>
11:36 pm - Wednesday November 30, 2022

ኢትዮጲያና ዶ/ር ኢንጂኒየር ቅጣው እጅጉ [የመጨረሻ ክፍል - ታምሩ ተመስገን ]

ኢትዮጲያና ዶ/ር ኢንጂኒየር ቅጣው እጅጉ!!! 

(የመጨረሻ ክፍል)

ታምሩ ተመስገን
አንባቢ ሆይ የዚህን ሰው ታሪክ በወፍ በረረ በ2 ክፍል ማስነበቤ ዋናው ጉዳይ በትውልድ ላይ ቁጭትን ለመፍጠር እንዲሁም የስኬት ጉዞ ምን ያክል ፈታኝ እንደሆነና በመጨረሻ ግን ውለታ እንደማይረሳ ለመጠቆም ነው።
 
እነሆ
… በጊዜው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት የነበሩት ጂሚ ካርተር በNASA ውስጥ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽዎ የምስጋና ደብዳቤ የላኩለት ይህ የኛ ሰው በሐምሌ 16 1961 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የሰውን ልጅ ወደ ጨረቃ የወሰደችውን Apollo 11 ስያሜዋ የሆነውን መንኮራኩር ተልዕኮ ላይ  አሻራውን እንዳሳረፈ የምናውቅ ስንቶቻችን ነን?…
የኛ ሰው ከ4 ቀን ጉዞ በኋላ ሐምሌ 20 1961 ዓ.ም ኔል አርምስትሮንግ፣ በዝ አልድሪንና ማይክል ኮሊንስ የተባሉ ጠፈርተኞች ጨረቃን በእግራቸው እንዲረግጡ ድርሻውን በመወጣቱ ታሪክ ዘወትር ይዘክረዋል።
የኛ ሰው በአሜሪካ ዶክተር ኢንጂኒየር ቅጣው እጅጉ ነበር! እነሆ ጀግና ለአገሬ!
… ለዚህ ሁሉ ስኬት ለበቃውን የኛ ሰው ህይወት አልጋ በአልጋ ነበረች ብላችሁ ለምትገምቱ አንባቢያን ከህይወቱ አስቸጋሪውን ዘመን ጥቂት ጨልፌ ላካፍላችሁ፣
ልጅ ቢኒያም ቅጣው ዛሬ ላይ ሆኖ ያን የአባቱን ዘመን ሲያስታውሰው እንዲህ ይላል … “አሜሪካ ለእርሱ  ጣፋጭም መራርም ነበረች።  ይሁን እንጂ የገጠሙትን መሰናክሎች የሚቀበልበትና ለማለፍ የሚያደርገውን ጥረትም በጣም የሚደነቅ ነው። አሜሪካዊቷ  ወላጅ እናቴ ማለትም የአባቴ ባለቤት በብዙ መንገድ አባቴንና እኔን ጎድታናለች።” ቢኒያም ጉዳዩ ማብራራቱን ይቀጥላል…
“ከቤተሰቦቿ ጋር ተመሳጥራ ብዙ ግፍ ውላብናለች። በፈረንጆቹ 1989 በአንድ አጋጣሚ አባቴ ላይ የመግደል ሙከራ ሁሉ ደርሶበታል። በ1980ዎቹና 90ዎቹ ዓመታት እናቴ የአሜሪካንን ፍትህ ስርአት  ክፍተት ተገን በማድረግና የቆዳ ቀለማችንን በመጠቀም ህይወታችንን ስትበጠብጥና ዘረኝነት ስትፈጽምብን ነው የቆየችው።
በዚህ አስቸጋሪ ግፊት የተነሳ ነበር አባቴ የከፈተውን ኤክሴል ቴክ ዳይናሚኪስ የተባለውን ድርጅቱን ለመዝጋት የተገደደው። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ነበር እኔና አባቴ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድ ላይ ለመሆንና ለመቀራረብ የቻልነው።
እኔም ሆነ አባቴ ባሪያ ተብሎ መሰደብና የዘረኝነት ጥቃት ሰለባ መሆን እንዴት እንደሚለበለብ በዛ ወቅት አይተናል።
“ልጆቹን አፍኖ ወደ እስላም ሀገር ካልወሰድኩ የሚለው አፍሪካዊ መጣ”  ብሎ አንድ የፍርድ ቤት ዳኛ  ሲናገር ከአባቴ ጎን በችሎት ላይ ቆሜ ለመታዘብ ችያለሁ። ያ ዘረኛ ዳኛ ክርስቲያን አፍሪካዊ መሆናችንን እያወቀ ነበር በዘረኛ ምላሱ እንደዛ የተናገረን።
አባቴ ለእንደዚህ አይነት ጥቃት እጁን የሚሰጥ ሰው አልነበረም። የፍርድ ቤት ጭቅጭቁን ለመርታት ፍትህ ለማግኘት ሲል በሎስ አንጀለሱ ሉዮላ የህግ ትምህርት ቤት ገብቶ  ህግን እስከማጥናት ደርሷል።
ለጥናት ሲሄድ ብዙ ጊዜ አብሬው እሄድ ነበር። አንዳንዴ ቤተመጽሀፍት ውስጥ በሚያነብበት ወቅት እግሩ ላይ እንቅልፍ ይጥለኝ እንደነበር አስታውሳለሁ።
ከዚህ ሁሉ በኋላ እኔን ለማሳደግ ሙሉ መብት በህግ አገኘ። ከአንድ ዓመት ተኩል ተጨማሪ ሙግት በኋላ ደግሞ ታናሽ ወንድሜንና እህቴን የማሳደግ መብቱን በችሎት በመርታት አገኘ። ታዲያ ይህ ሁሉ የችሎት ሙግት 11 ዓመታትን ያስቆጠረ ነበር።” ይላል ቢኒያም የህይወታቸውን ከባድ ጊዜ በከፊል ሲያስታውስ።
[መጠቅለያ]
… የኢትዮጲያዊያን ማህበረሰብ ማዕከልን በገንዘብም በዕወቅትም ሲደግፍ ኢትዮጲያዊያንም የህግ ድጋፍ እንዲያገኙ ደፋ ቀና ሲል የነበረው እንዲሁም በሎስ አንጀለስ ከተማ አስተዳደር  ፌርፋክስ በሚባለው ኢትዮጲያዊያን በስፋት በሚገኙበት መንደር አካባቢ (ትንሽቱ ኢትዮጲያ) የምትባል መንደር እንድትመሰረት ፈቃድ እንዲሰጥ ያለ ስስት ጥረት ሲያደርግ የነበረው የኛ ሰው በአሜሪካ አርአያ አባት ህልመኛ ሊቅ አርቆ አሳቢ ተስፈኛ ተራማጅ ዶክተር ኢንጂኒየር ቅጣው እጅጉ በህይወት ቢኖር ኖሮ ዛሬ ላይ የ72ተኛ ዓመት ልደቱን ያከብር ነበር።
.
እግዚሐብሄር ነፍሱን በአፀደ ገነት ያሳርፍ ዘንድ ክብራቸውን የሚረዱ ኢትዮጲያዊያን ሁሉ ፀሎት ነው። አበቃሁ!
Filed in: Amharic