን በማዳከም የኃይል ሚዛኑን በመቀየር አሁን የምናየውን የፖለቲካ ምህዳር በመፍጠር የተለያዩ በርካታ አካላት ድርሻ አላቸው።
.
ይሁንና #TeamLemma የሚባለው የብአዴንና የኦህዴድ ጥምረት የውስጥ ትግል በማድረግ ከፍተኛ የሆነ የጎላ ድርሻ አለው። ጃዋር የኦህዴድ አመራሮች መቼም ለእኔ መልስ አይሰጡኝም መልስ ከሰጡም ትርፉ ለእኔ ነው በማለት የለውጡ ፊታውራሪ እሱ እንደሆነ፣ ሁለተኛ መንግስት እንደሆነ፣ መስዋዕትነት ከፍሎ እንቅልፍ አጥቶ ታግሎ ያመጣው ለውጥ እንደሆነ ሲገልጽ ኖሯል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሲገርፉን፣ ሲያስሩን፣ ከአገር ውጭ ሲያሰድዱን፣ ወደ አገራችን እንዳንገባ ያደረጉን የኦዴፓ ሰወች አሁን ደግሞ በአገራችን እንዳንኖር አደረጉን ዓይነት ሀፍረት የሌለውን ቅስቀሳ ማድረግ ጀምሯል። ጃዋር በፖለቲካ ምክንያት ወደ ውጭ አገር አልተሰደደም፤ ጃዋር አሁን መቼም ሰበብ ይፍጠር እንጂ ወደ ሲንጋፖር ሲሄድ አይደለም ፖለቲካ ሊያውቅ ቂጡን ያልጠረገ ጩጨ ነበር። ከሲንጋፖር ወደ አሜሪካ የተጓዘውም ልክ ባህር አቋርጠው የተሻለ ኑሮ በመሻት እንደሚጓዙት ወገኖቻችን እሱም የተሻለ ኑሮና ትምህርት በመሻት እንጂ በፖለቲካ ምክንያት ተሳዶ አልነበረም። አሜሪካ ሲማር የነበረው የፖለቲካ አቋም ለኢህአዴግ የሚስማማ ዓይነት እንጂ ሌላ አልነበረም።
.
ጃዋር ባለፈው ወደ አገሬ ልመለስ ብዬ ፓስፖርቴን ለማሳደስ ወደ ኢትዮጵያ ብልክም በፖለቲካ አቋሜ ምክንያት ፓስፖርቴን የኢትዮጵያ መንግስት ነጠቀኝ ብሎ ጽፎ ፈታ አድርጎኛል። ለመሆኑ እሱ የመንግስት ትኩረት ያረፈበት ፖለቲከኛ መሆኑን እያወቀ የኢትዮጵያ መንግስት እንዴት ፓስፖርት ያድስልኛል ብሎ አሰበ? ቢያድስለትስ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ሊታገል ወይስ ኑሮውን አስተካክሎ እዚያው ሊቀጥል? ያው ጃዋር በዚያ መልኩ የጻፈው ነገር የፈጠራ ወሬ እንደሆነ ለማረጋገጥ ችያለሁ (መቼም ዕድለኛ ነው ዛሬ ምንም ቢል፣ ምንም ቢዋሽ ትክክል ነው ብሎ የሚያምነው በርካታ ደጋፊ አፍርቷል)። የሆኖ ሆኖ ጃዋር ገና በልጅነቱ ከአገር የወጣውም በዚያው የቀረውም በፖለቲካ ምክንያት ሳይሆን በትምህርትና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ነው።  በእርግጥ በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት ገዥወቹ ያሳደዷቸው በርካታ ኦሮሞወች እንዳሉ ማንም የማይታበል ሀቅ ነው።
.
ጃዋር ራሱን ያለፈው መንግስት ተጠቂ አድርጎ ለማቅረብ የሚፈልገው ጠሚ ዓቢይን ጨምሮ አሁን ስልጣን ላይ ያሉትን የኦዴፓ ሰወች ለማሸማቀቅ እነሱን ጨቋኝና የግፈኛው ሥርዓት አድራጊ ፈጣሪወች ተደርገው እንዲሳሉ እንዲሁም እሱ ያስተባበረው ወጣቱ በታገለው ትግል ለውጥ እንደመጣና የኦዴፓ ሰወች ለለውጡ ድርሻ የሌላቸው እንደሆኑ እንዲቆጠር ነው። ከዚህም በላይ ታግየ አታግየ ነጻ ያወጣኋቸው ትናንት በአገሬ እንዳልኖር ያደረጉኝ የኦዴፓ ሰወች አሁን ደግሞ በአገሬ እንዳልኖር እያሴሩብኝ እየገፉኝ ነው የሚል የብልጥ ለቅሶና አመራሩን በማሥጠላት ራሱን ጻዲቅ አድርጎ ፖለቲካ ለመስራት ነው። ሀቁ ግን በመስዋዕትነት ደረጃ ከተሰላ ከእነ ታየ ደንደአ ዓይነት ቆራጥ ታጋዮች ጎን በጎን ህወሓትን የሸኘው ጃዋር ያደረገው ተጽእኖ ሳይሆን የብአዴንና የኦዴፓ ሰወች ፊት ለፊት ያደረጉት ትግል ነው። ቄሮንም ቢሆን ጃዋር መርቶት አያውቅም፤ መቼም እነ ለማና ዓቢይ እንዲሁም ደመላሽ ቄሮን እኛ እንመራ ነበር ብለው እንደማይከራከሩት ስለሚያውቅ ያለ ሀፍረት ያላደረገውን ነገር የቄሮ መሪ እንደነበረ ይደሰኩራል።
.
እንደሚታወቀው ጠሚ ዓቢይ ገና ከወጣትነት ዕድሜው ጀምሮ እናት አገሩን በውትድርና በማገልገል፤ በህወሓት ወታደር ቤት ውስጥ ጭራሽ እንደ እሱ ዓይነት ሰው ይኖራል ተብሎ በማይገመትበት ሁኔታ ራሱን ለትልቅ ነገር በማጨትና በማብቃት ለዚህ ደረጃ በቅቷል። ጃዋር ያለፉት ገዥወች አደረሱብኝ ከሚለው የፈጠራ የበደል ወሬ እንዲሁም  አደረግኩት ከሚለው ትግል በላይ ጠሚ ዓቢይ በህወሓት ሰወች ከልጅነት የወታደር ቤት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከፍተኛ በደሎችን፣ ጭቆናወችን፣ ውጣ ውረዶችን አስተናግዷል። ጃዋር አደረግኩት ከሚለው የትግል አስተዋጽኦ በላይ ጠሚ ዓቢይና ጓደኞቹ ህወሓትን አንገት ለአንገት ተናንቀው አስወግደዋል። ለመሆኑ ከለውጡ በፊት ጀምሮ ከግድያ ሙከራስ ያመለጠው ስንት ጊዜ ነው? እውነት እናውራ ከተባለ እነዚያን አረመኔ ገዥወች ጉሮሮ ለጉሮሮ በመተናነነቅ ልካቸውን ከማሳየትና ዓይናቸው እያየ ሁሉን ነገር ከጥቅም ውጭ ከማድረግ በላይ ጀግንነት፣ ድፍረት፣ ህይወትን ያክል ነገር ያለ ስስት በማስያዝ የተደረገ ትግል ጃዋር ያደርገዋል ወይ? ጃዋር ጠባቂየ ተነሳብኝ በሚል በደረቅ ሌሊት እሪ ድረሱልኝ የሚል አስቂኝ ሰው አይደል እንዴ?
.
እንዲያው ለመሆኑ ማነን ነው ያለፉት ገዥወች ደረጃ እድገት የከለከሉት፣ መሆን የሚችለውን እንዳይሆን ያደረጉት፣ ከመንግስት ኃላፊነት ቦታ እያነሱ ከአንዱ ወደ አንዱ ያላጉት፣ ከወታደር ወደ ሲቪል መስሪያ ቤት፣ ከፌደራል መስሪያ ቤት ወደ ክልል፣ ከገለልተኛ ሕዝብ አገልጋይነት ወደ ኦህዴድ አባልና አመራርነት ያሻቸውን ያደረጉት ጠሚ ዓቢይን ወይስ ጃዋርን? ለመሆኑ ጃዋር የሆነው ምንድን ነው? ጃዋር መስዋእትነት የከፈለ ሳይሆን ትግሉ መስዋእት ሆኖ እሱን ለስኬት ያበቃው፣ በዚህም ተጠቃሚ ከመሆን በላይ ሊቆጣጠረው የማይችለው ዝና ያስገኘለት ነው። ባልተለመደ መልኩ ከባህላችንና ልማዳዊ ወጋችን በተቃራኒው የማይገባውን ራሱን ከፍ አድርጎ በመስቀል ከለማና አብይ እኩል መሪ ነኝ የሚል፣ ሁለተኛ መንግስት ነኝ የሚል እፍረተ ቢስና ይሉኝታ የሌለው ሰው ነው ጃዋር። ጃዋር ከአብይና ከለማ ጋርም እኩል የሚመደብ ሰው አይደለም፤ ሁለተኛ መንግስት እመራለሁ የሚለውም ቀደዳ ነው። እንግዲህ ባልሆነው ነገር ላይ እንደሆነ አድርጎ ሲያወራ ጥቂት እንኳ አይሰቀጥጠውም። በባህልና ወጋችን እንኳን ያልሆኑትን ነገር ቀርቶ የሆኑትን ነገር ቢሆንም እኔ እንዲህ ነኝ፣ እኔ እንዲህ አደረግኩ ማለት ይከብዳል ባይሆን ሌላ ሰው ይናገርልን እንጂ?
.
ለመሆኑ ጃዋር እንደሚደሰኩረው መስዋዕትነት ለመክፈልስ፣ ለፖለቲካ ትግልና ጉድጓድ ለመማስ፣ ኢትዮጵያን ለመሰለ አገር የተወሳሰበና በፈተና የተሞላ ፖለቲካ ለመቋቋም፣ ከሌሎች ጋር አብሮ የመስራት ባህርይና ቁርጠኝነት አለው ወይ?
.
እጅጉን የማደንቀው የነጻነት ታጋይ ኤርኔስቶ ቼጉቬራ ኩባን ነጻ ካወጡ በኋላ ከካስትሮ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እየተቀዛቀዘ ሲሄድ የሌሎች አገሮችንና ቡድኖችን የነጻነት ትግልን በመደገፍ ለመታገል በመወሰን ወደ ኮንጎ ለመንቀሰቀስ ይወስናል። በመጨረሻም ወደ ኮንጎ በመሄድ የኮንጎ አማጽያንን በመቀላቀል ለትግል ጫካ ይገባል። ጫካ ከገባ በኋላ የአማጽያኑን መሪ ካቢላን አገናኙኝ ብሎ ሄዶ ይገናኘዋል። ኤርኔስቶ ካቢላን ያገኘው እጅግ በሚያስገርም ሁኔታ በአራት እንስቶች ተከቦ፣ በማርቲን እየታሸ፣ ያሻውን እየበላ፣ እየጠጣ የተቀማጠለ ኑሮ እየኖረ የነጻነት ትግል መሪ ሳይሆን የጫካው ንጉሥ መስሎት ነበር። ኤርኔስቶም በተመለከተው ነገር ተስፋ ቆርጦ በእዚህ መልኩ የነጻነት ትግል አይደረግም በማለት ፊቱን አዙሮ አማጽያኑን ትቶ ወደ ኩበሰ ተመለሰ። አንድ ወቅት አንዳርጋቸው ጽጌ እኛ ጫካ የገባነው የምንፈልገውን ነጻነት ለማግኘት ምን ያክል ቁርጠኛ እንደሆን ከማሳየቱ በላይ የትግላችን መራርነት ወያኔወች እነሱ ከቤተመንግስት ምቾትና ድሎት ህይወት ወጥተው መቼውንም የማያደርጉትን ነገር እኛ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ህይወት በቃን ብለን እጅግ አስቸጋሪና ፈታኝ በሆኑት በኤርትራ በረሃወች ድንጋይ ተንተርሰን፣ መሬት ላይ ተኝተን እንደምንታገል ስለሚያውቁ ከሚገባው በላይ ፍርሀት ላይ ናቸው፣ ወሬያቸውም፣ ቅዥታቸውም ስለ እኛ ነው ብሎ ነበር።
.
እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ግራ ቀኙ አስቸጋሪ በሆነ ፖለቲካ ውስጥ ጃዋር እንደ ካቢላ በግራና በቀኝ ተከቦ፣ የ40 ሚሊዮን ብር ቤት ውስጥ እየተኖረ፣ በሁለት V8 ግራና ቀኝ ታጅቦ፣ በአጀብና በወጀብ እየተንቀሳቀሱ እንዴት ነው ፖለቲካ የሚሰራው? እንዴት ነው ጫት እየቀረጠፉ በመዋል አመሻሽ ላይ ደግሞ ሁለት ጠርሙስ ቮድካ በመቸለስ እንዴት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካ ተሳታፊ ሆኖ ተጽእኖ የሚፈጠረው? እንዴት ተብሎ ነው ትግልስ የሚደረገው? ነገሮችን በአፍ ሲያወሯቸው ቀላል መስለው ይታያሉ ስንተገብራቸው ግን ፈታኝነታቸው የሚታወቅ ነው።
.
ፖለቲካ ሰው ጋር አብሮ መስራትና ማሰራት የሚጠይቅ ዘርፍ ነው። ጠሚ ዓቢይ በዚህ በኩል ያላቸው ባህሪ የሚደነቅ ነው። ባለሙያን በማክበርና እንደ ባህሪይውና ምግባሩ በማሰራት በኩል ይመሰገናሉ። ስልጣን ከያዙ በኋላ ፍርድ ቤት ላይ፣ ምርጫ ቦርድ ላይ፣ ሰብአዊ መብት ላይ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ዘርፎች ላይ ያደረጉትን አይተናል። መለስ ዜናዊ እንደሚያደርገው እከሌ ይበልጠኛልና ላርቀው የሚሉ ጨለምተኛ ሰው አይደሉም፤ ከበላይና የበታችነት እይታና ግንኙነት ይልቅ ቀለል ባለ መልኩ የጓደኝነት ስሜት በመፍጠር ስራ የሚሰሩና የሚያሰሩ ሰው እንደሆኑ በቅርበት ከሚያውቋቸው ሰወች ለመረዳት ችያለሁ። ከዚህም በላይ በድርድር የሚያምኑ ሰጥቶ በመቀበል መርህና ቅንነት የሰፈነበት ሰላማዊ ምክክርን የሚጠቀሙ ሰው ናቸው። ይህ ባህሪያቸው በአገር ቤት የሚፈለገውን ያክል አድማጭና ተከታይ ኖሮት ለውጥ ባያስገኝላቸውም በጎረቤት አገራትና በቀጠናው ከፍተኛ ውጤት አስገኝቷል። በዚህም ምክንያት እጅግ ከፍተኛ ክብር የሚሰጠውን የኖቤል ሽልማት ሊቀዳጁ በቅተዋል። ጃዋር መሀመድ እንግዲህ እንዲህ ዓይነት ባህሪ ያለውን ሰው ነው እሱ በሚታወቅበት እኔ ብቻ ባህሪው ፖለቲካ ላይ በመሳተፍ ውጤታማ እሆናለሁ የሚለን።
.
ጃዋር ኦ ኤም ኤን ላይ ከጅምሩ አንስቶ እስካሁን ድረስ የሚያደርገው ነገር በሙሉ የእሱን ማንነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። የቴሌቭዥን ጣቢያውን አብረው ከመሰረቱት ሰወች መካከል ከጋዜጠኛ ጀምሮ እስከ ቦርድ አመራር ድረስ ሁሉንም ተራ በተራ አሰናብቶ ብቻውን የቀረ መስራች ሆኗል። ከአንድ ወይም ከሁለት ሰው ጋር ቢሆን ችግሩ ወደ ሰወቹ እናሳብብ ይሆናል ነገር ግን ከዚያ ሁሉ ሰው ጋር የተጋጨና ሰው ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችል ቅንጣት ባህሪ የሌለው ሰው ነው። ከጓደኞቹ ጋር ያለውም ግንኙነት ተመሳሳይ ሲሆን እና በረባ ባልረባው ነገር እየተጋጨ የሚኖር ነው። ጃዋር ከራሱ ውጭ ማንንም ማየት የማይፈልግ ሰው እንደሆነ የሚገባችሁ ልክ እንደ መለስ ዜናዊ ከአጠገቡ ደህና አቅም ያለው ሰው እንኳን አያቀርብም። በዙሪያው ያሉ ሰወች በሙሉ ከአሽከርነት ውጭ ሌላ ሚና የላቸውም። በጣም የሚያስገርመው ጃዋር ለቴሌቭዥን ጣቢያው ምክትል እንኳን አድርጎ ያስቀመጠው ሰው የለውም። ሁሉን አድራጊ ሁሉን ፈጣሪ የሆነ ህግ የማይገዛው ሰው ነው፤ የመንግስትን ፕሮቶኮል አሰራር እንኳን የማይረዳ ሁሉን ነገር ከህግና ሥርዓት ውጭ ለማድረግ ወደኋላ የማይል ነው።
.
የኦሮሞን ሕዝብ ታሪካዊ የፖለቲካ ትግል ምላሽ እየሰጠ ያለው ማን ነው?
.
ኦነግ በሽግግር መንግስቱ ጊዜ ከተባረረ በኋላ ሲያነሳ የነበረው የመገንጠል ጥያቄ በራሱ ከፍተኛ አመራሮች ነቀፌታ ስለደረሰበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሸረሸረ መጥቶ መገንጠል የተሸነፈ አስተሳሰብ ከሆነ ውሎ አድሯል። ከመገንጠል ውጭ ያለው የኦሮሞ ፖለቲካ ደግሞ ኦሮሚያ የኢትዮጵያን ሰፊ ቦታ የሚያካልል እና በርካታ ሕዝብን ያቀፈ አካባቢ ከመሆኑ የተነሳ ሕዝብ ከዚህ ቀደም አገዛዞች ሲያደርጉት ከነበረው የመብት ረገጣ እና ጭቆና ነጻ በመውጣት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ማዕቀፍ ውስጥ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ልዩ ልዩ ማዕቀፎች ሕዝቡ በወርድና ቁመኑ ልክ ተጠቃሚ፣ ተገልጋይ እንዲሆን ባህልና ቋንቋው እንዲጎለብት እንዲሁም የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው በማድረግ ዕድገትና ለውጥ ለማምጣት መስራት ላይ ያተኮረ ነው። በዚህ ረገድ በአዴፓና ኦዴፓ አመራሮች ትብብርና ስልታዊ የፖለቲካ መደጋገፍ የተገኘው የፖለቲካ የበላይነት ያለፈውን ዘመን የጭቆና መንበር ከማላቀቅና ሕዝቡ ነጻነት እንዲያገኝ ከማድረግ በላይ ያለፉት 50 ዓመታት የኦሮሞ ሕዝብ የፖለቲካ ትግል ምላሽ የሚያገኝበት ዕድልን አስገኝቷል።
.
ይህን በብርቱ ትግል የተገኘን ታላቅ የፖለቲካ ድል ወደ ልማት እድገት በመለወጥ የኦሮሞ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በአንድነትና በእኩልነት ተባብሮ የሚፈልገው የስኬት ደረጃ ለመድረስ ሥራወች እየተሰሩ ይገኛሉ። ታዲያ ጃዋርና መሰሎቹ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄና ትግል ተጠለፈ የሚሉት ከኦሮሞ ሕዝብ ታሪካዊ የፖለቲካ ትግልና ጥያቄ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ የሚፈልጉት ባለመሆኑና እንደተመኙት አዛዥ ናዛዥ Informal Governor ለመሆን አለመቻላቸውና ጠሚ ዓቢይ ደግሞ ለዚህ ያልተገባና ያልተገራ ፍላጎት የማይመቹ ሰው በመሆናቸው ነው። እንደሚታወቀው የኦሮሞ ሕዝብ የዘመናት የፖለቲካ ጥያቄወች ከኦሮሞ ማኅበረሰብ በወጣውና በመሪነት መላ ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ባለው ጠሚ ዓቢይ አህመድ የሚጠለፉበት ምክንያት ሊኖር ባይችልም እንደ ጃዋር ዓይነት የግል ፍላጎታቸውና ምኞታቸውን ማኅበረሰባዊ አውድ በመፍጠር የፖለቲካ ሽርሙጥና ለመፈጸም ጧት ማታ እየተጉ ይገኛሉ። ይሁንና ሁሉም ነገር የሂደት ውጤት ነውና እያንዳንዱ ነገር በጊዜ ሂደት ሕዝብ የሚረዳው ይሆናል።
.
ጠሚ ዓቢይ የኢትዮጵያ መሪ በመሆናቸው ለኦሮሞ ሕዝብ  የሚያስቡት፣ የሚያልሙት፣ ሊፈጽሙለት የሚፈልጉትን ነገር በሙሉ የሚገልጹትና የሚሰሩት በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ነው። ለኦሮሚያ፣ ለኦሮሞ እያሉ ስሜት ቀስቃሽ ኮርኳሪ ንግግሮችን ማድረግ ቀላል ነገር ቢሆንም ለሕዝቡ ዕድገትና ብልጽግና ማምጣት ግን ፈታኝና ትጋት የሚጠይቅ ነው። የኦሮሞን ሕዝብ ኮርቻ አድርገው መሪ ሆነው ሊፈናጠጡ ያሰፈሰፉ ሰወች በሙሉ አንገብጋቢ ከሆነው የኢኮኖሚና ልማት ጥያቄን በምን መልኩ ፈትተው ሕዝቡን ተጠቃሚ ሊያደርጉ እንደሚችሉ አስበውም ጉዳያቸውም ሆኖ አያውቅም። ከዚያ ይልቅ እነሱን የሚያስጨንቃቸው በኢትዮጵያ ቤተመንግስት ውስጥ የሚገኘው የኦሮሞ ቁጥር ነው፤ መሪው ኦሮሞ በሆነበት ቤተመንግስት ውስጥ የሚገኘው የኦሮሞ ቁጥር ለሕዝቡ ዳቦ ይሆነው ንፁህ ውሀ ባናውቅም እያንገበገባቸው ጧት ማታ በአገኙት አጋጣሚ የሚያለቅሱበት ጉዳይ ሆኗል። በቤተ መንግስት ባለሟል የብሄር ስብጥር ቢሆንማ እነዚህ ወገኖች ተጨቁነናል በሚሉት በንጉሣዊ ሥርዓት ወቅት ከላይ አስከ ታች ኦሮሞ ነበር። ጃዋር መሀመድ በ2020 ምርጫ እወዳደራለሁ እያለ ቢፎክርም ከግለሰቡ ባህሪና ተግባር አንጻር በፓርቲ ደረጃ ሊሰራ የማይችል፤ ከሌሎች ጋር በመተባበርና በመከባበር መሰራት ያለበትን የፖለቲካ ሥራ በግሉ ሁሉንም ነገር ለማድረግ ሲሞክር ወለል ብሎ የሚቀር ነው። ከሁሉም በላይ የአሜሪካ ዜግነትን ለመመለስ በራሱ ከዓመት በላይ ጊዜ የሚፈጅ ሲሆን ዜግነት ቢመለስለት እንኳን የኢትዮጵያ ምርጫ ህግ የሚጠይቃቸውን መስፈርቶች ለሟሟላት መቻሉ አጠራጣሪ ነው።
Filed in: Amharic