>

“የማይቀርልህ እንግዳ፣ አጥብቀህ ሳመው!” (አብርሃ በላይ)

“የማይቀርልህ እንግዳ፣ አጥብቀህ ሳመው!”

አብርሃ በላይ
ትህነግ በፌዴራል መንግስት ላይ ጦርነት ካወጀች 3ተኛ ቀኑን ይዟል። እንደ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ፣ ጠ/ሚ አብይ አህመድ ጦርነት ቢሸሽ ተገቢ ነው። ግን ደግሞ ጦርነት እንደ ክፉ ጥላ እየተከተለው  ነው።
ሆኖም ግን አብይ “ትህነግ ለጦር፣ እኛ ለፍቅር!” በማለት ቆርጦ የተነሳን የኢትዮጵያ ጠላት በጥሩ ቃላት ሸምግዬ እገላገላለሁ እንደማይል ተስፋ አናደርጋለን።
ይህ ፈተና የኢትዮጵያ የመኖር እና አለመኖር ጉዳይ ነው። ትህነጎች ለጦርነት ሲዘጋጁ፣ የጦርነት ሞተሩን ኃያልነት ተማምነው ነው። ያ የጦር ሞተር ደግሞ የትግራይ ህዝብ ነው።
ደርግ ለውድቀቱ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረገው የትግራይ ህዝብ ከጥቂት ባንዳዎች መለየት አቅቶት፣ ሁሉንም አንድ ላይ ልውቃውና ላጥፋው ብሎ መነሳቱ ነው።
አብይ ያን የታሪክ ስህተት እንዳይደግም የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያዊ ወገኑ እንዲቆም ቀድሞ ተከታታይ ሥራ መሰራት አለበት! በሌላ አነጋገር፣ ባንዳዎች የትግራይን ህዝብ ያሰሩበትን ገመድ አብይ በደህና መጋዝ ገዝግዞ መጣል አለበት።
ታላቁ የኢትዮጵያ መሪ አፄ ምንሊክ ከጣልያን ጋር የሚያደርጉት ጦርነት አይቀሬ መሆኑን ሲያውቁ፣ ስፋትና ጥልቀት ያለው ዝግጅት ማድረግ ነበረባቸው። ከነዚህም አጀንዳዎች አንዱ ከ10 የማያንሱ የታላላቅ ጦርነቶች ደል አድራጊ መሪ የነበሩት አሉላ አባነጋን የቀጣዩን ጦርነት አንደኛው አርኪቴክት እንዲሆኑ በክብር መጋበዝ ነበር። አሉላና ምንሊክ ቀደም ብለው ባላንጣዎች እንደነበሩ ይታወቃል። ልባሞቹ የቀድሞ መሪዎች ግን የውጭ ጠላት የመጣ ጊዜ፣ የሀገራቸውን ክብር ነበር ያስቀደሙት።
አሁንም ቢሆን፣ የሁሉም ብሄር ብሄረሰብ ፅንፈኛ መከታ የሆነችው ትህነግ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊታችን ተመታ ድምጥማጥዋ እንድትጠፋና የምንወዳት ሀገር ህልውና እንዲቀጥል፣ አብይ ድፍን የትግራይ ህዝብን ያቀፈ ሀገራዊ ዝግጅት ለማድረግ ከአሁኗ ሰዓት መንቀሳቀስ አለበት።
“የማይቀርልህ እንግዳ፣ አጥብቀህ ሳመው” ተብሏልና!
Filed in: Amharic