>

ዶ/ር አብይ አህመድ የብሔር ፖለቲካን ከምርጫ ፖለቲካ መለየት አለባቸው!!! (የቀድሞው የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት)

ዶ/ር አብይ አህመድ የብሔር ፖለቲካን ከምርጫ ፖለቲካ መለየት አለባቸው!!!

የቀድሞው የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት
(ኢትዮ 360 ) – ታህሳስ 30/2012)ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የብሔር ፖለቲካን ከምርጫ ፖለቲካ መለየት አለባቸው ሲሉ የቀድሞ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ሰር ሊፍ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ አሁን ከገባችበት ቀውስ እንድትወጣ ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም ካላቸው፡ የብሔርና የምርጫ ፖለቲካን በግልጽ ለይተው ማስቀመጥ ነው ከሳቸው የሚጠበቀው ብለዋል።
በ2006 የላይቤሪያን የፕሬዝዳንትነት መንበረ ስልጣን ስጨብጥ እንዲህ አይነት ፈተና ነበር የገጠመኝ ይላሉ ኤለን ጆንሰን ሰር ሊፍ።
ከብዙ ድካምና ውጣ ውረድ በኋላ ዛሬ ላይ ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ይላሉ።
የዛሬ ስምንት አመት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የቆሙበት የኖቬል ሽልማት መድረክ ላይ እኔም ቆሜ ነበር።
በወቅቱ አንድ ነገር አስብ ነበር ያም ታሪክ የሚመዝነን በዛ ሰአት በተናገርንው ሳይሆን በቀጣይ በምንሰራው እንጂ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ያሉት የሽግግር ወቅት ላይ ነው ይላሉ።
በዚህ ወቅት ያከናወኗቸው በርካታ ተግባራት አሉ።
ነገር ግን የተወሳሰቡና ያልፈቷቸው ብሎም ከባድ አደጋ ሊያመጡ የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች አሁንም ከፊታቸው አሉ።
ባለፉት አስርት አመታት ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግባለች የተባለችው ኢትዮጵያ የዜጎቿን የአኗኗር ሁኔታ ስትቀይር አልታየችም።
የዚህ ማሳያ ደግሞ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያገኙ ዜጎቿ ቋጥር 30 በመቶ ብቻ ነው፡የኢንተርኔት አገልግሎት የሚያገኙት ደግሞ 18 በመቶ ይላሉ ኤለን ጆንሰን ሰር ሊግ።
ይሄ ደግሞ አህጉሪቱ ካስቀመጠችው ደረጃ  በታች ነው።
ከ60 አመት ቅኝ ግዛት በኋላ ነጻ የወጡ ሃገራት ባካሄዱት የሽግግር ወቅት ብሔራዊ ማንነትን፡ዲሞክራሲንና የገበያ ኢኮኖሚን በመገንባት ልምድን በማዳበር ከገጠማቸው ችግር መውጣት ችለዋል።
ይህን ሲያደርጉ ደግሞ ያለፏቸው በርካታ ፈተናዎች ነበሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም ከፊታቸው ሐገራዊ ምርጫ የሚባል ትልቅ ፈተና ተጋርጧል።
ይህንን ጋሬጣ ለማለፍ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመሪያ ተግባራቸው ሊሆን የሚገባው የብሄር ፖለቲካንና የምርጫ ፖለቲካን በግልጽ ለይቶ ማስቀመጥ ነው።
ሌላኛው የፈተኛ መውጫ ተግባር ደግሞ ግልጽነትና የዲሞክራሲ ማሻሻያን ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም መያዝ ነው ይላሉ ሰርሊፍ።
እውነተኛና ለወደፊቱ ተስፋ የሚጣልበት እቅድ መንደፍም ጊዜ የማይሰጠው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቤት ስራ ነው ይላሉ።
ከፋይናንሻል ታይምስ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሰርሊፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መልኩ ጥረት ካደረጉ የአፍሪካና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዳይለያቸው እጠይቃለሁ ሲሉ ምክራቸውን አጠቃለዋል።
Filed in: Amharic