>

ኢትዮጲያና ዶ/ር ኢንጂኒየር ቅጣው እጅጉ (ታምሩ ተመስገን)

ኢትዮጲያና ዶ/ር ኢንጂኒየር ቅጣው እጅጉ

 

ታምሩ ተመስገን
… የዶ/ር ኢንጂኒየር ቅጣው እጅጉን ልጅ አገኘሁት። ስሙን እዚህ ላይ የማልጠቅሰውን ልጁን የመተዋወቅ እድሉ ገጥሞኛል።
በቀደም የኢትዮጲያ የመጀመሪያዋ ሳተላይት መምጠቋን ተከትሎ [ጀግናችንን እንዘክር] በሚል ርዕስ ስለ ዶ/ር ኢንጂኒየር ቅጣው እጅጉ አጠር ያለች የህይወት ዳሰሳ ማስነበቤ ይታወሳል። ይህንንም ፅሁፍ አንበቦት ደስ እንዳለውና የፎቶ ማስተካከያ እንዳደርግም በውስጥ መስመር አወራን ።
አሁን ከዚህ ዝቅ ብየ የምነግራችሁን ታሪክ ሌሎችንም ደግሞ የላከልኝ እራሱ የዶ/ር ኢንጂኒየር ቅጣው እጅጉ ልጅ ነው።
በ2010 ዓ.ም ከአንድ ሚድያ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ በተወሰኑ ክፍሎች ባስነብባችሁ ብየ ወደድኩ
“አባቴ ከእኔም ሆነ ከኢትዮጲያዊያን ብዙ ይጠብቅ ነበር።…” ይላል ልጁ የአባቱን ኢትዮጲያዊነት መንፈስ መተረክ ሲጀምር “አባቴ አንድ ኢትዪጲያዊ መላበስ ይገባዋል የሚለውን ስብእና ሁሌም ይነግረኝ ነበር። “ኢትዮጲያዊ ፈጣሪን የሚፈራና ሀገሩን የሚወድ ሰው መሆን አለበት። ኢትዮጲያዊ ቅኔ አዋቂ፣ ጀግና ጠንካራ ሰው ነው። ኢትዮጲያዊ ለሁሉም ነገር ዝግጁ የሆነ ሰው ነው።” በማለት መንፈሰ ጠንካራ ኢትዮጲያዊ እንድሆን ይመክረኝ ነበር።
አባቴ በኢትዮጲያዊነት ስርአት ነው ኮትኩቶ ያሳደገኝ። ጥብቅ ስርአትን በቤታችን እንድንከተል ያደርግ ነበር። በሳምንት ሁለት ወይንም ሶስቴ ቤተክርስቲያን እንድንሄድ ያደርግ ነበር። የተከለከሉ ምግቦችን አሳማ ወይንም የባህር አውሬዎችን በፍጹም አንበላም። ጾም ስንጾም ሁሉ አስታውሳለሁ። እኔና አባቴ በኢትዮጲያ የሚወደዱትን አቃጣይ ምግቦችን አፍቃሪ ነበርን። ቃሪያና በርበሬ ነፍሳችን ነው። በትንሽነቴ ከበርበሬ እቃ ውስጥ በርበሬ ስቅም የተያዝኩበትን ጊዜ አስታውሳለሁ።
ኢትዮጲያዊያን እንደሚያፈቅራት ሁሉ እግር ኳስን ክለባችንን እንደግፋለን። በየሄድንበት ሁሉ አባቴ ከሁሉ በፊት የኢትዮጲያ ስም በክብር እንዲነሳ ነበር የሚፈልገው። ሀገራችንን እንድንወድና እንድናስከብር ነበር የሚፈልገው።
አባቴ መታወስ ያለበት ለፈጣሪና ለሀገሩ ባለው ጥልቅ ፍቅር ለትልቅ  ደረጃ የበቃ ሰው ሆኖ ነው።”
.
የሰውየው አፍሪቃዊ ምኞት
… ይህ የዘመን ሰንደቅ ከከፋ ጠቅላይ ግዛት ከቦንጋ ከተማ እስከ NASA ድረስ ተራምዷል። ይህ ሰው የአባቱን እርፍ ጨብጦ ከቦንጋ ሰማይ ስር ከማረስ በአሜሪካ ሰማይ ስር ሮኬት እስከ ማስመንጠቅ ድረስ ተጉዟል።
ውልደቱ እ.ኤ.አ የካቲት 25 1948 ከፋ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ መሆኑን የታዘበ ሰው “እንዴት እንዴት አድርጎ ከባህርዳር ፖሊቴክኒክ ተነስቶ በጃፓን በኩል ሾልኮ NASA ውስጥ ስመ ጥር የሲስተም መሀንዲስና የጠፈረ ሳይንቲስት ሆነ!?” ብሎ ቢደነቅ አይገርምም። እዚህ ጋር አንባቢ የዚህ ሰው ከፍ ያለ ጉዞ አልጋ በአልጋ እንዳልነበርና የጥረት ውጤት ለዓላማ የመታመን ጥንካሬ ያስገኘው ስኬት እንደሆነ ሊገነዘብ ይገባል።
ይህ ሰው ለNASA ጉዞው መሰረቱን ባህር ዳር ፖሊቴክኒክ ሲያስቀምጥ ለ30 ዓመታት ለኮሌጁ ሪከርድ ሆኖ መቆየት የቻለውን ከፍተኛ ነጥብ በማስመዝገብና ከአጼ ሀይለስላሴ እጅ ሽልማት በመቀበል ነበር።
ይህ በኢትዮጲያ አየር ሀይል ውስጥ የተዋጊ ጀት አብራሪ የመሆን ህልም የነበረው ሰው የአቶ እጅጉ ሀይሌና የወ/ሮ አስካለ በላይነህ ልጅ ዶክተር ኢንጂኒየር ቅጣው እጅጉ ነበር።
እንደ አገር መዝቀጣችንን የምትረዳው ነጮች ሚት እየፈጠሩ ያልነበረ የማይኖር ታሪክ እየፈበረኩ ጀግና እየወለዱ ሕዝባቸውን ለማጀገን ደፋ ቀና ሲሉ እኛ ግን በሌላ ገፅ ጠፋንና በእኩል ደረጃ የሚያስማማን በአንድ ሚዛን የምንመዝነው ብሔራዊ ጀግና ብሎ ነገር አጣን። ሁሉም የየራሱን ጀግና በየቤቱ አድቦልቡሎ ሰርቶ ያነግሳል እንጂ እንደ አገር እንደ ሕዝብ ከነገ የሚያሻግረን አንድ አይነት ህልም አንድ አይነት ተስፋ አንድ አይነት ምስራቅ የሚያሳየን ብሔራዊ ጀግና የለንም። በዕውነቱ ግን ምን አይነት እርግማን ነው ይሄ???
ጊዜ በሰው ላይ እንጂ ሰው በጊዜ ላይ እንዳይደለው ሁሉ ምናልባት ጊዜው ሲደረስ ይህን ሰውና የመሳሰሉትን ጀግኖች ብሔራዊ ጀግኖቻችን አድርገን ትውልድ በእግራቸው ተተክቶ አገራችን ከነበረችበት ማማ ላይ ትመለስ ይሆናል ብየ አስባለሁ።
 
ልጁ ቢኒያም ቅጣው በላከልኝ መረጃ አባቱ ስለአፍሪካ የነበረውን ህልም እንዲህ ይናገራል፤
“የአባቴ ምኞትና ተስፋ ከመሰረታዊው አስተሳሰብ የተቀዳ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጲያን ከገነቡና መስዋእት ከከፈሉ የቀደሙ ነገስታት ራእይ የሚነሳ ጭምር ነው። “አይምሯቸው በቀኝ አገዛዝ ስርዓት ስር ከወደቁ ሰዎች ራስህን አርቅ እነርሱ የኢትዮጲያ ዋነኛ ጠላቶች ናቸው።” እያለ ይነግረኝ ነበር። አባቴ ኢትዮጲያና ኤርትራ ታርቀውና ተዋህደው ማየት እንደሚመኝ በአደባባይ ከመናገር ተቆጥቦ የማያውቅ ቢሆንም  በግሉ ከዚህም አልፎ ሶማሊያና ጅቡቲ ጭምር ከኢትዮጲያ ጋር እንዲዋሃዱ ይፈልግ ነበር። ይህ ኢትዮጲያ ከጎረቤቶቿ ጋር መዋሃድ ደግሞ ከራስዋ አልፎ ለአፍሪካ ቀንድ ጭምር መጠናከርና ሰላምን ያመጣል ብሎ ያምን ነበር።
አጼ ሀይለስላሴ ለኢትዮጲያ ወይም የቀድሞው የጋና መሪ ክዋሚ ንኩርማ ለአፍሪካ ይመኙ እንደነበረው ሁሉ አባቴም ለሀገሩ ኢትዮጲያ በጎ ነገሮችን ነበር የሚመኘው።
አባቴ  በሀገር ቤትም ሆነ በውጪ የሚኖሩ አፍሪካዊያን ነፃነታቸውን እንዲያረጋግጡና የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲገኙ ኢትዮጲያዊያን መታገል ይኖርብናል ይል ነበር። ሌላው ቀርቶ አፍሪካ(Afrika) እያለ ‘c’ ፊደለን በ ‘k’ በመተካት ነበር የሚጠቀመው። ይህን የሚያደርገው ደግሞ ከተስፋና ቃል በዘለለ መልኩ ለአፍሪካ ተግባር እንደሚያስፈለጋት ለማመላከት ነበር።”
ቢኒያም ስለአባቱና የአፍሪካ አንድነት ምኞቱ እንዲህ በማለት ይቋጫል
“አባቴ ከጥቁር አሜሪካዊያን ማህበረሰብ ጋር ከመነጋገርና ከመወያየት በተጨማሪ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች በመዞር ስለአፍሪካዊነትና ስለጥቁሮች አንድነትና መጠናከር የተለያዩ ሃሳቦችን አበርክቷል። በኬኒያ፣ ሱዳን፣ ሩዋንዳ፣ ዩጋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ኮንጎ፣ ካሜሩን፣ ሴራሊዮን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያና በብዙ ሀገሮች ዞሯል። በነዚህ ሀገራት በተገኘባቸው መድረኮችና ምክክሮች ሁሉ የአፍሪካን መንፈስ ከፍ የሚያደርጉ ሃሳቦችን አበርክቷል። አፍሪካዊያንና ጥቁሮች በንግድና ኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲያስተሳስሩ፣ በትምህርትና የስራ እድል በመፍጠር እንዲደጋገፉ ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። አባቴ አፍሪካን አንድ በማድረጉ ረገድ ኢትዮጲያዊያን ግንባር ቀደም ሚና እንዲኖራቸው ይፈልግ ነበር።”
.
ይቀጥላል
Filed in: Amharic