>
5:13 pm - Friday April 19, 8537

ከህወሃት ጋር ህብረት ማድረግ መብት ነው? (መስከረም አበራ)

ከህወሃት ጋር ህብረት ማድረግ መብት ነው?

 
መስከረም አበራ
ሰው የማሰብ ነፃነት አለው፡፡ማንም ሰው ወዳመነበት ፖለቲካዊ መንገድ መጓዝ መብቱ ነው፡፡ይህ መብት ግን ገደብ የሌለው ፍፁም አይደለም፡፡ የህግ እና የሞራል ገደብ አለው፡፡ የማሰብም ሆነ የሌላው መብታችን መገደቢያ የሌሎች መብት ነው፡፡ የእኛ የማሰብ ነፃነት የሌሎችን መብት የሚጋፋበት መስመር ላይ ሲደርስ ግዴታ መሆን ይጀምራል፡፡የሌሎችን መብት አለመጋፋት የማሰብም ሆነ የሌላው መብታችን ገደብ ነው፡፡ህግ አንድ ሁለት ብሎ በማይጠይቀን ሁኔታ መብታችን ሞራላዊ ገደብ አለው፡፡የዚህ ሞራላዊ ግዴታ የመሰረት ድንጋይ ሰብዓዊ እሳቤ ነው፡፡
በሰብዓዊነት ሚዛን ተፈትኖ ከወደቀ ጋር ማህበር መጠጣት ከአውሬነት መጋራት ነው፡፡ህወሃት በሰብዓዊነት ተፈትኖ የወደቀ ወደ አውሬነት የሚቃጣው ባህሪ ያሳየ ቡድን ነው፡፡ይህን ሃያ ሰባት አመት ዓይተነዋል፡፡ በዚህ ዘመን ሁሉ ህወሃት ከዛሬ ነገ ይሻለዋል ሲባል  በሚብስ አውሬነት ሲገዛን እንደኖረ የሚከራከር የለም፡፡ሃያ ሰባት አመት “ቢቆዩኮ ሊሻሻሉ ይችላሉ” የሚባልለት አጭር ዘመን አይደለም፡፡ይበልጥ ተስፋ አስቆራጩ ደግሞ የህወሃት የሰብዓዊ መብት ይዞታ በዓውሬነቱ እያደር የሚብሰው መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ መሻሻልን ማሰብ ከህወሃት መባስ ነው፡፡
ህወሃት በማዕከላዊ ሰው በእግሩ ገብቶ በቃሬዛ እስኪወጣ ድረስ በሃገሩ ልጅ የሚጨክን እኩይ ስብስብ ነው፡፡በማዕከላዊ የተደረገው ብዙ ነው፤ሰው እንደ ፎቶ ግራፍ ግርድዳ ላይ ተሰቅሏል፣ጀርባው ተተልትሏል፣ተኮላሽቷል፣በወንድ ልጅ ላይ ግብረሰዶም፤በሴት ልጅ ላይ የርብርብ መደፈር ተደርጓል፣ፈጣሪ የሰጠውን አየር እና ብርሃን እንዳያይ ተደርጓል፣የሴት ወንዱ ጥፍር ተነቅሏል፣ውስጥ እግሩ በሰንሰለት ተተልትሏል፣የበላው በአፉ እስኪመጣ ተዘቅዝቆ ተሰቅሏል፣በደረቅ ሌሊት ጅብ እንዲጫወትበት ወደጫካ ተወስዶ ከዛፍ ጋር ታስሯል፣ከግንድ ጋር በታሰረበት የማይገድል ጥይት እየተተኮሰበት “ሞቻለሁ አለሁ” እያለ የሰቀቀን ሌሊት አሳልፏል፡፡
በጄል ኦጋዴን መላው የሶማሌ ወጣት አዛውንት የምድርን አሳር አይቷል፡፡በጄል ኦጋዴን በተደረገው እርኩሰት ምድረ ፈረንጅ በእኛ “አጃኢብ!” ብሏል! “Human rights watch” በምድረ ሶማሌ ህወሃት በሰው ልጆች ላይ ስለፈፀመው እርኩሰት ባለ ሶስት ዲጅት ገፅ ሪፖርት ፅፏል፡፡ይህን ሪፖርት ሳነብ ከቁጥጥር ውጭ ሆኔ ቤተመፅሃፍት ወስጥ እስከማንባት ደርሻለሁ፡፡ሪፖርቱን አንብቤ ሰሚ ካለ በሚል ወያኔ ስልጣን ላይ እያለች አንድ ፅሁፍ ፅፌ ነበር፡፡ ለትውስታ መልሼ እለጥፈዋለሁ፡፡ማንም የሰው ፍጡር ይህን ሪፖርት አንብቦ በሰላም አያድርም! በበኩሌ ታምሜ ነበር፡፡ ወልቃይት ጠገዴን የትግራይ አካል ለማድረግ በሰው ልጆች ላይ የተሰራው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለወሬ የማይመች ነው! በዚሁ ሰበብ እስከ ዛሬ ድረስ ባዶ ስድስት እስርቤት በህወሃት አረመኔያዊ እጅ የሚማቅቁ የሰው ልጆች እንዳሉ ግልፅ ነው፡፡
ከህወሃት ጋር ያለኝ የመረረ ጠብ ዋና ምክንያቱ በየእስር ቤቱ በቁጥጥሩ ስር የዋሉ ምስኪን የሰው ፍጡራንን ከማስራብ ማስጠማት ጀምሮ በሚያደርገው ቁጥር ስፍር የለሽ አረመኔነት ነው፡፡ በግሌ ህወሃት እንደ ናዚ መታገድ ያለበት፣ማንኛውም ምልክቱ እንዳይታይ መደረግ ያለበት ሰው በላ ፓርቲ ነው፡፡ በህይወቴ ሆኖ ማየት የምፈልገውም ይህን ነው-ህወሃት የሚባል ፓርቲ በህግ ታግዶ ማየት!
እየሆነ ያለው ግን ሌላ ነው፡፡ “በደለኛ በበደሉ ካልተጠየቀ የተበዳይነት ስሜት ያዳብራል” ብሎኝ ነበር አዋቂው ወዳጄ አቶ ብርሃነ መዋ በአንድ ወቅት፡፡ እውነቱን ነው፡፡ ህወሃት በሰው ልጆች ላይ ለፈፀመው አረመኔያዊነት የሚጠይቀው ስለጠፋ ጭራሽ “የሃገር አዳኝ ነኝ” ብሎ ከእሱ የባሱትን ሰብስቦ እየመከረ ነው፡፡ከህወሃት  ጋር “wine and dine” የሚያደርግ ሁሉ የህወሃት አውሬነት ተጋሪ እንጅ ፖለቲከኛ አይደለም፡፡
ከህወሃት ጋር ማህበር መጠጣት የማሰብ ነፃነት ፅንሰሃሳብ ተጠቅሶ ለክርክር የሚቀርብ ነገር አይደለም፡፡በዚህ በሰለጠነ ዘመን ማንኛወም ህግ ሲወጣ፣ማኛውም ፓርቲ ሲታገል፣ማንኛውም ድርጅት ሲንቀሳቀስ የሰብዓዊ መብትን በማይነካ መንገድ ካልሆነ ወዲያውኑ ህገወጥ፣ወንጀለኛ እንጅ የፖለቲካ ሃሳብ ያለው አካል ተደርጎ አይወሰድም፡፡
 ስለዚህ ህወሃትን ከበው መቀሌ የተቀመጡ ሁሉ ውግዝ የሚገባቸው፣በሰው ልጆች ሰብዓዊነት ላይ ወንጀል የሰራ ስርዓትን ደጋግፈው መልሰው ለማቆም የሚፈልጉ፣በሰብዓዊነት ላይ ቀልድ የያዙ ፍጡራን ናቸው፡፡ የሰውን ሰብዓዊ ክቡርነት ያላወቀ አውሬ ስለ ፌደራሊዝም ሊያወራ አቅሙ አይፈቅድም!  መጀመሪያ ከአራዊት ተርታ ወጥቶ ሰው መሆን ያስፈልጋል !
ከህወሃት ጋር ማህበር ለመጠጣት ቢያንስ በሰው ልጀች ላይ የፈፀመውን አውሬነት አምኖ ይቅርታ መጠየቅ አለበት፡፡ ህወሃት ደግሞ እንኳን ጥፋቱን አምኖ ይቅርታ ሊጠይቅ ቀርቶ ጭራሽ ተበዳይነት እየተሰማው ያለ አካል ነው፡፡ይህ ለማንም ግልፅ ሆኖ ሳለ ህወሃት ጠራኝ ብሎ እግር ነቅሎ መሮጥ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ መቀለድ፣በሰብአዊነት ላይ ማሾፍ ነው! በዚህ አጋጣሚ “በወገኖቼ ሰብዓዊነት ላይ አልቀልድም” ሲል ለህወሃት ልኳን ነግሮ ጥሪዋን እንደማይቀበል የተናገረው ኦብነግ እና ወደ መቀሌ ያላቀናው ኦነግ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
መቀሌ የከተሙት ሲመለሱ በያሉበት የመገለል የሞራል ቅጣት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በሰብዓዊነት ላይ የቀለደ መገለል ሲያንሰው ነው፡በተገኙበት-ይዋረዱ!
Filed in: Amharic