>

ብልፅግና ፓርቲ ለቄሮ ኤታማዦር ሹም የቀረበ ገፀ በረከት ይሆን?!? (ሳምሶም ጌታቸው)

ብልፅግና ፓርቲ ለቄሮ ኤታማዦር ሹም የቀረበ ገፀ በረከት ይሆን?!?
ሳምሶም ጌታቸው
* ጃ-warም የንግግሮቹ ድፍረትና እርግጠኝነቱ የመነጨው “አጥብቆ ያሰረ ዘቅዝቆ ይሸከማል” እንደሚባለው፣ ውስጥ ለውስጥ በዘረጋው የደረጀ ኔትወርክ ጥንካሬ በመተማመን እንጂ ተራ ፉከራ አለመሆኑን በግልፅ እየታየ ነው!
ከምናየው፣ ከምንሰማው፣ ከምንታዘበው ተነስተን ስናስበው፣ አሁን ባለው የኃይል አሰላለፍ፣ ጃ-war ከፈለገ በሰዓታት ውስጥ ቤተመንግስት ገብቶ ጠ/ሚ ዓብይንና ባልንጀሮቻቸውን ከስራ ማሰናበት ይችላል። ጃ-war ይህን ከማድረግ የሚያስተጓጉለው ነገር ቢኖር፤ 1ኛ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለመፈንቅለ መንግስት ዕፈፅሞ ውቅና የማይሰጥበት ጊዜ ላይ መገኘታችን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በሀገር ውስጥ ሊነሳበት የሚችለውን የተቃውሞ ግርግር ለማስቀረት በማሰብ ነው።
ስለዚህ ጃ-war ሁለቱንም ፈተናዎች በቀላሉ ለመሻገር በምርጫ ድራማ ውስጥ ማለፍን ይመርጣል። በዚያ ሂደት ውስጥ በአሸናፊነት ለመውጣት ደግሞ በእስከ አሁኑ የዘረጋውን ኔትወርክ ይበልጥ በማስፋትና በማጠንከር መንገዱን እንደሚጠርግ አያጠራጥርም።
ይህ ሁሉ እያለ፣ የሰሞኑ የኢሕአዴግ ተዋህጃለው አስቂኝ ድራማ ለጃ-war ሰፊ የመጫወቻ ሜዳ የሚያመቻች ገፀ-በረከት አድርጎ መውሰድ ይቻላል። በብሔር ማንነት የተከፋፈሉ ክልሎችና ይህን አካኼድ የሚመራ፣ የሚያስፈፅም እና የሚያስገድድ ሕገ መንግስትና የመንግስት አወቃቀር ይዞ፣ በአንድ ወጥ ሀገራዊ ፓርቲ መንግስት እመራለሁ ማለት የክ/ዘመኑ አስቂኝ የፖለቲካ ድራማ ነው።
ሕዝቡ በዓመታት ግፊትና ቅስቀሳ የጎሳ ብሔርተኝነቱ ጫፍ በደረሰበት፣ ሁሉም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማኅበራዊ መስተጋብሮችና ዕሴቶች ከብሔር አንፃር በሚመዘኑበት፣ በተጨባጭም የስልጣን ቅርምቱም ሆነ ሹም ሽረቱ በብሔር፣ በጎሳ በተተበተበት፣ እጅግ ብዙ የተወሳሰቡና ያልጠሩ፣ የሕግና የፖለቲካ ሒሳቦች ባልተወራረዱበት በዚህ ሰዓት፣ ሰለ ሀገር አቀፍ ፖለቲካ ፓርቲ ላውራ ቢባል፤ በብሔር በተከፋፈለው ሕዝብ ዘንድ ከመናቅ፣ ከመጠላትና ከመተፋት የዘለለ ውጤት አያስገኝም። ስለሆነም አዲሱ ውህድ ፓርቲ በየክልሎቹ ከፍተኛ ሽንፈትን መከናነቡ አይቀርም። ያ ደግሞ ጃ-war በአቋራጭ ለሚያልመው የመጨረሻው ግብ በሩን ወለል አድርጎ ይከፍትለታል።
ለነገሩ ሰሚ አልተገኘም እንጂ ጃ-war ደጋግሞ ዕውነቱን ተናግሯል፦
 “ሰዉ ዝም ብሎ ይቃዣል እኔ ከፈለኩ አዲሳባን በ24 ሰአታት ውስጥ በቁጥጥር ስር ማዋል እችላለሁ!”
“ጠ/ሚሩ ፈፅሞ የብቃት ችግር አለባቸው!”
“ኢትዮጵያ ሁለት መንግስት አላት!” 
በማለት ለአብይ መንግስት ያለው ጥግ ይደረሰ ንቀት ከማሳየቱም በላይ ለደጋፊዎቹ የአቅሙን ልክ አሳይቷል። ለእኛ ለተቃዋሚዎቹም ከህግም በላይ አድራጊ ፈጣሪ መሆኑን አሳይቷል።
አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን በየትኛውም ሀገርም ሆነ የፖለቲካ ሥርዓት፣ ስልጣን የያዘን አካል እጉያው ስር ሆኖ በዚህ መጠን ሊገዳደረው አይችልም። ጃ-warም የንግግሮቹ ድፍረትና እርግጠኝነቱ የመነጨው “አጥብቆ ያሰረ፣ ዘቅዝቆ ይሸከማል” እንደሚባለው፣ ውስጥ ለውስጥ በዘረጋው የደረጀ ኔትወርክ ጥንካሬ በመተማመን እንጂ ተራ ፉከራ አለመሆኑን በግልፅ እየታየ ነው።
ይሄ ሁሉ ሲሆን ጠ/ሚ ዓብይና ጓዶቻቸው ግን በቲቪ ብቅ እያሉ የሚሰጡት መግለጫ፤ ሌላ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ያላቸው እንጂ በዚህ ሁሉ ሥጋት ውስጥ የሚገኙ አይመስሉም። ውሳኔዎቻቸውና መግለጫዎቻቸው ሁሉ ወቅቱን የማይመጥኑና ትርጉም የለሽ ሲሆኑ እየታዘብን ነው። በዚያ ላይ የጠ/ሚው ቋሚ ደጋፊዎችም እንዲሁ ዓይናቸውን የጨፈኑ፣ ጆራቸውን የደፈኑ መሆናቸው ያስገርማል። እናም ጥያቄው፣ በጋራ ቆመን ሀገራችንን ለመታደግና ተገቢውን ግፊት በጠ/ሚ ዓብይ ላይ ለማሰማት፤ ስንት ወጣቶች ሲሞቱ፣ ስንት ንብረት ሲወድም፣ ወደ ቤተመንግስቱ የሚገሰግሰው አካልስ ስንት ሜትር ሲቀረው ይሆን የምንነቃው?
Filed in: Amharic