>
9:10 am - Saturday November 26, 2022

የአንድ ቀን ዜና - ቤልጅየም- ህንድ- የመን…(ደረጄ ደስታ)

የአንድ ቀን ዜና – ቤልጅየም- ህንድ- የመን…..

ሳዑዲ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ህልፈት ዜና!!!

ደረጄ ደስታ
ቤጅልየም ብራስልስ አቅራቢያ በሚገኘው  (A16-E42 highway) አውራ ጎዳና ላይ፣ ለዲሴምበር 20 አጥቢያ፣ ከሌሊቱ 10 ሰዓት፣ አንድ አስክሬን ወድቆ የተመለከተች ሴት ለፖሊስ አሳወቀች። ፖሊስ መጣ። ሟች በመኪና ተድጦ መሞቱ ግልጽ ስለነበር የአስክሬን ምርመራ (ኦቶፕሲ) አላስፈለገም ብሏል። በጭለማ የለበሰው ጠቆር ያለ ልብስ ከርቀት እማይታይ በመሆኑ ለአደጋው ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ፖሊስ ገምቷል። አሸካርካሪው ነስፍ አጥፍቶ አምልጧል። የሟች ኪስ ቢበረበርም ማንነቱን እሚገልጽ ምንም ነገር አልተገኘም። መታወቁ አይቀርምና የ28 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ኤርምያስ ኡርጌሳ ሆኖ ተገኘ። ከርታታው ኢትዮጵያዊ (ፎቶው ከታች) በሊቢያ በረሃ ሳይቀር አቋርጦ ስንት መከራ አይቶ ነው አውሮፓ የደረሰው። ወደ እንግሊዝ ለመዝለቅ ተስፋ ነበረው። ጥቂት ሲቀረው አደጋው አስቀረው። የአራት ዓመት ህጻን ሴት ልጁን ትቶ አልፏል። ብዙ የተነገረለት አልመሰለኝም። በአካባቢው ያሉ ኢትዮጵያውያን እርዳታ ሲያጠያይቁ እንደነበረ አንብቤያለሁ። አሸክርካሪው ባልተያዘበት ምርመራውም በዚያው እንዳይቀር እሚያስታውስ አካል ያስፈልገው ይሆናል። ኤምባሲውም ጉዳዩን አውቆት እየሰራበት ከሆነ መልካም ነገር ነው።
ይህ ዛሬ የተመለከትኩት ዜና ከሌላ አሰቃቂ ዜና ጋር በአንድ ቀን ሳነበው አንዳች ስሜት ፈጠረብኝ። የወገን አበሳው አያልቅምና ከዚያኛው በፊት አንድ አሳዛኝ ዜናም እንዲሁ ልንገራችሁ። ለስደት የተንከራተቱ ብቻ ሳይሆን ለመልካም ነገር ራሳቸውን ያጩትም ህይወት እየጠፋ መሆኑን እያስተዋልን ነው። ይህ ዓይነቱ ዜና በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየተዘወተረ የመጣ ዜና ይመስላል። ለምስሌ ህንድ ውስጥ በTelangana ግዛት በሚገኘው ኦስማኒያ ዩኒቨርስቲ  ከ2018 ጀምሮ የዶክትሬት ዲግሪውን  (የፒ ኤች ኤዲውን) ለማግኘት እጣረ ያለ የ32 ዓመት ወጣት ኢንጂነሪንግ ተማሪ በተኛበት ክፍል ሞቶ መገኘቱ ተዘግቧል። ከጓደኛው ጋር ቅዳሜ አብረው ውለው እሁድ ቀኑን ሙሉ ስልክ ሳይመልስ በመቅረቱ ስጋት ያደረበት ጓደኛው ወደ ማረፊያ ሆስቴል ክፍሉ ሲሄድ ክፍሉ ዝግ ሆኖ ያገኘዋል። ቢያንኳኳም እሚከፍት አልተገኘም። ተሰብሮ ሲገባ ወጣቱ ካሊድ ባሊ ራሱን ፊቱ ላይ ባጠቀለው ላስቲክ አፍኖ በመግደል ህይወቱን አጥፍቶ መገኘቱ ተዘገቧል። ከአንድ ወር በፊት አገሩ ኢትዮጵያ ደርሶ የተመለሰ መሆኑን ከመዘገቡ ሌላ የተሰጠ ማብራሪያ የለም። እንግዲህ አንዱ በሰው ሲጠፋ ሌላው ራሱን ሲያጠፋ በስደትና በውጭው ዓለም ብዙ ነገር እየተሰማ ነው።
የስደት ነገር ከተነሳ ከነዚህ ሁሉ የከፋና የሚዘገንነው ደግሞ ዛሬ ከወደ የመን የተሰማው ዜና ነው። ትናንት በየመን ሳዳ ግዛት ታዋቂ በሆነው የድንበር መገበያያ ቦታ Al-Raqu market የሳዑዲ አረብያ ጦር በተኮሰው የከባድ መሳሪያ 17 ሰዎች መገደላቸውን የቻይና ዜና አውታር http://www.xinhuanet.com/english/2019-12/25/c_138655455.htm ዘግቧል። ከተገደሉት 17 ሰዎች መካከል 12ቱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መሆናቸውንም ጽፏል። እነማን ይሆኑ?
Filed in: Amharic