>
5:13 pm - Thursday April 19, 7674

ግልፅ ደብዳቤ ለኦሮሞ መኳንንት (መስከረም አበራ)

ግልፅ ደብዳቤ ለኦሮሞ መኳንንት

 

መስከረም አበራ

 

ይህን ጦማር ፈቃዳችሁ ሆኖ እንድታነቡ ስፅፍ አስቀድማችሁ፣ ምናልባትም ርዕሱን ብቻ አይታችሁ “ይህች ነፍጠኛ የኦሮሞ ጥላቻዋ ተነሳባት” የምትሉ አትጠፉም፡፡ ይህ ቅድመ-ፍርዳችሁ ጊዜየን ወስጄ የምፅፈውን ፅሁፍ እንዳታነቡ እንዳይከለክል ስል ብቻ ማንነቴ እናንተ እንደምታስቡት እንዳልሆነ ለመግለፅ እገደዳለሁ፡፡ እኔ ከኦሮሞ እናት እና ከአማራ አባት የተወለድኩ ጎጃም ውስጥ ያደግኩ ሰው ነኝ፡፡ ስለዚህ ኦሮሞ እጠላለሁ ማለት እናቴን እጠላለሁ ማለት ነው፡፡ እናንተም ኦሮሞ እንደምጠላ የምታስቡት እናንተ የምትጠሉት “ነፍጠኝነት” ሁለመናየን የሞላ ነጠላ ማንነቴ ስለሚመስላችሁ ነው፡፡ የምትጠሉትን ማንነት ይዤ በመገኘቴ ሳቢያ የእናንተው ችኩል ጥላቻ እኔም ኦሮሞ እንደምጠላ እርግጠኛ ያደርጋችኋል፡፡

ከኦሮሞ እናት እንደተወለድኩ እየነገርኳችሁም ኦሮሞ እንደምጠላ በማስባችሁ የምትቀጥሉ ሳትበዙ አትቀሩም፡፡ የዚህም ምክንያት ያለው እናንተው ጋር ነው፡፡ በእናንተ ጎራ የፖለቲካ ባህል የእናቱ አማራ መሆን የአማራ ጥላቻውን የማያስተነፍስለት፣ አማራ እስከሆነች ድረስ እናቱን ለመጥላትም የማያመነታ አስፈሪ እሳቤ የያዘ ሰው እንዳለ ከአማራ እናት ተወልዳችሁም በሚዲያ ወጥታችሁ ስለዚሁ መከረኛ የአማራ ህዝብ ከምታወሩት ነገር እንደማስተውል፤ እንደምታዘባችሁም መካድ አልፈልግም፡፡ የሆነ ሆኖ እኔ ኦሮሞ የማልጠላው ኦሮሞ እናት ስለወለደችኝ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቅስ ማመልከቻ አስገብቼ፣ በብቃቴ ተወዳድሬ ከኦሮሞ እናት/ከአማራ አባት አለመወለዴን ስለማውቅ ደክሜ ባላመጣሁት ማንነቴ ላይ ተመርኩዤ መውደድ መጥላቱ ልክ ስለማይመስለኝ ነው፡፡ ይልቅስ ታላቅ ዕድል እና ክብር የሚመስለኝ ሰው ሆኜ መፈጠሬ ነው፡፡

ሰውነት ክቡርነት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ስለዚህ ሰው ሁሉ እንደእኔው ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ክቡርነት ይሰማዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኔ ሰውነቴ ክቡር ስለሆነ መከበር አለብኝ ብየ እንደማስበው ሌላውም ስለራሱ እንዲሁ ይሰማዋል ስል በጥብቅ አምናለሁ፡፡ስለዚህ በሰው ልጆች ላይ ክብር እንዲጓደል፣ እኩልነት ድርድር ውስጥ እንዲቀርብ አልሻም፡፡ ሰዎች ሁሉ የሚጋሩት ድንቅ ማንነት ሰውነት ነው ብየ አጥብቄ አምናለሁ፡፡ የሰብዓዊ መብት የመብቶች ሁሉ ቁንጮ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ሌላው ማንነት ብዙና ተለዋዋጭ ነውና የፖለቲካ ዕምነት ይሆን ዘንድ አቅም የለውም፡፡ ይህን የምለው እኔ ብቻ አይደለሁም፡፡ ዓለም እያሳደደ የሚያነባቸው፣ እየተደመመ የሚያደምጣቸው ምሁራን ጭምር እንጅ!

ማንነት አንድ አይደለም፡፡ ይልቅስ እጅግ በርካታ፣ በጣም ውስብስብ፣ አንዱ ካንዱ የማይበልጥ፣ ቋሚነት የሌለው ነገር ነው ይላሉ እኔ መፅሃፎቻቻን ለማግኘት የቻልኳቸው ታዋቂዎቹ ምሁራን ፍራሲስ ፎኩያማ እና አማር ቲያሲን በመፅሃፎቻው፡፡ እናንተም በዘውግ ክር ብቻ የሰፋችሁት ፖለቲካ ሃገሪቱን ወደ ገሃነም ይዞ ሲምዘገዘግ ስታዩ ይህ ሚስጥር ዘግየት ብሎም ቢሆን ምን ያህል እንደገባችሁ እርግጠኛ ባልሆንም የገባችሁ ይመስላል፡፡ መገለጫው ደግሞ በዘር ግንባር ተቀናጅቶ በየግንባሩ እንደ ፍየል ሊዋጋ ትንሽ የቀረውን ግንባራችሁን ቀይራችሁ ውህድ ልታደርጉ እየሞከራችሁ መሆኑ ነው፡፡

በዚህ ውስጥ የኦሮሞ ፖለቲከኞችም ሚና ስላላችሁ ለመለወጥ መንገድ ለመጀመራችሁ አንድ ምልክት ተደርጎ ለመውሰድ ይቻላል፡፡ ግን ደግሞ ቃል በተግባር ይመዘናል፡፡ ወደ ተግባር ሚዛን ሲመጣ እናንተ የኦሮሞ ፖለቲከኞች በተግባር የምታደርጉት ድርጊት እና ሌሎች ወደ ውህደት እየተንደረደሩ ያሉ የግንባሩ አባል/አጋር ፓርቲዎች የሚያደርጉት ድርጊት የትየለሌ የተራራቀ ነው፡፡ አሁን እንደምታደርጉት ድርጊት ከሆነ ውህዱ ፓርቲ እመራበታሁ የሚለውን የሲቪክ ፖለቲካ ለመተግበር ቀርቶ ከፅንሰሃሳቡ ጋር ለመላመድ ራሱ ቀላል የሚሆንላችሁ አይመስልም፡፡

ከእናንተ ጋር ሲወዳደሩ የግንባራችሁ አባል/አጋር የሆኑ ሹማምንት የሲቪክ ፖለቲካን ለመልድ የሚያሳዩት ዝንባሌ እጅግ ሚዛን የሚደፋ ነው፡፡ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል በፊውዳል ዘመን ቀርቶ አሁን ብሄረሰቦች ከእስርቤተ ተፈቱ በተባለበት የህወሃት/ኢህአዴግ ዘመን እንኳን የሶማሌን ክልል የሚመራው ፓርቲ በሃገሩ ዋነኛ የፖለቲካ ውሳኔዎች ላይ ድምፁን ለማሰማት ከእናነተ እኩል ሲሰየም እንዳልኖረ እኔ ለእናንተ አልነግርም፡፡ እናንተ ከዘውጋችሁ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሾም እንቅልፍ አጥታችሁ ስታሰሉ፣ የፓርቲያችሁ ሊቀመንበር ለማ መገርሳ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል ስላልሆነ ይህ እንቅፋት እንዳይሆን ዶ/ር አብይን ሊቀመንበር አድርጋችሁ የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ወንበር እንቅልፍ አጥታችሁ ስታማትሩ የሱማሌ ክልል ተወላጅ ግን ቀለል ያለ የፌደራል ሚኒስትር መስሪያ ቤት ሚኒስትር ለመሆንም እንዳይችል ሆኖ ኖሯል፡፡

ይህ የሆነው እናንተም በተቀበላችሁት፣ አካል ሆናችሁ ስትሰሩበት በኖረው አግላይ አሰራር በመሆኑ በዚህ ህወሃት ብቻ አይወቀስም፡፡ ከሁሉ የሚገርመኝ “ዲሞክራሲያዊ” የሚለውን ስም ባንጠለጠለው ግንባራችሁ ውስጥ አባል ሆናችሁ፣ በዚህ የሰለጠነ ዘመን የምትኖሩ እናንተ ይህ መሆኑ ሳይጎረብጣችሁ ራስ ደህና ብላችሁ እየኖራችሁ ፊውዳሉ ሚኒሊክ በፊውዳል ዘመን ሰብዓዊ መብት አላከበረም ብላችሁ መውቀስ ከጀመራችሁ ቀን የማይበቃችሁ፣ ሰሚ ይሰለቻል ብላችሁ የማታስቡ መሆኑ ነው፡፡ምኒሊክ በኦሮሚያ ያደረገውን ሁሉ በሶማሊ ክልል አድርጓል፡፡ ብሄረሰብ ከእስር ቤት ተፈታ ሲባል ግን የሶማሌ ኢትዮጵያዊያን እኩል ኢትዮጵያዊ የመሆኑ መብት እንደ ታስሮ ቀርቷል፡፡ ከአሳሪዎቹ አንዱ እናንተው ናችሁ! የሶማሌ ኢሊቶች ይህን ስለማያውቁ አይደለም አሁን ሃገር አዲስ የጉዞ ምዕራፍ ትያዝ ሲባል እጃቸውን ሰብስበው፣ ራመድ የማለት ፖለቲካን ለመስራት ግንባር ቀደም ሆነው የተሰለፉት፡፡ በዚህ የትየለሌ በልጠዋችኋል!

እናንተ ቤተ-መንግስት የገባችሁበትን ሩጫ ስትሮጡ እግራቸውን ታስረው የኖሩ፣ ይህንንም አሳምረው የሚያውቁ የሶማሌ ልሂቃን ትናንትን ትተው በዛሬ ውስጥ ነገን ለመስራት ደፋ ቀና የማለቱን ስራ ክልላቸውን ሰላማዊ በማድረግ ጀምረዋል፡፡ህዝባቸው ቀስት እና ጦርን ጥሎ፣ ያለፈውን ችላ ብሎ ወደፊት እንዲራመድ አስተምረዋል፡፡ ከዚህ ያፈነገጠውን (ሄጎ የሚባለውን ገዳይ ቡድን) ዘር ከልጓም ሳይስባቸው አደብ አስገዝተው የሃገር ሰውን ሁሉ አጃኢብ አስብለዋል! ምሬት አብርሯቸው ጦር ያነሱ ብረት አንጋች የሶማሌ ሸማቂዎች ዛሬ መናኝ የሚያስንቁ የሰላም ሰባኪዎች ሆነዋል፡፡ ይህ ሁሉ ለምን ሆነ ከተባለ ዋናወን ወረታ የሚወስደው ክልሉን የሚመሩ መሪዎች እሳቤ መዋጀት ነው፡፡

እሳቤያቸው በመዋጀቱ “በክልላችን የጠፋው ጥፋት እኛኑ እንጅ ማንንም አይወክልም” ሲሉ የመታረም መጀመሪያ የሆነውን ፀፀት በህዝባቸው ዘንድ አሰረፁ፡፡ በጎሳ ተከፋፍሎ የኖረ ህዝባቸውን አንድ አድርገው ጭራሽ በሱማሌነታቸው ውስጥ ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን እንዲያስቡ መምራት ጀመሩ፡፡ ተሳካላቸው! በሚያስተዳድሩት ክልል በማንነቱ የሞተን ሰው ቤተ-ዘመድ ካሱ፣ የእምነት ቦታው የተቃጠለበትን ስንት እጥፍ አብልጠው ሰርተው፣በኢትዮጵያ ባንዲራ አሸብርቀው “እነሆ መፅናኛህ!” አሉ፡፡ ይህን ሁሉ ሲሰሩ ተግዳሮት ሳይኖርባቸው ቀርቶ አይደለም፡፡ ግን ከልብ አልቅሰዋልና እንባ አልገደዳቸውም፡፡ ራሳቸው ተለውጠዋልና ለህዝባቸው አዋጩን መንገድ መጠቆም አላቃታቸውም!

እናንተስ?ወገባችሁን ጠበቅ አድርጋችሁ ህዝባችሁን ከፅንፈኛ አክቲቪሰቶች እና ምሁራን ተብየዎች አስተምሮ ከመዋጀት ይልቅ ከፅንፈኞች የባሰ ፅንፈኛ የመሆን ውድድር ውስጥ ተዘፍቃችሀዋል፡፡ የቱ እውነተኛ ቀለማችሁ የቱ ማስመሰላችሁ እንደሆነ ለማወቅ ከመላዕክት ጋር ስብሰባ መቀመጥ ይጠይቃል፡፡ ራስን ሆኖ መውጣትን የመሰለ የድል በር የለም! ራሳችሁን ሁኑ፡፡ በአንድ ጊዜ እኛ ኢትዮጵያን በምንል ሰዎች ዘንድ አማላይ ለመሆምን፤ ኢትዮጵያን የማይፈልጉ ፅንፈኞች በሚሰብኩት የኦሮሞ ህዝብ ዘንድ የበለጠ ፅንፈኛ ሆኖ ለመቆጠርም የምታደርጉት መሰባበር መነኩሴም ኮማሪትም ለመሆን የምትፈልግን ሴት ያስመስላችኋል! በስተመጨረሻም ከሁለት ያጣ እንደሚያደርጋችሁ እወቁት፡፡ ይህ ነገር አሁንም ጀምሯችኋል፡፡

ስልጣን ስትይዙ ዘሩን ሳይቆጥር ራሳችሁን እንኳን እሲኪገርማችሁ ድረስ በደስታ የሰከረው ኢትዮጵያን የሚወደው ህዝብ ዛሬ ላይ የእግዜር እንግዳ ብሎ ገብቶ ሰርቆ እንደሄደ እንግዳ እየቆጠራችሁ ነው፡፡ያልሆኑትን በመምሰል መልቲነት እየጠረጠራችሁ ነው፡፡ ሁለተኛ ላይምናችሁ እየተማማለባችሁ ነው፡፡መታመን መወደድ የማይከብዳችሁ አድርጎ እየቆጠራችሁ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ያመጣው ልባችሁ የሚላችሁ እውነተኛ ነገር ምን እንደሆነ ቃል ከተግባር ፈትኖ ለማረጋጋገጥ እጅግ የምታዳግቱ፣ ለመደገፍም ለመንቀፍም የማትመቹ በመሆናችሁ ነው፡፡ እባካችሁ የሆናችሁትን ሆናችሁ ኑ! ራስን መሆንን የመሰለ ውበት የለም፡፡

አፋችሁ ኢትዮጵያዊነትን እየሰበከ ተግባራችሁ ግን ሌላ ነው፡፡ ኦሮሞ ሳይሆን ኦሮሚያ ክልል የሚኖር ኢትዮጵያዊ አሰቃቂ ሞት፣ እንግልት፣ ስደት፣ የንብረት መቃጠልን በተመለከተ ትንፍሽ አትሉም፡፡ትንፍሽ ካላችሁም የመምሰል እና የመሆን ርቀታችሁ ከገመትነው በላይ በእጅጉ የተራራቀ መሆኑን ብቻ አስመስክራችሁ ከመድረክ ትወርዳላችሁ፡፡ የምትመሩት ክልል የህግ አስከባሪ አካል ግፍን በማስቀረት ፋንታ ዘውጉን አጥንቶ ግፈኛው የዘውጉ ሰው እስከሆነ ድረስ በግፍ ለመተባበር የማያመነታ መሆኑን እያወቃችሁ ባላየ ታልፋላችሁ፡፡ በል ሲላችሁም ገዳይ አስገዳይን የዘውጋችሁ ሰው ስለሆነ ብቻ “ወንድማችን፣ የአይን ብሌናችን” ትላላችሁ፡፡የስለት እና የድንጋይ ሞት አንሶባችሁ፣ የመንግስት ሃላፊነት ላይ ቁጭ ማለታችሁም እዳ ሳይመስላችሁ በአደባባይ “ለገዳይ መሳሪያ እናከፋፍላል” ስትሉ በኩራት ነው፡፡ ይህን ስትሉ አድማጭ ትናንት “ከኢትዮጵያ አልፈን አፍሪካን አንድ የማድረግ ህልም ታይቶን የሃገር አስተዳዳሪነት ተመኘን” ማለታችሁን የማመሳከር ችሎታውን ትዘነጋላችሁ፡፡ እንዲህ በመሆን እና በመምሰል መሃከል የሚያላጋችሁ መሆናችሁ ከመምሰላችሁ ስለሚበረታ ነው፡፡መሆናችሁ ክፉኛ የዘለቃችሁ ዘውገኝነታችሁ ነው፤ መምሰላችሁ ደግሞ ሌላ!

መሆናችሁን የተቆጣጠረው ዘውገኝነታችሁ የኦሮሞን ህዝብ በአጭር ጊዜ ውስጥ በብርቱ ማስጠላት ውስጥ መክተቱ እንደ ዜጋ የሚያሳዝነኝ ነገር ነው፡፡መብለጥን ኢላማ የሚያደርገው እናንተም ከህወሃት የቀዳችሁት የእበልጣለሁ ባይነት፣ የማግበስበስ ክፉ አባዜ የኦሮሞ ህዝብ ማንነትም፣ ፍላጎትም፣ የትግል ግብም፣ አይመስለኝም፡፡ በህወሃት ቤት ያዳበራችሁትን ይህን ክፉ እሳቤ በህወሃት እልፍኝ ዝር ያላለው በደሳሳ ጎጆው ቁጭ ብሎ ግፍ ሲጎጭ የኖረው የኦሮሞ ህዝብ እሳቤ እንዴት ሊሆን ይችላል?እናንተ በህወሃት እልፍኝ የተማራችሁት በጤናማ መንገድ የስራ እድል አግኝቶ ከትንሽ ተነስቶ፣ ሰርቶ ጥሮ ግሮ የሚያድግበትን የመልካም አስተዳደር በር ብቻ ከመንግስት ከሚፈልገው አብዛኛ የትግራይ ወጣት ውስጥ የትግራይ መኳንንት ቤተ-ዘመድ የሆነውን ጥቂቱን ቆንጠር አድርጎ እርሱ አስቦት በማያውቅ ሁኔታ በአንድ ሌሊት ቱጃር ማድረግን ነው፡፡ ይህን ዕድል ያላገኘን ቤተ-ዘመድ ከትግራይ ጠርቶ አዲስ አበባ ውስጥ ኮንዶሚኒየም በገፍ ማደል እናንተም “ለኔ ባረገው” ስትሉት የኖራችሁት የህወሃት ፈሊጥ ነው፡፡ ይህ ያልሆነለት ደግሞ ያለ ይሉኝታ የነበረው እየተነቀለለት በየመንግስት መስሪያ ቤቱ ይሰገሰጋል፡፡

በህወሃት ቀንበር ስር የነበራችሁ፤ አሁን ደግሞ የህዋትን የፌደራል ስልጣን የተካው የእኛ ዘውግ ነው ብላችሁ የምታስቡ የኦሮሞ መኳንንት አብዛኞቻችሁ ትምህርት ቤታችሁ ህወሃት ስለሆነ ለህዝብ መስራት ማለት ከላይ የተጠቀሰውን የህወሃት ተግባር መድገም ይመስላችኋል፡፡ ህወሃትን እያያችሁም እያደነቃችሁም ስለኖራችሁ ስልጣን የፍርደ-ገምድልነት የይለፍ ይመስላችኋል፡፡ ህወሃትን ለመጣል ስትታገሉም የኦህዴድ ባለስልጣናት ሁሉ ተመሳሳይ አላማ ያላችሁ አልመሰለኝም፡፡ የህወሃትን ስልጣን ወለድ እብሪት ጠልተው ይንን ላለመድገም ስልጣን የተመኙ በጣም ጥቂት የኦህዴድ መኳንንት እንዳሉ መካድ ባይቻልም ብዙዎቻችሁ ግን ህወሃትን የታገላችሁት “የባለስልጣንነት እብሪቱ እኛ ላይምን ይመስላል?” ብላችሁ ለመሞከር ይመስላል፡፡ከህወሃት ጋር ያጣላችሁም “ግፍ ለመስራት እኔ ምን ያንሰኛል?” ማለት እንጅ “ለምን ግፍ ይሰራል?” የማለት ልህቀት አይመስለኝም፡፡ በመሆኑም በህወሃት መንገድ እየነጎዳችሁ ነው፡፡

ሰው ስንት አመት ቆጥቦ የሰራውን ቤት በድብቅ ለተፈናቃይ የኦሮሞ አርሶ አደር ሰጠን ብላችሁ ለዘውጋችሁ ዲያስፖራ ጭምር የማከፋፈል ማናለብኝነት ላይ የደረሳችሁት ህወሃት እዚህ ጥጋብ ላይ ለመድረስ የፈጀበትን የሃያ አመት እድሜ ሳትጠብቁ ገና በስድስት ወራችሁ ነው! ታዛቢያችሁ ብዙ ነው፡፡ ከመሬቱ በግፍ ለተፈናቀለ ኦሮሞ ምንም ቢደረግ ማንም የሚደግፈው ሰናይ ተግባር ነው፡፡በድብቅ መስጠትን ያመጣው በአርሶ አደሩ ስም የምትሰሩትን አድሏዊ አሰራር ለመሸፈን ነው፡፡ በግፍ የተፈናቀለ አርሶ አደር አንድ አባወራ ሆኖ ሳለ ነገ ጥረው ግረው ህይወታቸውን መግፋት ላለባቸው ልጆቹ ጭምር ሰው ቆጥቦ የሰራውን ቤት ማደል የግፍ ግፍ ነው፡፡

የተነሽው አርሶ አደር ልጆች እንዲህ ያለ ዛብ የለቀቀ ካሳ ይገባቸዋል ከተባለ እንኳን አዛኝ ቅቤ አንጓች ነኝ ያለ ሁሉ አዲስ ቤት ገንብቶ መስጠት እንጅ ስንት ዘመን ቤት አገኛለሁ ብሎ፣ ካልተረፈው ቆጥቦ የሰራን ህዝብ ቤት ማደል ነገ ወድቀህ ተነሳ የሚል ማጣትን የሚያመጣ የህወሃት አይነት የኪሳራ ጉዞ ነው፡፡ ዛሬ ህወሃትን ወድቀህ ተነሳ የሚለው የጠፋው እንዲህ ያለው ግፉ ተጠራቅሞ ከፅዋ በመምፍሰሱ ነው፡፡

እውነት ለመናገር ተነሽ የኦሮሞ አርሶ አደሮች ራሳቸው እንዲህ ያለ ዛብ የለቀቀ ካሳ እንዲካሱ የሚፈልጉ አይመስለኝም፡፡ ይህ የማግበስበስ፣አንዱን መቶ በመቶ አሸናፊ ሌላውን በዜሮ የቀረ ከሳሪ የማድረግ ስነ-ልቦና የኢህአዴግ ካድሬ ስነ-ልቦና እንጅ ዋናውን አጥቶ እንኳን ተመስገን የሚለው የኢትዮጵያ ደሃ ህዝብ መለያ አይደለም፡፡ የኦሮሞ ህዝብም ከዚህ የተለየ ስነልቦና ያለው አይደለም፡፡ ተነሽ የኦሮሞ አርሶ አደሮች ያጡትን የሚመጥን ካሳ ካገኙ እንደ ኢህአዴግ ካድሬ እኔ ብቻ በልቼ ልሙት የሚሉ አይደሉም፡፡ የኦህዴድ መኳንንትም ይህን የምታደርጉት ለአርሶ አደሮቹ አስባችሁ አይመስለኝም፤ ይልቅስ በህወሃት ስትቀኑበት የነበረው ስልጣን ወለድ እብሪት እጃችሁ መግባቱን የኔ ለማትሉት ዘውግ ማስመሰከራችሁ፣ የስነልቦና ቀወሳችሁን ማስተካከላችሁ እንጅ! በዚህ መሃል የኦሮሞን ህዝብ እያስጠላችሁት እንደሆነ እወቁ፡፡በጣም ጥቂት ለሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች በምታደርጉት አድሎ መላውን የኦሮሞ ህዝብ ክፉኛ እያስጠላችሁ እንደሆነ ማየት ያቃታችሁ የስልጣን ሰገነት ስለጋረዳችሁ ነውና እኔ መሬት ያለሁ ወገናችሁ ልንገራችሁ፡፡

ሌላ በስተመጨረሻ ሳልጠቅስ የማላልፈው ነገር በምትመሩት የኦሮሚያ ክልል የኦርቶዶክስ ተዋህዶን ቤተ-ክርስቲያን ለማጥቃት የሚደረገውን ፋታ አልቦ ጉዞ መግታት ሲገባችሁ ዝም ብላችሁ የምታዩት ነገር፣አንዳንዴም በተለይ የበታች ሹማምንቶቻችሁ ተባባሪ ሆነው የሚገኙበት አካሄድ፣ እናንተ አውራዎቹም የበታች ሹማምንታችሁን አድሏዊ ስራ ለማስቀየስ የምታደርጉት አስተዛዛቢ መጣጣር መጥፎ ነገር ይዞ እንደሚመጣ እንድታውቁ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ገዥዎቹ ሁሉ የሚውሉበትን ግፍ የሚያቃልለው በየዕምነት ቦታው ሄዶ ለፈጣሪው በመንገር ነው፡፡ ከነገስታት የሚመጣበትን ዘመናትን ያስቆጠረ ግፍ ችሎ የኖረው በየዕምነት ቦታው ሄዶ በሚያገኘው መለኮታዊ መፅናናት ነው፡፡ ይህ ብቸኛ የመፅናኛ አለት ከፈረሰበት መጽናናት የለውምና ቁጣው ይነድባችኋል፡፡ የህዝብ ቁጣ ምን እንደሚያደርግ ህወሃትን ጠይቁ! አደብ ግዙ …..በክልላችሁ የተፈጠረውን ከፍተኛ ስርዓት አልበኝነት አንድ በሉ፡፡

የዘውጋችሁ ሃይለኝነት መገለጫ፣ አንዳዴም የፖለቲካ ጉልበታችሁ ምንጭ አድርጋችሁ የምታስቡት የዘውጋችሁ ጎረምሶች የሚያነሱት ትርምስ ኦሮሚያ ክልል በሌላው ኢትዮጵያዊ ዘንድ እንደሞት ሃገር እንድትቆጠር እያደረገ እንደሆነ እወቁ፡፡ ለዚህ ትርምስ ባለድርሻውም ሆነ ተጠያቂው ሜንጫ እና አጣና ይዞ የሚወጣው ጎረምሳ ብቻ እንዳልሆነ ራሳችሁ በአደባባይ የምታወሩት ጠብ አጫሪ ንግግር ምስክር ነው፡፡ ኦሮሚያ የሞት ቀጠና ተደርጋ ስትወሰድ ደግሞ የኦሮሞ ህዝብም ከሞት እና ገዳይነት ጋር አብሮ እንደሚነሳ እወቁት! ጠባጫሪነትን በተፋው በዛው አፋችሁ እንደገና “የኦሮሞ አቃፊ ህዝብ ነው” የምትሉት ነገር አሁን አሁን ለኦሮሚያ ክልል እየተሰጠ ያለውን ጥሩ ያልሆነ መልክ አይቀይረውም፡፡ ሰው የሚያምነው የሚያየውን እንጅ የእናንትን ፕሮፖጋንዳ አይደለም፡፡ ወደዳችሁም ጠላችሁም በሃገራችን ካሉ ክልሎች ውስጥ እናንተ እንደምታስተዳድሩት ክልል እለት ዕለት የሚታመስ፤ ለሃገር ቀጣይነትም ስጋት እየሆነ ያለ ክልል የለም! ሌሎች ክልሎች የፀጥታ ችግር ቢገጥማቸው እንኳን በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩን ፈትተው ወደ ሰላማዊ የማስተዳደር ስራ ሲገቡ ይታያል፡፡ እናንተ ክልል ግን ሁከት ደምብ እየሆነ ነው፡፡ እናንተ ራሳችሁ የችግሩ ምንጭ ከሆነው የብሄር (ሃይማኖት) ፅንፈኝነት የተዋጃችሁ ብትሆኑ ኖሮ በክልላችሁ የሚታየው ችግር ከአቅማችሁ በላይ ሆኖ የሚያስቸግር ከቶውንም አይሆንም፡፡ በክልላችሁ የሰማኒያ ምናምን ሰው ሬሳ ሲታፈስ ብዙም ያልገረማችሁ ሰዎች ሌላ ቦታ ሁለት የኦሮሞ ተማሪ ሞተ ብላችሁ ለመግለጫ ስትጠራሩ ተስፋ ታስቆርጣላችሁ…..

ዛሬ ለውህደት እየተንደረደራችሁ ባለበት ወቅት፣እኔን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያዊ ከውህደታችሁ አንዳች የተሻለ ነገር ጠብ ይላል ብሎ በሚጠብቅበት ወቅት እዛው የምትረግጡት ነገር በእናንተ ተስፋ ማድረጋችንን ያጨነግፈዋል፡፡ የእናንት ዘውግ ሞት ከሌላው ሞት በልጦ ከተሰማችሁ ስንኖርም ከሌላው ዘውግ እንበልጣለን እያላችሁ እንደምትኖሩ ክርክር የለውም፡፡ ከዛሬው ያልታየ የመለወጥ ዝንባሌ ውህደቱ ሲመጣ ተብቆ እንደመንፈስ እንደማይወርድባችሁ የታወቀ ነው፡፡ ስዚህ ለውጣችሁን በተግባር እንየው፤ በጥቂት እንኳን ተለወጡ፣ ያመናችሁበትን ብቻ ስሩ፣ ሰውን ለማስደሰት ብላችሁ የምትሰሩት ስራ የፖለቲካ ህመማችንን አክፍቶ አሟሟታችንን መጥፎ ያደርግ ይሆናል እንጅ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ እውነተኛ ቀለማችሁን እንየው፤ ለእውነተኛው እምነታችሁ ብቻ ስሩ! ያኔ ባይሳካላችሁ እንኳን ለለውጥ ስትሰሩ የሆነ እንደሆነ ቢያንስ ታሪክ ይመዘግብላችኋል፡፡ለእምነታችሁ ድፈሩ፣ ፖለቲካ ማመቻመች እንዳለውም አውቃለሁ ግን ማስመሰል ከበዛው ደግ አይደለም፡፡አንድ በማስመሰል፤ አንድ በመሆን ሁለት ለመያዝ ስትሮጡ አንዷን ሃገራችንን እንዳታሳጡን!

Filed in: Amharic