>
6:38 am - Tuesday July 5, 2022

አበሻና ጽሕፈት [ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም]

ሰኔ 2006

በቅርቡ ከአንድ ወዳጄ ጋር ስለኢየሩሳሌም ማኅበር ስናወራ መሥራቹ አቶ መኮንን ዘውዴ ትዝ አሉኝና ስለሳቸው ውለታ ሳወራ ነበር፤ ከሳቸው ጋር ተያይዞም ከዚህ በፊት አይ አበሻ! በሚል አጠቃላይ ርእስ አበሻና ልመና ወዘተ. እያልሁ መጻፍ ጀምሬ የነበረው ትዝ አለኝ፤ አንዳንድ ስላልገባቸው ነገር ሁሉ መጻፍ የሚወዱ ሰዎች አቅጣጫውን ሊለውጡት ሙከራ ሲጀምሩ ትቼው ነበር፤ አሁን የመክሸፍን ጉዳይ ደግሜ ለመጻፍ ስጀምር አንዳንድ በጣም መሠረታዊ የሆኑ የመክሸፍ መገለጫዎችን ስጽፍ በመጽሐፍ መልክ እስኪወጣ አላስችል አለኝና አንዱን ሀሳብ አደባባይ ለማውጣት ወሰንሁ፤ በዚያውም አቶ መኮንን ዘውዴን ማስታወሻ ይሆነኛል።

ወደ 1935-36 ግድም በአዲስ አበባ ውስጥ ክፉ ችግር ቸጋርን አስከትሎ ነበር፤ አጼ ኃይለ ሥላሴ ገና ከስደት ከተመለሱ ሁለትና ሦስት ዓመት መሆኑ ነው፤ አገር አልተረጋጋም፤ የኢጣልያኑ አገዛዝ ቅሪት፣ የእንግሊዞች ዘረፋ፣ የሱዳን፣ የኬንያና የደቡብ አፍሪካ ወታደሮች እንደልባቸው የሚፈነጩበት ጊዜ ነበር፤ በአንድ በኩል በአርበኞቹ ላይ የነበረው ኩራት፣ በሌላ በኩል በኢጣልያኖች፣ በእንግሊዞችና በሌሎች የውጭ አገር ሰዎች የበላይነት ኩራቱ የሚደፈጠጥበት ጊዜ ነበር።

በቤት ውስጥ እናቴና የእናቴ ረዳት ሆና ያሳደገችኝ ሴት ሲቸገሩ በየዕለቱ አያለሁ፤ አብዛኛውን ጊዜ የሁለቱም ችግር ለእኔ ነበር፤ ስለዚህ ኃላፊነት ተሰማኝና የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማድረግ ሥራ ያዝሁ፤ የነበረኝ ችሎታ የእጅ ጽሕፈት ብቻ ነበር፤ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በር ላይ ራፖር ጸሐፊ ሆንሁ፤ የእጅ ጽሑፌ በጣም ጥሩ ስለነበረ አብዛኛዎቹ ሰዎች ወደእኔ በመምጣታቸው ደህና ገንዘብ አገኝ ጀመረ፤ እናቴን ከመርዳት አልፌ ሌላ ሌላ ነገርም ለመልመድ እየዳዳኝ ነበረ፤ ቁልቁለቱን ለመውረድ የሚረዱኝ ነበሩ፤ አንድ ዘመድ ትምህርቴን ብቀጥል እንደሚሻለኝ ነገረኝና ለትምህርት ሚኒስቴር ማመልከቻ ጽፌ አቶ መኮንን ዘውዴ ለሚባሉት አንድሰጥ መከረኝ፤ እኔም እንደተመከርሁት አደረግሁና አቶ መኮንን ማመልከቻዬን ገና ተቀብለው ሲያዩት ማን ነው ይህን ማመልከቻ የጻፈልህ? ብለው ጠየቁኝና እኔ መሆኔን ስነግራቸው ወረቀትና ብዕር ሰጡኝና እስቲ ጻፍ አሉኝ፤ በጣም አስደሰታቸውና ከተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ዲሬክተር የምስክር ደብዳቤ እንዳመጣላቸው ጠየቁኝ፤ በበነጋታው ይዤላቸው ስሄድ እሳቸውም ወዲያው ማዘዣ ሰጡኝና በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አዳሪ ሆንሁ፤ የእናቴንና የአሳዳጊዬን ችግር ቀነስሁ።

ከላይ የተዘረዘረው ታሪክ ዓላማ ራሴን ለማስተዋወቅ አይደለም፤ ጽሕፈትን ለማስተዋወቅ ነው፤ በኢትዮጵያ የጽሕፈትን መክሸፍ፣ የእውቀትን መክሸፍ ለማሳየት ነው፤ አቶ መኮንን ዋጋ የሰጡት በኢትዮጵያ ባህላዊ ትምህርት ዋጋ የሚያወጣውን የእጅ ጽሑፍ ውበት ነው፤ በኢትዮጵያ የጽሕፈት ዋና ተግባር ለቤተ ክርስቲያን የጸሎት መጻሕፍትን ለመጻፍና ለቤተ መንግሥት ማዘዣዎችን ዜና መዋዕሎችን ለመጻፍ ነበር።

በሌሎች አገሮች የጽሕፈት ዋና ተግባር እውቀትን ለማሰራጨት፣ እውቀትን ለማስተላለፍና እውቀትን ለመለዋወጥ ነበር፤ ነገር ግን የራሳችን ፊደል ቢኖረንም፣ የጽሕፈት ባህል ጅምሩ ቢኖረንም የጽሕፈት ተጠቃሚዎች ነበርን ለማለት የሚያስደፍር ምንም ነገር የለም፤ እንዲያውም የኢትዮጵያ ታሪክ መክሸፍ ዋናው ቁልፍ አንደነበረ ግልጽ ሆኖ ይታያል፤ በመጀመሪያ ሁለት መሠረታዊ እውነቶችን ላንጥፍ፡— አንደኛ የፊደሎችና የጽሕፈት ጉዳይ የተጀመረው በምሥራቁ የዓለም ክፍል ዛሬ መሀከለኛ ምሥራቅ በሚባለውና በሩቅ ምሥራቅ አገሮች ነው፤ ሁለተኛ መጻሕፍትን ማሳተሚያ መኪና የተፈጠረው በምዕራባውያን ነው፤ እንደሚባለው በአሥራ አምስተኛው ምዕተ-ዓመት መዝጊያ ላይ ነው፤ ጽሕፈት በምሥራቃውያን ከተፈጠረ ከብዙ ምዕተ-ዓመታት በኋላ ማተሚያ መኪና ተሠራ፤ በጽሕፈት መፈጠርና በጽሕፈት ማተሚያ መፈጠር መሀከል ያለውን የዓመታት ልዩነት በአንድ በኩል፣ በጽሕፈት ፈጣሪዎችና በጽሕፈት ማተሚያ መኪና ፈጣሪዎች መሀከል ያለውን ልዩነት ልብ በሉ፤ ከተቻላችሁም ተወያዩበት።

ነገሩን ወደኢትዮጵያ ስናመጣው የፊደላችን ዕድሜ በሺህ ዓመታት የሚቆጠር ለመሆኑ ድንጋይ ይመሰክራል፤ የጽሕፈት መኪና ከገባ ግን ከመቶ ሃምሳ ዓመት የሚበልጥ አይመስለኝም፤ ዛሬ የመለስ ዜናዊ አገልጋዮች እንደሚሉት የኢትዮጵያ ታሪክ ከመቶ ዓመት አይበልጥም ሲሉ፣ በወግ በሥርዓት የተመዘገበ ታሪክ የለም ማለታቸው ይመስለኛል፤ በዚህም ምክንያት እኛ ባለቤቶች እንሆንበታለን ማለታቸው ነው፤ እንግዲህ መክሸፍ መክሸፍን እንዴት እንደሚወልድ በገሀድ ይታያል፤ ፊደል ከሸፈ፤ ጽሕፈት ከሸፈ፤ እውቀት ከሸፈ፤ ኅትመት ከሸፈ፤ በመክሸፍ መሰላል ወንበሩ ላይ የወጡት የመክሸፍ ልጆች ናቸው፤ እነዚህ የመክሸፍ ልጆች የመክሸፍን ዕድሜ ለማራዘም ቢሞክሩ ምን ያስደንቃል? አፈናውን ቢያጠናክሩት፣ የዜና ማሰራጫዎችን ሁሉ በቁጥጥራቸው ስር አድርገው ውሸታቸውን የሚያጋልጡባቸው ጋዜጦች እንዳይኖሩ ማድረግ የባህርያቸው ነው፤ ደንቁሮ ማደንቆር የባሕርይ ነው።

በመገናኛ ብዙኃን ዛሬ ዓለም የሁሉም ሆናለች፤ ለአፈና አገዛዝ አትመችም፤ ኢትዮጵያውያን ፊደልን ሲንቁ እውነትንና እውቀትን ናቁ፤ እውነትንና እውቀትን ሲንቁ ዳገቱን እየተዉ ቁልቁለቱን ወረዱ! ቀላል ነው፤ መክሸፍ ማለት አንዲህ ነው።

Filed in: Amharic