>

ጃዋርን በፓርቲያችን በአባልነት ተቀብለነዋል!!!  (ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና)

ጃዋርን በፓርቲያችን በአባልነት ተቀብለነዋል!!!

 

 ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና 

 

ማንም ኢትዮጵያዊ የእኛ አባል ሊሆን ይችላል በግለሰብም ሆነ በህዝብ ላይ ወንጀል የሠራ እስካልሆነ ድረስ”!!!

ቀደም ሲል ፖለቲካ ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ይልቁንም ከዳር ሆኖ በአገሪቱ ለተጀመረው ለውጥ ድጋፍ ማድረግን እንደሚመርጥ ተናግሮ የነበረው ጃዋር በቅርቡ የሃሳብ ለውጥ ማድረጉን እና ፖለቲካ ውስጥ ለመግባት መወሰኑን እንደተናገረ ይታወሳል።

ፖለቲካውን ለመቀላቀል ቢወስንም ተሳትፎው በየትኛው ፓርቲ እንደሚሆን አለመወሰኑንም በወቅቱ ገልፆ ነበር።

ጃዋር ፓርቲያቸውን እንደተቀላቀለ ከቢሯቸው መረጃ የተሰጣቸው ትናንት እንደሆነ የሚናገሩት ፕሮፌሰር መረራ “ኦፌኮ እገባለሁ ብሎ ለቢሯችን ነግሯል” ብለዋል።

ከሦስት ወይም ከአራት ቀናት በፊት ፕሮፌሰር መረራ ባሉበት የፓርቲያቸውን ጽህፈት ቤት መጎብኘቱንም ገልፀዋል።

ጃዋር ወደ ኦፌኮ ለመቀላቀል ከመወሰኑ ቀደም ብሎ ከአመራሩ ጋር ያደረገው ንግግር እንደነበረ የተጠየቁት ሊቀመንበሩ “አባላት ስንመለምል ንግግር የለም፤ እሱ ራሱም እኮ እዚህ ገብቻለው ሊል ይችላል። እኛም ስብሰባ ላይ “እኛን ተቀላቅሏል” ብለን ልንናገር እንችላለን ማንም ኢትዮጵያዊ የእኛ አባል ሊሆን ይችላል የምንከለክልበት የተለየ መንገድ የለንም። በግለሰብም ሆነ በህዝብ ላይ ወንጀል የሠራ እስካልሆነ ድረስ” ብለዋል።

ጃዋር መሐመድ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ በመንግሥት ተመድበውለት የነበሩ ጥበቃዎች “እኔ ሳላውቅ ለማንሳት ሙከራ ተደርጓል” በሚል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መልዕክት ካሰፈረ በኋላ የተፈጠረውን ውዝግብና አለመረጋጋትን ተከትሎ ነበር ለምርጫ እንደሚወዳደር ፍንጭ የሰጠው።

ወደ ፖለቲካው ለመግባት መወሰኑን ተከትሎ የአሜሪካ ዜግነቱን መሰረዝ የሚያስችለውን ሂደት በቶሎ እንደሚጀምር ጃዋር በተደጋጋሚ በተለያዩ ቃለ ምልልሶቹ ጠቅሶ እንደነበር የሚታወስም ነው።

አንዳንድ የዜና ምንጮች ጃዋር ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲን ማነጋገሩንም ጭምር ገልፀዋል።

በፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ሊቀመንበርነት የሚመራው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ በፕሮፌሰሩ ይመራ በነበረው የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስና (ኦሕኮ) በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ይመራ በነበረው የኦሮሞ ፌደራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ውህደት የተመሰረተ ፓርቲ ነው

Filed in: Amharic