>
5:16 pm - Thursday May 23, 4267

በአገርማ ቀልድ የለም!... በቀበሮ ባሕታውያኑ አደጋ እየተደገሰ ነው!!! (ውብሸት ታዬ)

በአገርማ ቀልድ የለም !

በቀበሮ ባሕታውያኑ አደጋ እየተደገሰ ነው!!!

ውብሸት ታዬ
   የበለጠ ነቅተን አገራችንን የምንጠብቅበት ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን! ምክንያቱም በአገራችን ታሪክ ውስጥ የትኛውም ቃል የማይገልጸው አገር ገዳይ የሆኑት ሕወሓቶች ‘አገር እናድን’ ሲሉ እየተሳለቁ በመሆናቸው ነው።
   ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በጥይት ጨፍጭፈው ገድለዋል፣ አገር እየለመኑ ለሌሎች ሰጥተዋል(አሰብን)። ቡድናዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በመቶ ኪሎ ሜትሮች የሚለካ ወሰን ለሱዳን አሳልፈው ሰጥተዋል(አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጠንክረው በመሟገታቸው እስካሁን ዓለም አቀፍ እውቅና አላገኘም)። ለሌሎች እንደከረሜላ ከሚያድሉት ወሰን መለስ ሲሉ እንደወልቃይት ያሉ አከባቢዎችን በክልል ሽፋን በጠራራ ጸሐይ ወደራሳቸው ከልለዋል።- አሳድሩኝ ብሎ ርስት አካፍሉኝ እንዳለው መሆኑ ነው።  ሌላው የሕወሓቶች ቅዠት በፈጠረው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት 120 ሺህ ልጆቻችንን አጥተናል።
በሌብነት ደግሞ የተካኑ ናቸው፤ በዓለም ባንክ መረጃ መሰረት በሕዝብ ትግል ከአራት ኪሎ ተባረው ወደጎሬያቸው ከመግባታቸው በፊት ሰላሳ ቢሊዮን ዶላር ያህል ወደውጭ አሽሽተዋል። ግብረ ገብ የራቃቸው ናቸውና ሸሽተው በተደበቁበት ሳይቀር አንድ ሹም ሃምሳ እናቶችን ደፍሮ ለሕግ የማይቀርብበት ለጉድ የፈጠራቸው መሆኑን ሕዝቡ የተቃውሞ ሰልፍ በመውጣት ለዓለም ያሳየበት እውነታ አለ። ስለጅቡ የተነገረው ሁሉ ይገልጻቸዋል!
   ጅብ ቀን ለምን አይወጣም? ቢሉ መልሱ ሌሊት የሠራውን ስለሚያውቅ ነው። ስለጅብ ብዙ ተተርቷል፤ ብዙም ይታወቃል። ስለማይተማመን ኋላና ፊት አይሄድም፣ የራሳቸውን ዝርያዎች ከሚባሉ አውሬዎች አንዱ ጅብ ነው። …
   የ27 ዓመታት ሥራዋን የምታውቀው ሕወሓት መቀሌን የሙጥኝ ካለች ከረመ። እንደጅብ ተጠራርተው ካራቆቱት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቋት እየቆነጠሩ ሆድ አደሮችን ወደዋና መዲናቸው ሲጋብዙም ከርመዋል።
   እናም መሰሎቻቸው ለቃቅመው ‘የፌዴራሊስት ሃይሎች’ የተሰኘ ጉባኤ ያካሄዱ ሲሆን ለሦስት አስርታት በወንጀል ተጨማልቀው የተጓዙበትን ርዕይ ለማስቀጠል የመጨረሻ ሙከራ ጀምረዋል።  ሂደታቸውን ለማሳካት ከአገራችን ታሪካዊ ተቀናቃኞች ጋር የተለያዩ ግንኙነቶችን ሲያደርጉ ከርመዋል። በፌዴራሊዝም ስም እየማሉ አገር ለመበተን ከሚባትሉ ቡድኖችና ግለሰቦች ጋር ብዙ ዶልተዋል። (በቅርብ ጊዜ የዚህ ሁሉ አስደማሚ እንቅስቃሴ ዝክር በተደራጀ እና እውነተኛ መረጃ ለሕዝብ እንደሚቀርብ በቂ መረጃ አለ!)
   በመቀሌው ለሕወሓት ቀብር ለቅሶ የደረሱ ስብስቦች ካወጡት አምስት የአቋም መግለጫ አንዱ ‘ኢህአዴግ በህብረ ብሔራዊ የፌደራሊዝም ስርዓት እንዲመራት በአደራ የተቀበላት አገርና የተሰጠው የፖሊቲካ ስልጣን መንገድ ስቶ አገሪቷን ወደ መበታተን አያመራች ነው።’ የሚል ነው። መጀመርያ ለኢሕአዴግ አደራ የሰጠው የለም። ጭራሹኑ ሕወሓት ኢትዮጵያን ሰርቋታልና ይመልስ እየተባለ ነው። – መመለሱም አይቀርም !
   ሁለተኛው አስገራሚ ነገር ስለመበተን ያሉት ነው። ሕወሓት ሕልሟ ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ መበተን በመሆኑ አዲስ ነገር አልነገሩንም። እነሱ እያሉ ያልተበተነች አገር ከላያችን ባራገፍናቸው ማግስት ይህ እንዴት ይሆናል?!
   ***//***
ፌዴራሊዝም የመንግሥት ሥርዓት ቅርጽ መሆኑ ቀርቶ የፖለቲካ ማጭበርበርያ ካርድ እየሆነ ነው። ተከፋዮቹ የመቀሌዎቹ ‘ፌዴራሊስቶች’ ይህን አረጋግጠውልናል።    ፌዴራሊዝም ዛሬ በዓለማችን ላይ ምርጥ የስርዓተ መንግስት ዓይነት ነው። ሃያ አምስት አገራት(የዓለማችንን ሕዝብ 40% ያህል) የተለያየ የፌዴራል አስተዳደር ስርዓት ይከተላሉ። አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጀርመን፣ ሜክሲኮ፣ ሩሲያ፣ ብራዚል፣ ሕንድ፣ ወዘተ ፌዴራላዊ አገራት ናቸው። በእርግጥ ፌዴራሊዝም በአፍሪካችን ብዙም የተለመደ አይደለም። አገራችንን ጨምሮ ናይጄሪያ ኮሞሮስና ደቡብ አፍሪቃ ብቻ ፌዴራሊዝምን ይከተላሉ።
ስለዚህ በአገር እናድን ሰበብ አገር ለማጥፋት በሚማማሉ ሳይሆን በእውነተኞቹ የሕዝብ ልጆች ስለፌዴራሊዝም መመከር አለበት። ምን ዓይነት ፌዴራሊዝም ያስፈልገናል? ምን ዓይነት ሕገ መንግሥት እንቅረጽ? የሌሎች አገራት ተሞክሮ ምን ይመስላል? በእኛ ነባራዊ ሁኔታ ከአጭር ከመካከለኛና ከረዥም ጊዜ አኳያ ምን አይነት ፖለቲካዊ ፍኖተ ካርታ ይኑረን? ወዘተ፣ … ሊመከርበት ይገባል። በመንግሥት ዙርያ ጮህ ብላችሁ ሆያ ሆዬ እያላችሁ ያላችሁ ወገኖች፤ ይልቅ ጩኸቱን ቀንሱና ቁም ነገሩ ላይ አተኩሩ።    ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ስለአገራችን ነቅተን እንከታተል። ማን ምን እያደረገ እንደሆነ እናስተውል፤ ከሰሙን እረፉ እንበላቸው። በአገርማ ቀልድ የለም !
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ፤ ሕዝቧን ይባርክ!
Filed in: Amharic