>

በምስራቅ ዕዝ ሙዚቀኞች ላይ የደረሰው እልቂት (ታህሳስ 1980)  (አፈንዲ ሙተቂ)

በምስራቅ ዕዝ ሙዚቀኞች ላይ የደረሰው እልቂት (ታህሳስ 1980) 

አፈንዲ ሙተቂ

«ይቅርታ» ማንን ገደለ??

 
ንግሥት አበበ «ገላዬን መውደዴ» የሚል የምትታወቅበትን ዘፈኗን በልቧ ሰንቃ፣ ድርስ እርጉዝ ነኝ ብትል ሰሚ አጥታ ከ17 ሙዚቀኞች ጓዶቿ ጋር ከሐረር ሙዚቀኛ ግቢ ተነስታ ወደ አስመራ ተጓዘች። ጎራው (ዲናሬ) ከሚባለው ከአንዱ ዘፋኝ በቀር በህይወት የተመለሰ አልነበረም። ሁሉም በሻዕቢያ ላውንቸር ተበሉ። የንግሥት አበበ ያላለቀ አልበም ከሞቷ በኋላ ተለቀቀና እንባ አራጨን። 
 
ለመሆኑ ዛሬ ስንቱ ኢትዮጵያዊ ነው እነዝያን በአንድ ጀንበር የተሰዉ 17 ኢትዮጵያዊያን አርቲስቶችን የሚያስታውስ? ሻዕቢያስ ስለድርጊቱ በይፋ የጠየቀው ይቅርታ አለ ወይ? 
——-
እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1980 ገደማ በሀረር ከተማ ከአምስት ያላነሱ ኦርኬስትራዎች ነበሩ፡፡ ከነርሱም መካከል ሶስቱ ከሀረርጌ ክፍለ ሀገር አልፎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ስም ነበራቸው፡፡ እነርሱም በተለምዶ “የምስራቅ እዝ ኪነት” የምንለውና በዘመኑ አጠራር ግን “የአንደኛው አብዮታዊ ሰራዊት ኦርኬስትራ” የሚባለው የኪነት ቡድን (እነ ንግሥት አበበ እና ኑሪያ ዩሱፍን የመሳሰሉ ከዋክብትን ያቀፈ)፣  “የምስራቅ በረኛ አብዮታዊ ፖሊስ የኪነት ጓድ” (እነ ኤልሳቤት ተሾመ፣ ፍቅሩ ቶሌራ፣ ሙሳ ቱርኪ፣ ፋንታሁን ፈረንጅ እና ግርማ ንጋቱ የነበሩበት) እና “ጎሐ ምስራቅ የኪነት ቡድን” (እነ ሰለሞን አካሉ፣ ሙሉጌታ አባተ፣ መፍቱሐ አባስ እና ሙስጠፋ አብዲ የመሳሰሉትን ያቀፈ) ናቸው፡፡
«   ከሶስቱ ቡድኖች አንዱ የሆነው የምስራቅ ዕዝ ኪነት ቡድን ከሻዕቢያ ጋር ለሚፋለመው ሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት ዝግጅቱን ለማቅረብ ወደ ሰሜን ተጓዘ፡፡ ግን በሰላም አልተመለሰም፡፡ ንግሥት አበበን ጨምሮ በርካታ አባላቱን በሞት አጣ፡፡ በቡድኑ ላይ የደረሰው እልቂት በኢትዮጵያ ሬድዮ ሲነገር በርካቶችን በእንባ አራጨ፡፡ በተለይ ከዘመኑ አፍለኛ ዘፋኞች አንዷ የነበረችው የንግሥት አበበ ሞት የብዙዎችን ልቦና የሰበረ ነበር፡፡ ያ አሳዛኝ ትራጄዲ እንዴት ተከሰተ? የቡድኑ አስተዋዋቂ የነበረውና ከሞት የተረፈው  ግርማ ከበደ (በቅጽል ስሙ “ግርማ ዲናሬ”) ሁኔታውን ለኢትኦጵ መጽሔት እንደሚከተለው አብራርቶ ነበር፡፡
—–
«ኢትኦጵ፡- አንድ ጊዜ የምስራቅ እዝ ኪነት ቡድን ወደ ሰሜን አቅንቶ በሻዕቢያ ደፈጣ ተዋጊዎች እንደተመታ ሰምቻለሁ፡፡ በዚያን ጊዜ አንተ ነበርክ?
«ግርማ፡ አዎን እኔም ነበርኩ፡፡ ደመናው ከልሎኝ ከተረፉት ጥቂቶች አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ጊዜው 1980 ዓ.ም. ታሕሳስ 21 ቀን ነው፡፡ ዝግጅታችንን ግንባር ላለው ሰራዊት አቅርበን ወደ አስመራ ስንመለስ ጠላት አድፍጦ ይጠብቀን ነበርና 17 አርቲስቶች በዚያ ውጊያ ህይወታቸው ጠፋ፡፡ ካጀቡን ወታደሮችም 20 ያህሉ በውጊያው ተሰውተዋል፡፡ 14 አርቲስቶች ደግሞ ቆስለዋል፡፡ አራት ሰዎች ብቻ ምንም ጉዳት አልደረሰብንም፡፡
«ኢትኦጵ፡- የምስራቅ እዝ የተዋጣላት ድምጻዊት ንግሥት አበበ በዚህ ውጊያ ላይ ነበር ህይወቷ ያለፈው?
«ግርማ፡- አዎን (በሐዘን ስሜት አቀረቀረ)::
«ኢትኦጵ፡- እስቲ ያንን ሁኔታ እንዴት ትገልጸዋለህ?
«ግርማ፡- ወደ አስመራ ስንመለስ ትልቅ ስጋት ነበረብን፡፡ ሻለቃ ታደሰ የተባሉ አዛዣችንም ጥንቃቄ እንድናደርግ ደጋግመው አሳስበውናል፡፡ እሳቸውም እዚያው ነው የተሰውት፡፡ ሻለቃው እንደሰጉት እኛም አንዳች አደጋ ሊገጥመን ይችላል ብለን ፈርተን ነበርና አልቀረልንም፡፡ አደጋው መጣ፡፡ ንግሥት በፈንጂ ደረቷ ስር ተመትታ ነው የወደቀችው፡፡ ብዙ ቦንብ ነበረ የሚወረውሩብን፡፡ አጃቢዎቻችን ለመከላከል ብዙ ሞከሩ፤ ግን አልሆነም፤ አለቁ፡፡ እነርሱን መጨረሳቸውን ሲረዱ አርቲስቶች ወዳሉበት መኪና ተኩስ ከፈቱ፡፡ እየተላቀስን በጥይት ቀጠቀጡን፡፡ “ሁሉንም ጨርሰናል” ብለው ካደፈጡበት ወጡ፡፡ የተረፈ እንዳለ ፈተሹ፡፡ እኔ አንድ ስርቻ የሞተ መስዬ ተደበቅኩ፡፡ መቼም ፈጣሪዬን እንደዚያ ቀን የተማፀንኩበት ጊዜ አልነበረም፤ ተረፍኩ፡፡
«ኢትኦጵ፡- ያንን አደጋ እንጠብቀው ነበር ስትል?
«ግርማ፡ ብዙ ጭንቀት ነበረብን፡፡ ለምሳሌ ንግሥት አበበ የሶስት ወር አራስ ነበረች፡፡ ዝግጅታችንን ስናቀርብ “ለጥምቀት ሀረር አንደርስም ወይ? እኔ ልጄን ክርስትና አስነሳለሁ፤ እንደምንም ብለን በዚህ ጊዜ መጨረስ አለብን” ትል ነበር፡፡ አዛዣችንም ጉዞ ስንጀምር “እኔም ለልጆቼ፣ እናንተም ለቤተሰቦቻችሁ ስትሉ በጉዞ ላይ ጥንቃቄ አድርጉ” ይሉን ነበር፡፡ ይህንን ስንሰማ ሁላችንም ስጋታችን አየለ፡፡ እንደፈራነው ያን ዓይነት እልቂት ጠበቀን፡፡ ሀዘኑ እስከ ህይወቴ ፍጻሜ የሚጠፋ አይመስለኝም፡፡ በጠቅላላው የምስራቅ እዝ ኦርኬስትራ ነው የተመታው፡፡ የት ይደርሳሉ የሚባሉ አርቲስቶች ናቸው በዚያ ጨካኝ ትዕይንት ያለቁት፡፡
(ኢትኦጵ መጽሔት፣ ቅጽ 4፣ ቁጥር 7፣ ሰኔ 1994፣ ገጽ 40)
 —
«እንዲህ ነው እንግዲህ አደጋው የተፈጠረው! ንግስትን ጨምሮ በርካቶች ያለቁት በዚያ አደጋ ነው፡፡ ታዲያ ሻዕቢያ በተመሳሳይ ወቅት ናደው የሚባለውን እዝ አጥቅቶ እጅግ ወሳኝ የሆነ ድል መቀዳጀቱም ይታወሳል፡፡
«ከዚያ አደጋ ቆስለው ከተረፉት አርቲስቶች አንዷ የነበረችው የኦሮምኛ ዘፋኟ ኑሪያ ዩሱፍ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች (ኑሪያ በአደጋው አንድ እግሯን አጥታለች)፡፡ ግርማ ዲናሬ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ነው የሚኖረው፡፡ ፒያሳን የሚያዘወትሩ ሰዎች ሊያገኙት ይችላሉ፡፡
«በነገራችን ላይ አንዳንዶች በስህተት “በአደጋው ያለቁት የምስራቅ በረኛ ፖሊስ የኪነት ጓድ አባላት ናቸው” እያሉ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ ትክክለኛው ታሪክ ግን በግርማ ዲናሬ አንደበት ከላይ የተገለጸው ነው፡፡ ሰላም!»
Filed in: Amharic