>
5:31 am - Friday July 1, 2022

«በምትለምን  ሀገር የማትለምን ቤተ ክርስቲያን ነች ያለችን!!!» (ዲ/ን ዳንኤል ክብረት)

«በምትለምን  ሀገር የማትለምን ቤተ ክርስቲያን ነች ያለችን!!!»

ሙአዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
አደባባይ ሚዲያ፣ አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 6/2012 ዓ.ም)፡- “ቤተ ክርስቲያን ሆይ፥ ፀሐይሽ አትጠልቅም” በሚል መሪ ቃል ታኅሣሥ 5/2012 ዓ.ም በሚሌኒየም አዳራሽ የተካሔደው እና በአገልጋይ ዕጦት የተዘጉ፣ በአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ጥቃትና ተጽዕኖ ሥር ያሉ ሦስት የኦሮሚያ አህጉረ ስብከት አብያተ ክርስቲያንን ለማስከፈትና ለማጠናከር እንዲሁም ገቢ ለማሰባሰብ እና በሆሮጉድሩ ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ እና ምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት የሚገኙ ከ800 በላይ የገጠር አብያተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማጠናከር ያለመውና ጉባኤው ቁጥሩ ከ40ሺህ በላይ የሆነ ሕዝብ ተሳትፎበታል የተባለው ጉባዔ በስኬት መጠናቀቁ ታውቋል።
በዝግጅቱ ላይ የተለያዩ ትምህርቶች፣ መዝሙሮች እና አባታዊ መልእክቶች የተላለፉ ሲሆን በተለይም ሙሐዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ያሰማው ንግግር ታዳሚውን በስሜት ቁጭ ብድግ አድርጓል። በየመካከሉ በጭብጨባ ሲቋረጥ የነበረው ንግግር «በምትለምን ሀገር የማትለምን ቤተ ክርስቲያን ነች ያለችን» በሚለው ኃይለ ቃል የታጀበ ነበር።
በምትለምን አገር ውስጥ የማትለምን ቤተክርስቲያን ላቆዩልን አበው ክብርና ምስጋ ይገባል!”
 
በሚሊኒየም አዳራሽ የዲ/ን ዳንኤል ክብረት      
                 ድንቅ ንግግሮቹ
1.በምትለምን ሀገር የማትለምን ቤ/ክ  ነው አባቶቻችን የሰጡን
2.እኛ በሰዎች ፊት አናለቃቅስም ወይም ሰዎች እንባችንን እንዲያብሱልን ስንል አናለቅስም የምናለቅሰው ለፈጣሪያችን ነው ለቅሷችን በሰማይ ነው ሥራችን በምድር ነው
3.ማንም እንዲተባበረን ማንም እንዲሰራልን መብታችንን እንዲያስከብርልን አንጠይቅም ራሳችን እናስከብራለን : የእንጨቷ ቤ/ክ ስትፈርስ፣ የድንጋይዋ፣ የድንጋይዋ ስትፈርስ፣
የዋሻዋ የዋሻዋ ስትመዘበር የብሯ የብሯን ቢያፈርሷት የወርቋን
የወርቋን ቢያፈርሷት የእንቁዋን እየተካን፡እንሰራታለን፡እንጂ ፀሐይዋ አይጠልቅም
4.ኢትዮጵያ ሀገራችን ናት በፀሎቶቻችን ሁሉ “ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ” ሳንል ፀልየን አናውቅም ኢትዮጵያን ሠርተናታል ታሪኳን ጽፈናል ታሪኳን አዚመናል በሥዕል አስቀምጠናል እስካሁን አድርሰናል ስለዚህ ከማንም እገዛ አያስፈልገንም
5.በተራራ ገዳማትን አባቶች ሲሰሩ የማንንም እርዳታ አልፈለጉም IMF አልረዳቸውም WORLD BANKም አልረዳቸውም
6.ወለጋ ትልልቅ ሕንጻዎች የሉም ትልልቅ ክርስቲያኖች ግን አሉባት
7.ቅዱሳን ፓትርያሪክ  ሊቃነ ጳጳሳት ሥራችሁ አስተዳዳሪዎችን ማዘዋወር አይደለም ሥራቹ መንጋውን መጠበቅ ነው
8.ያቃጠላችሁና የገደላችሁ ወዳጆቻችን ገድለ ሰማዕታትና ስንክሣር እንዲቀጥል ስላደረጋችሁልን እናመሰግናለን “በዛቲ ዕለት አዕረፈ” ብሎ የሚጀምረው ስንክሣራችን የተዘጋ መስሎን ነበር ለካስ ገና መቀጠልና ብራና መጻፍ አለብን
 እናንተ ይህን ባታደርጉ እንዲ ምን ይሰበስበን ነበር እናመሰግናችኀለን!
ዲ/ን ዳንኤል በዚህ ንግግሩ «እንዲህ እንደዛሬ ቤተ ክርስቲያን ፈተና ውስጥ ስትሆን ሁለት ነገሮችን ማስተዋል ያስፈልጋል። አንደኛ ቤተ ክርስቲያን የምትቃጠለው፣ ክርስቲያኖች የሚሳደዱት እኛ ምን ስላጠፋን ነው? ወይም እኛ ምን ስላልሠራን ነው ብለን መጠየቅ አለብን? ሁለተኛ ይህ ድርጊት ወደፊት እንዳይደገምና ሥራችን ወደ ትውልድ እንዲሻገር ምን ማድረግ አለብን ብለን እንድናስብ ይረዳናል» ሲል ይጀምራል። «ይህን ባናደርግ ግን ትውልድ ይወቅሰናል። ቤተ ክርስቲያን ግን ትቀጥላለች» ሲልም አክሏል።
ለዚህም «የእኛ ሥራችን በምድር ደመወዛችን ግን በሰማይ ነው። … በቤተ ክርስቲያናችን ሥራ ላይ ማንም እንዲረዳን አንፈልግም፤ ማንም እንዲተባበረንም አንሻም የራሳችንን ሥራ ግን ራሳችን እንሠራለን … ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ኢትዮጵያን ሠርታለች። … በጸሎታችን «ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ» ሳንል የዋልንበት ጊዜ የለም» ሲልም ያወሳል። «ኢትዮጵያን ሥለናታል፣ ቀርፀናታል፣ ጽፈናታል፣ ታሪኳንም አስቀጥለናል።» ለዚህም የነላሊበላን፣  የነ አክሱምን እንዲሁም የአዲስ አበባን አድባራት በአብነት ጠቅሷል።
«ይህ ሁሉ ታሪክ ያላትን ቤተ ክርስቲያን ለማጥፋት መሞከር የሞኝ ሀሳብ ነው፡፡ ይህንንም ይዘው የተነሱ ወገኖች  ያሰቡትን ለመፈፀም ቢጥሩም እኛ ግን እንደ ምስማር ሲመቱን እንጠብቃለን፣ ሲነኩንም እንብሳለን፤ በዚህም አናዝንም፤ አናለቅስም፤ አንገታችንንም አንደፋም» ሲል ጉባኤተኛውም በጭብጨባ አጅቦታል። «ወገኖቻችን እንዳሰቡት ሳይሆን እንዳላሰቡት ሁኖ የእንጨቱን ሲያፈርሱት በውቅር፣ የውቅሩን ሲያፈርሱት በወርቅ፣ የወርቁንም ቢያፈርሱት በአልማዝ እንሠራታለን» ሲል ፈተና ለክርስቲያኖች የሚሰጣቸውን ብርታት አንስቷል::
ለዛሬው የሚሌኒየም አዳራሽ ጉባኤ መነሻ የሆነው  የምዕራብ ወለጋ እና አካባቢው አህጉረ ስብከትን ወቅታዊ ፈተና በመጥቀስ ምክንያታችን እሱ ቢሆንም ውጤቱ ግን የወለጋን ያልተነገረ ታሪክ የሚዘከርበት ለቤተ ክርስቲያን እና ለሀገርም ጭምር የሚጠቅም ሀሳብ ያላቸው ሊቃውንት መፍለቂያም እንደሆነ ታሪክ እና መረጃዎችን እየጠቀሰ ስለወለጋ መስክሯል። በመሆኑም ጉባኤው የተቃጠሉብንን አብያተ ክርስቲያን ለማሠራት፣ የተዘጉትንም ለማስከፈት ብቻ ሳይሆን ያልቆረቡትን ለማስቆረብም ጭምር ነው ብሏል።
ለዚህም የሀሳቡን አመንጭ ሊቃነ ጳጳሳት እና በጉባኤው የተገኙትን ፖትርያሪኩን አመስግኗል። ይህ ወቅት ቤተ ክርስቲያን ዘመነ ሰማዕታትን የምታስቀጥልበት፣ ያልፀኑትን የምታበረታበት እንደሆነ፤ ለዚህም ከእያንዳንዱ ምእመን የሚጠበቅ የቤት ሥራ እንዳለ ጨምሮ አብራርቷል። «ዘመኑ ቤተ ክርስቲያን ከነ አሻራዋ እና ከነ ድንቅ ታሪኳ ለቀጣይ ትውልድ የምናሻግርበት ሊሆን ይገባል» ሲል በየመሐሉ በከፍተኛ ጭብጨባ የታጀበውን ንግግሩን ቋጭቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዲ/ን ዳንኤል ቅዱሳን ፓትርያርኮች እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ እንዲሁም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና በ40 ሺህ የሚቆጠሩ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች በተገኙበት ያደረገውን ንግግር እንደ ጠብ ቀስቃሽ እና የሌላውን እምነት ለመጉዳት እንደተደረገ በማስመሰል መዘገብ የጀመሩ መኖራቸው ታውቋል። የ«ሐሩን ቲዩብ» ጋዜጠኛ የሆነው አብዱራሒም አህመድ በፌስቡክ ገጹ ዲ/ን ዳንኤል ያልተናገረውን እንደተናገረ በማስመሰል የተሣሣተ መረጃ ሲያሰራጭ ቆይቷል።
«የጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ ዳንኤል ክብረት በትላትናው እለት ጠዋት ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመወከል የኖቤል ሽልማታቸውን ቅጅ ለተለያዩ ተቋማት በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ አስረክቧል። ከሰዓት ደግሞ ሱፉን አውልቆ ነጠላውን በመልበስ ሚሊኒየም አዳራሽ [በተካሄድ] የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዝግጅት በመግኘት ዋና ተናጋሪ በመሆን ሲፎክር ተሰምቷል። ዳንኤል በንግግሩም ”እንደ [ኦርቶዶክስተናችን] ከማንም መብት አንጠይቅም የማንንም ድጋፍ አንፈልግም ራሳችን [በጉልበታችን] መብታችንን እናስከብራለን ።፡ እኛም ራሳችን ሀገርን ያቀናን ነን ራሳችን ሀገር ነን ። ሌሎቹ የእምነት ተቋሞቻቸውን የገነቡት በውጭ እርዳታ ነው እኛ ግን በራሳችን የሰራን ነን።» በማለት ጠብ ቀስቃሽ ንግግር በማድረግ ሲፎክር ተሰምቷል።» ያለው ጋዜጠኛ አብዱራሒም ዲ/ን ዳንኤል ያላለውን «በጉልበት» የምትለውን ቃል ለምን እንደጨመረ ግልጽ አላደረገም።
በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን በግል የፌስቡክ ገጻቸው ያሰፈሩት የአደባባይ ሚዲያ አዘጋጅ ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ በበኩላቸው «መብትን በሰላማዊ መንገድ መጠየቅ ለ”ድምጻችን ይሰማ” ትክክል እንደነበረው ሁሉ ለዳንኤልም ለኤፍሬምም ለ”ፀሐይሽ አትጠልቅም”ም ትክክል የማይሆንበት ምን ምክንያት አለ። ሁልጊዜ እንደምለው ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት። የበለጠ መብት አንጠይቅም፤ አንፈልግምም። ያነሰ መብትም አንቀበልም። እኩል የሆነ እኩልነትን መጠየቅ ሰብዓዊና ዜግነታዊ መብታችን ነው» ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።
ዲ/ን ዳንኤል በጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ መንግሥት ውስጥ በአማካሪነት መሥራት ከጀመረ ወዲህ በአክራሪ ብሔርተኛ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች እና ዋልታ ረገጥ አስተምህሮ በሚከተሉ የእስልምና እና የፕሮቴስታንት እምነት አራማጆች መጠነ ሰፊ ቅስቀሳ ሲደረግበት እንደቆየ ይታወቃል። «ሃይማኖተኛ ሰው ፖለቲካ ውስጥ መግበት የለበትም» የሚሉ ኦርቶዶክሶችም ዲ/ን ዳንኤልን ሲያሔሱ ቆይተዋል። በጠ/ምኒስትሩ የፖለቲካ አካሔድ እና ወንጀል በሚፈጽሙ ሰዎች ላይ ርምጃ በመውሰድ በኩል አሳይተዋል ባሉት ለዘብተኛ አቋም ምክንያት ዲ/ን ዳንኤልን የሚተቹ ሰዎችም እንዳሉ ይታወቃል።
በትእግስት ሊደመጥ የሚገባው የሙአዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት ድንቅ መንፈሳዊ መልእክት!!!
Filed in: Amharic