>
12:02 am - Thursday December 1, 2022

አደራ...አደራ... አደራ .... ታዬ ቦጋለ - (ኢልመ ደሱ ኦዳ)

አደራ…አደራ… አደራ ….

ታዬ ቦጋለ – ኢልመ ደሱ ኦዳ
ግልፅ መልእክት፦
1. ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ አሊ (PhD)
2. ለክቡር የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሣ (የክብር ዶክተር)
*
ከሁሉ በማስቀደም በነፍሳችሁ (ነፍስ እንጂ ነብስ አይባልም) ተወራርዳችሁ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስቸጋሪና ፈታኝ የሆነውን የወያኔ / ትህነግ ሥርአት ለመጣል ከሌሎች ጓዶች ጋር በመሆን ለተጫወታችሁት ፋና ወጊ እንቅስቃሴ የላቀ ክብር አለኝ። በዚያ እጅግ አስፈሪ ድቅድቅ ጨለማ ወቅት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ (ሊባል በሚችል ደረጃ) ከጸሎት እስከ ህይወት መስዋዕትነት አብሯችሁ ተሰልፏል።
*
ለማመስገን የፈጠነ ልቡና የሌላቸውና በሰላ ትችታቸው የሚታወቁት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ጭምር፤ የትመጣችሁ ሳያገብራቸው – በእናንተ ወደ ፖለቲካው ሜዳ መምጣት፦ ‘የፈጣሪ እጅ ጭምር አለበት’ በማለት በተገቢው የከበሬታ ወንበር ላይ አስቀምጠዋችኋል።
*
የአማራ ክልል ህዝብም እንኳን እናንተን ኢትዮጵያዊነት ከነፍስና ስጋችሁ ጋር ተሸምኖ በአደባባይ የደመቃችሁትን ይቅርና የዛሬን አያድርገውና በቀለ ገርባን ሳይቀር፦
 “መሪዬ ነው” ብሎ ተቀብሎ ነበር።
(ደግሜ በጉልህ የማሰምርበት፦ የኢትዮጵያ ህዝብ ምንጊዜም እንጀራው በአንድ በኩል አይወፍር፤ በሌላው ወገን አይሳሳ እንጂ ሁሉም ወገኑ በመሆኑ የሚያከብርህ በሰውነትህ ብቻ ነው። ለዚህ ነው “ኦሮሞው ለአማራው ደሙ እንጂ ባዳው አይደለም” የሚለው መፈክር ከኋላው በርካቶችን ያሰለፈው።)
*
ከሁሉም በላቀ ሁኔታ የምንወደው የትግሉ ወቅት ቄሮ ጀርባውን ሳይሆን ግንባሩን ለጥይት አረር / ለስናይፐር እየሰጠ ሲወድቅ፤ ከአንድ እናት አንጀት የበቀለው የአማራ ፋኖ የወንድሙ ደም መፍሰስ አላስችል ብሎት፦
“የፈሰሰው የኦሮሞ ደም የእኔም ነው!”
ለሚለው ህያው ቃሉ ታምኖ በግፈኛው የአግአዚ ቡድን በአንድ ቀን በባህርዳር ብቻ 59 ወገኖች የስናይፐር ሰለባ ሆነው የማይተካ ህይወታቸውን የገበሩት።
*
ይህንን ያህል ሐቲት (ሐተታ) የደረደርሁት ከዚህም አልፎ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኃላፊነት ሲመጡ እነማን እንደተቃወሙ፤ እነማን ደግሞ ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈው ለሞት ጭምር ጨክነው እንደተገኑ፤ ከእናንተ ይልቅ ለትግሉ ሜዳና ለስብሰባው አውድማ የቀረብሁ ሆኜ አይደለም። እንዳይዘነጋ ለማሳሰብ እንጂ!
*
ዛሬ ታዲያ፦ ወያኔ ትህነግ 24/7 በደም የተገኘውን ለውጥ ለማኮላሸት እየተጋች ባለችበት ወቅት፤ ኦነግ/ ሸኔ ከጃዋር = ብቻ ሁሉም ወገን ከዓለማቀፉ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይል ጋር ተሳስሮ ሀገራችንን እንደ ሶማልያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሊቢያ፣ የመን፣ ኮንጎ… ሊያፈራርሳት ቋምጦ ባለበትና የኢትዮጵያ ህዝብ ተስፋ እየቆረጠ ባለበት ፈታኝ ወቅት… የወገን ደም የሚተግነው አጥቶ – በአሰቃቂ ሁኔታ የደም አበላ ሀገሪቷን እያጠመቀ፥ የእምነት ተቋማት እንደ ጧፍ እየነደዱ ባሉበት ወቅት… ወሳኝ የኃላፊነት ሥፍራ ይዛችሁ እያለ፦ ህብረ-ብሄራዊነትና ፌዴራላዊ ሥርአት ቅንጣት ባልተነካበት = አንድነታችንን ግን ይበልጡኑ ሊያጠናክር በሚችለው “የብልፅግና ፓርቲ” አካሄድ አለመስማማትና ወደ መግለጫ ጭምር ማለፍ – የህዝባችንን ተስፋ ምን ያህል እንደሚያጨልም ይጠፋችኋል ብዬ አልወስድም።
*
እንደ አንድ ለሀገሩ ጧት ማታ እንቅልፍ እንደሚያጣ ዜጋ በሀገሬና በህዝቤ ተስፋ ባልቆርጥም በፖለቲካ መሪዎቼ እምነት አጥቼ ተስፋ ቢስ ልሆን ጠርዝ ላይ ቆሜያለሁ። በእኔ ስሜት ውስጥም አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ዐየዋለሁ።
“ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው!” የሚለውን ብሂል፦ ከሚተዉት ሳይሆን እድሜ ዘመን ከነፍስ ከተሰናኘ የፍቅር ሱስ ጋር አያይዤ የለመለመ ተስፋዬ ለምን ይጠውልግ?!
*
ኦቦ ለማ ሆይ፦ የአንተን ውለታ የሚዘነጋና ዛሬ ክፍተት የተፈጠረ ሲመስለው – ሠርግና ምላሽ ሆኖለት – በአማራና በኦሮሞ ስም የሚፅፈው ዲጂታል ወያኔ በቀደደልኝ ቦይ ፈስሼ – በልቡናዬ ሠሌዳ ሰገነቱ ላይ ቆሞ – ላላወርደው የገዘፈ ማንነትህን – በወጀብ ላወርደው ከቶውኑ አልሞክርም። የልጅ ያህል ተስፋ የማልቆርጥብህ የእድሜ ዘመን መሪዬ ነህ። አባ ኪያ፦ አቋምህ ወርዶ አንተም ከነእንቶኔ ጎራ ከተሰለፍህ ግን – ሰው ነኝና ከሀገሬና ከህዝቧ ቤተሰቤም አልበለጠብኝም፤ ገፍቶኝ ሸሽቼዋለሁና – የምር ሰጋለሁ። አባ ኪያ = እባክህ በቀደመ ፍቅራችሁ ከዶክተር ዓቢይ ጋር በ፦ Mediation ሳይሆን ፥ በ፦ Negotiation ቁጭ ብላችሁ ምከሩ (without the interference of third party)…
ወዳጆቼ፦ የሚያምረው እሱና እሱ ብቻ ነው። ወደ ሰማይ ተመልከቱ (When things go down, look up!)
ፈጣሪ ቢፈቅድና እኔም ተጨምሬ ብንወያይም ደስ ባለኝ!
(እምዬን እናቴን ሳስባት ለራሴ የተጋነነ ግምት ሰጥቼ ሳይሆን እዚያ ከፍታ ድረስ መምጣት እንደምሻ መብከንከኔን ለማሳየት ነው።)
*
እባካችሁ ይህንን ከ1960ዎቹ ጀምሮ ከዓለም የተሻለ ተሞክሮ ቀስሞ የሚታደገው አጥቶ ዛሬም በ6,000 ዓመት ዘመን ያልተለወጠ ማረሻ የሚሰቃይ ገበሬ አስቡት። ጉሊት ጠርጋ፣ ካቲካላ ቸርችራ፣ በባዶ ሆዷ ከመቀነቷ ፈትታ ልጇን ለዩኒቨርሲቲ ልካ – ዛሬ በሰቀቀን የምታነባ ምስኪን እናት አስቧት። ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ እጅ እንኳ የማይሞላውን የሚያናክስ ልሂቅ ብቻ አስባችሁ – በዚህ ወገን ዕጣንታ ላይ አትጣጣሉ።
*
ታሪክ እናንተን ወደፊት አምጥቷችኋል። ነገም በሥራችሁ ሠፍሮ (መዝኖ) በደማቅ ቀለም ወይም በአስከፊ ጎን ያሠፍራችኋል። (መቼም The former ካልሆነ The latter ምርጫችሁ እንዳልሆነ አበክሬ እገነዘባለሁ።)
*
እባካችሁ በምትወዷት እናታችሁና በምትሳሱላችሁ ልጆቻችሁ ልማፀናችሁ – ራሳችሁን በዚህ ከአንድ እጅ (1%) ያነሰ ልሂቅ ተብዬ ሳይሆን >  በ110ሚሊየን ወገናችሁ ጫማ ውስጥ ቆማችሁ መዝኑ። ይህ አደራ እንዳይደበዝዝ!
አደራ ለማ ኮ፤ አደራ አቢቹ፤ አደራ ኢሲን ለቹ፣ አደራ አደራ አደራ
ከላቀ አክብሮትና ሰላምታ ጋር
ኢልመ ደሱ ኦዳ
Filed in: Amharic