>
10:35 pm - Sunday August 7, 2022

መደመር ወይስ መጨፍለቅ?! (ውብሸት ታዬ)

መደመር ወይስ መጨፍለቅ?!
ውብሸት ታዬ
   ባለፈው ሳምንት ለንባብ በበቃው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “የቀድሞ የጸረ ሽብር ሰለባዎች መንግሥትን ሊከሱ ነው” የሚለው ዜና ከወጣ በኋላ ስለጉዳዩ ብዙ ሰዎች ጥያቄ እያቀረቡ ነው። ወደዚህ ያደረሳችሁ ምንድነው? የሚሉም አሉ። የፍትሕ መበየን ጉዳይ ብቻ ነው። “የኋላውን ከረሱ የፊቱ የለም” ይባላልና እስኪ መለስ ብለን የተወሰኑ ነገሮችን እንመልከት። …
.
   የካቲት 7 ቀን 2010 ዓ.ም ከቀኑ 10:00 ሰዓት አከባቢ ነው። ለዓመታት በእስር የቆዩና ከተለያዩ የአገራችን አከባቢዎች የመጡ ዜጎች፤ ከዝዋይና ቃሊቲ እስር ቤቶች ተግዘው ለሦስት ቀናት በሰንዳፋ ፖሊስ ማሰልጠኛ ከቆዩ በኋላ ያለምንም የትራንስፖርት ወጪ በመገናኛ አደባባይ ላይ ተጣሉ።
   እነዚህ ዜጎች በደህንነት ሃይሎች እየታፈኑ የመጡት ከዋና ከተማችን እስከ 900 ኪሎ ሜትር ከሚርቁ አከባቢዎች ጭምር ሲሆን በቀላሉ ልትገምቷቸው በምትችሏቸው ምክንያቶች አንዳንዶቹ ከተያዙበት ቀን ጀምሮ ከቤተሰብ ጋር መገናኘት ያልቻሉ ነበሩ። በእጃቸው ላይ ቤሳ ቤስቲን አልነበረም። – ችግሩ ይህም ብቻ አልነበረም !
   በወቅቱ ለቤተሰብ ተጨማሪ ጭንቀት ላለመፍጠር መግለጽ አይፈለግ እንጂ በዚህ የረዥም ዓመታት እስር ብዙሃኑ በምግብ እጥረት እና በሌሎች መከራ በሚደሰቱት አሳሪዎች የሕክምና ክልከላ በአግባቡ ቆሞ መሄድ ራሱ ተአምር ነበር። – (ከእነ አሳፋሪ ነውራቸው ዛሬ ካልተዋሃዳችሁን እየተባሉ በአዲሱ የውህድ ፓርቲ ሂደት እሹሩሩ የሚባሉት እንግዲህ ይህን ግፍ በዜጎች ላይ ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ የነበሩት ናቸው።)…
   ከዚያ ቀደም ብሎ በምርመራ ወቅት የተፈጸመው ሰቆቃና አዕምሮ የሚያቆስል የሰብዓዊ መብት ጥሰት አስር በመቶው እንኳ አልተነገረም። ብዙዎች ናዚዎች በሰለባዎቻቸው ላይ እንደፈጸሙ ከተነገረው የምርመራ መንገድ ባልተለየ በፈጸሙባቸው አሰቃቂ ምርመራ ብዙ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በምርመራው ወቅት የደረሰባቸውን የአካል ጉዳት እንኳ ለማከም የቃሊቲው መንግሥት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ከነህመማቸው ለዓመታት ተሰቃይተው ወጥተዋል። መንፈሰ ጽኑው ዮሐንስ ጋሻው በኢትዮጵያውያን ወገኖቹ አጋርነት ነው ከእስር መልስ የተወሰነ ሕክምና ማግኘት የቻለው። እንደ ኢንጂነር ተስፋሁን ጨመዳ ያሉ የሕዝብ ልጆች ቃሊቲ ውስጥ በግፍ ተገድለዋል። ከአገር ውጪ ደግሞ ጀግናው ገዛኸኝ ነብሮን ተከታትለው በቅጥረኞች አስገድለውታል። በሕይወት መውጣት ከቻሉት አንዳንዶቹ ብዙ ዋጋ የከፈሉለትን የነፃነትን አየር በወጉ ሳያጣጥሙ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል።(ሊንኮቹን በቅደም ተከተል ይመልከቱ)
   በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት መጠየቅ ያለባቸው ከፍተኛ የማዕከላዊ ምርመራ ሃላፊዎች “አበጃችሁ!” የማለት ያህል ጎዳናዎችን ሞልተው በኩራት እየተንጎማለሉ ነው። – ‘መደመር’ ‘መጨፍለቅ’ የሆነ ይመስላል።
   ፍትሕ መበየን አለበት የምንለው ለዚህ ነው። ይቅር ማለት ብቻ ሳይሆን ይቅር መባባል ያስፈልጋል። ሁሉም ነገር በሥርዓቱ እና በወጉ መሆን አለበት።
   ከእስር እንደወጣን ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ተነጋግረን ከጠየቅናቸው ጥያቄዎች አንዱ ወሳኙ ነገር ጠ/ሚ/ሩ ሳይቀሩ የተፈጸመው “መንግሥታዊ አሸባሪነት” ነው ያሉለት የግፍ ገመና ፋይል እንዲዘጋ በሽብርተኝነት የፈረዱባቸውን የሕዝብ ልጆች ሰነድ እንዲያነሱ የሚል ነበር። ይህ በታሪክ ውስጥ የኢትዮጵያውያንን ማንነትና ምንነት የማይመጥን ነውረኛ ሰነድ ለፖለቲካዊ ትርፍ ሰባል እንደሚነሳ ቃል ተገብቶልን የነበረ ቢሆንም(ለአፈጻጸም አንድ ወር በቂ ነው ቢባልም) በመንግሥት ፈቃደኛ ያለመሆንና ለቀጣይ የአፈና መሳርያነት ለመጠቀም በሚመስል መንገድ ዛሬ ነገ እየተባለ እነሆ ሁለት ዓመት ዞሮ ሊገጥም ጥቂት ወራት ይቀራሉ።
   የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይ የሚበየነው በሕግ የበላይነት መረጋገጥ እንጂ ተጨማሪ ሹመቶችን በደል ለፈጸሙ በመስጠት ባለመሆኑ ይህን መስመር ለማስያዝ በአገር ውስጥም በዓለም አቀፍ ደረጃም ፍትሕ እንዲበየን የሚያስችሉ መንገዶችን ከምናከብራቸውና በፈታኙ ወቅት ከጎናችን ከቆሙ  የሕግ ባለሙያዎች ጋር በመነጋገር እየሄድንበት መሆኑን ለመግለጽ ያህል ነው።
   ሌሎቹ ጥያቄዎች በመስተዳድሩ በኩል በሳምንታት ውስጥ በቀላሉ ሊፈጸሙ የሚችሉ ጥያቄዎች የነበሩ ቢሆኑም ይህ ያልሆነበትን ምክንያት በቀጥታ መንግሥት መልስ እንዲሰጥበት ሕጋዊ አማራጮችን እየተከተልን የተባለው ነገር በእርግጥም መደመር ወይም መጨፍለቅ መሆኑን ለማረጋገጥ እንሞክራለን፤ ከጎናችን ሁኑ ! ቀጥሎ ያለው ሊንክ ከመረጃ ቲቪ ጋር በጉዳዩ ዙርያ የነበረን ቆይታ ነው።
https://www.facebook.com/184574221575426/posts/2887384277961060/ ቸር ቀን፤ ለሙስሊም ወገኖቻችን ደግሞ ዱዓችሁ የሚሰማበት ኸይር ጁምዓ ይሁንላችሁ !
እግዚአብሔር አገራችንን ይጠብቅ !
Filed in: Amharic