>

የኤርምያስ አመልጋን ጩህት ስንት ነጋዴዎች እና ሀብታሞች አድምጠዉት ይሆን?  (ሸንቁጥ አየለ)

የኤርምያስ አመልጋን ጩህት ስንት ነጋዴዎች እና ሀብታሞች አድምጠዉት ይሆን? 

ሸንቁጥ አየለ
 ኤርሚያስ አመልጋን በጣም ብዙ ጊዜ ሰምቸዋለሁ። ገና ወደ ኢትዮጵያ ቢዝነስ ሊሰራ ሲመጣም አስደማሚ የሆነ የቢዝነስ ጽንሰ ሀሳቡን በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ድርጅት ተገኝቶ ስለ ሼር ካምፓኒ ሲያቀርብ ተከታትዬዋለሁ።
ብዙ ጥያቄዎችም ሲመልስ ያስደምመኝ ነበር። በተለያዩ ሚዲያዎች ላይም ቀርቦ የቢዝነስ ህሳቤዉን ሲያንቆረቁረዉ በታላቅ አክብሮት ቁጭ ብዬ ስምቸዋለሁ።
በተበላሸ ስርዓት ዉስጥ እንኳን ቢዝነስ በመስራት ኢትዮጵያን ማገዝ ይቻላል የሚለዉን ህሳቤዉንም ደጋግሞ በልዩ ልዩ መልክ ሲያራምድ ነበር።
ከአመት በፊት ስለ ለዉጡም ታላቅ ተስፋ አንግቦ የተሻለ ፍትህ ስርዓት እየመጣ መሆኑን በመግለጽ በኢትዮጵያ ብዙ ለመስራት መነሳቱን ሲያብራራም አድምጨዋለሁ።
 የኤርምያስ አማልግን ንግግር ሁሌም እያደመጥሁ ግን አንድ ጥያቄ በህሊናዬ ይመላለስ ነበር። ሀገር በህግ የበላይነት ሳይመራስ፡ ሀገር በእኩልነት መሰረት ላይ የቆመ ስርዓት ሳይኖረዉ እዉን ቢዝነስ መስራት ይቻላል? የሚል ።
እናም ዛሬ ጃንዋሪ 1/2020 በአስራት ዜና ላይ ኤርምያስ አማልጋ በኢትዮጵያ ፍትህ ተስፋ መቁረጡን ፡ ይሄንንም የተበላሸ ፍትህ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማጋለጥ መወሰኑን እና ካሁን ብኋላ ፍትህ አገኛለሁ ብሎ ወደ ፍርድ ቤት እንደማይሄድ ያብራራበትን ዜና ሰምቼ እራሴን አንድ ጥያቄ ጠየቅሁ።
ይሄዉም የኤርምያስ አመልጋን ጩህት ስንት ኢትዮጵያዉያን ነጋዴዎች እና ሀብታሞች አድምጠዉት ይሆን? ስንቱስ ሀገራቸዉን በፍትህ፡ እኩልነት እና በተደላደለ መሰረት ላይ የቆመች ለማድረግ ገንዘባቸዉን ለመጠቀም ወስነዉ ይሆን?
 እነዚህ ጥያቄዎችን ሳስብ በራሴ የዋህነት ተገረምኩ። ለካ የኛ ሰዉ ሁሉ በራሱ ላይ ሲመጣ ነዉ በጊዜዉ ለብቻዉ የሚጮህዉ።
የራሴን ህዝብ ስነልቦና ለማወቅ የዘገዬሁ መስሎኝ አዕምሮዬ ጥያቄ መጠየቁን እንዲያቆም አባብዬ ዝም አስባልኩት። እጄ ግን እንቢ ብሎ ይሄን ከተበ።
ሆኖም ከሆነ ቦታ አንድ ድምጽ በርቀት ይሰማኛል።  “ኢትዮጵያ ህዝብሽ እረፍት እስኪያገኝ ከቶም እንቅልፍ አይወስደንም” የሚል የትዉልድ ድምጽ።
የታዋቃዊ ቢዝነስ ጠበብት ኤርሚያስ አመልጋ ቁልፍ መልዕክት ሲጨመቅ ግን ቢዝነስ ከመስራትህ በፊት ሀገር ስራ የሚል ይመስላል።
Filed in: Amharic