>

እሪ በል ኦሮሞ!!! (ያሬድ ጥበቡ)

እሪ በል ኦሮሞ!!!

ያሬድ ጥበቡ
ቁቤና ፊንፊኔ የኦሮሞ ብሄርተኝነት መቀበሪያ ይመስሉኛል። የኦሮሞ ብሄርተኞች በኢትዮጵያ ውስጥ ተከብረው መኖር ከፈለጉ ከቁቤና ፊንፊኔ መራቅ አለባቸው ብዬ አስባለሁ። ይህን ደግሞ ማድረግ የሚችለው ከብሄርተኛ ስሜት ራሱን ማግለል የሚችለው ኢትዮጵያዊ ኦሮሞ ይመስለኛል። ላስረዳ።
ቁቤ የምለው ኦሮሙኛ በላቲን ፊደልን ነው። ቁቤ የተፈጠረው የኢትዮጵያን ሃገረመንግስት የሚገዳደር የኦሮሞ ሃገረመንግስት ለመመሥረት በነበረ መቻኮል የተገኘ ቀመር ነው። የግእዝ ፊደል ከላቲኑ በተሻለ ኦሮሙኛን ሊወክልና ሊገልፅ መቻሉ፣ በጎደለበት ቦታ የግእዙ ፊደል ለመሙላት ቀላል መሆኑ (ዸ ዹ ዺ ዻ ዼ ዽ ዾ) (ማሟያው የኔ ስልክ ላይ እንኳ አለ)፣ የግእዙ ፊደል ቢያንስ ከ25 እስከ 30 በመቶ የጊዜ፣ ቀለምና የወረቀት ቁጠባን የሚያስገኝ መሆኑ (ለምሳሌ ቄሮ በቁቤ qeerroo ነው)፣ ግእዝ በሥራ ላይ ያለ ብቸኛ የአፍሪካና የአጠቃላይ የጥቁር ህዝብ ፊደል በመሆኑ ዘረኝነትን መዋጊያ ትልቁ መሳሪያችን በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ወደሌላው አፍሪካ ይዘን መሄድ ሲገባን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳንጠቀምበት ማድረግ ለነጮች ዘረኝነት መሳሪያ መሆን  በመሆኑ የኦሮሞ ብሄርተኞች ቁቤን ጥለው አፍሪካዊውን ግእዝ እስካልተቀበሉ ድረስ፣ ከቁቤ ጋር ሙጥኝ ማለታቸው የኦሮሞን ብሄርተኝነት ለዘላቂው የሚጎዳ ነው። በእንቅርት ላይ ጆሮገድፍ እንዲሉ ቁቤን በግእዝ ሳይለውጡ የኢትዮጵያ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን የሚያደርጉት ግፊት ደግሞ፣ ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያንም ቋንቋውን እንዳይመርጡትና እንዳይማሩት በማድረግ እድገቱ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ማድረጋቸው አይቀርም። ስለሆነም በረጅም ርቀት ማሰብና ዛሬ ሊደረግ የሚችለውንና በይደር የሚቀመጠውን መለየት አለባቸው ።  ለምሳሌ ከላይ ያነሳሁት ኦሮሙኛን ሃገርአቀፍ ቋንቋ ለማድረግ ዓመታትን የሚወስድ ዝግጅት፣ ሥራና ድካም ይጠይቃል።  የኦሮሞ ብሄርተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገባቸውን ክብርና ቦታ ከፈለጉ በሀይል፣ በእብሪትና በቁቤ ሳይሆን በመደራደር፣ በመግባባትና በግእዝ ቢያደርጉት የተሻለ ይመስለኛል። አለበለዚያ፣ ቁቤ የኦሮሞ ብሄርተኝነት መቀበሪያ ይመስለኛል።
ሌላው የኦሮሞ ብሄርተኝነት መቀበሪያ ፊንፊኔ ናት። አዲስአበባን ነው ፊንፊኔ የሚሏት የኦሮሞ ብሄርተኞች።  ፊንፊኔ ሥርወቃሉ ግእዝ መሆኑን የቋንቋ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ፊን አለ፣ ወደላይ ወጣ ለማለት ለፍልውሀ ምንጭ የተሰጠ ስም ነው። አማሮች ለአንዲት ፍልውሀ የሰጡትን ስም እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ ከሰጡት ስም ይበልጣል ወይም ይፀናል ብሎ ማሰብ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ጅልነት ነው። የኦሮሞ ብሄርተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ ተከብረው መኖር ከፈለጉ፣ አማሮች ለፍልውሀ የሰጡትን ስም ትተው  መጀመሪያ አዲስ አበባን ከነስሟ መቀበል አለባቸው። ሁለተኛ የአዲስ አበባ ባለቤት እኛ ብቻ ነን ከሚለው አጉራዘለል አስተሳሰባቸው መራቅ አለባቸው። ፖለቲካ መከወን የሚቻለው ጥበብ እንጂ  በመገገምና በጉልበት የፈለጉትን የመጫን እብሪት አይደለም። ደግሞም የፈለጉትን ሁሉ በአንዴና ዛሬውኑ ካልተገኘ ማለት ጨቅላነት ነው። የኦሮሞ ብሄርተኞች ዛሬ ማግኘት የሚቻለውን የዛሬ 25ና 50 አመት መገኘት ከሚችለው መለየት አለባቸው።
አዲስ አበባን የኦሮሞ ለማድረግ በሚያደርጓቸው ተግባራት የኦሮሞ ብሄርተኞች የአዲስ አበባ ባለቤትነቱን አሳልፎ ከማይሰጣቸው ኢትዮጵያዊ ሁሉ እየነጠላቸው ነው። በቡራዩ ጭፍጨፋቸው አንድን የደቡብ ብሄረሰብ ነጥለው ለማጥቃት ያደረጉት ጭካኔ ያስተላለፈው መልእክት ጥልቅ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። በአይነቁራኛ እየተጠበቁ ነው። አዲስአበባን ኦሮሞ ማድረግ አይችሉም፣ ይበልጥ ከቡራዩ ወደከፋ ወንጀል የሚያስገባቸውን ሲኦል ነው የሚፈጥሩት። ከዚህ ሲኦል ደግሞ ሆን ብለውና አስበውበት መራቅ አለባቸው። አለበለዚያ አዲስአበባ የኦሮሞ ብሄርተኝነት መቀበሪያ ይሆናል።
የኦሮሞ ብሄርተኞች ባህላቸውንና ቋንቋቸውን የበላይ ለማድረግ በሚያደርጉት ጥረት የሌሎችን ማፈን፣ አላስፈላጊ ውድድር ውስጥ መግባት፣ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን በሃገራቸው ላይ ማግለል ወዘተ ተግባራት ውስጥ ይሰማራሉ። እነዚህም ውለው አድረው የኦሮሞ ብሄርተኝነትን በሐይማኖት፣ በአውራጃና  አስተሳሰብ ከፋፍሎ ይበታትነዋል።  ስለሆነም የተሻለው መንገድ፣ የኦሮሞ ብሄርተኝነት አዲስአበባን ለቀቅ አድርጎና ለባለቤቶቿ ለኢትዮጵያውያን ትቶ፣ የት ቦታ ብከትም ነው እውነተኛ የሆነ በቋንቋም በባህልም ወጥነት ያለው የኦሮሞ ከተማ መፍጠር የምችለው ብሎ መምከር ይኖርበታል። ባለፉት 40 ዓመታት ከተፈበረኩት የሀሰት የኦሮሞ ልቦለዶች ራሱን አርቆ በእውነተኛ ማንነቱና በቃሉ ባቆየው ትውፊቱ ላይ ተመስርቶና ከአማራና ኢትዮጵያ ብሄርተኝነቶች ጋር የእልህና የእበልጣለሁ አጉል ስሜት ውስጥ ሳይደፈቅ እውነተኛ የኦሮሞ ልቦናውን የሚያገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይኖርበት ይመስለኛል። ይህንንም የልቦናውን ፈርጥ መርምሮ ለማግኘት ከአዲስአበባ እንዲያውም ከሸዋ በብዙ ኪሎሜትሮች ራሱን ማራቅ ይገባው ይመስለኛል። ምናልባትም ለኢስላሚክ ኦሮሚያ በምስራቅ አንድ የኦሮሞ ክልል ከተማ፣ በምእራብ ደግሞ ሌላ ሁለተኛ ከተማ ያስፈልገው ይሆናል። ይህን ለማድረግ ሲቆርጥ ይመስለኛል የኦሮሞ ብሄርተኝነት የተሻለ የሚያድገውና ከሌሎች ጋር በመተናኮስና በመናከስ ሳይሆን በነፃነት ማደግ የሚችለው። ሥነፅሁፉ፣ ድራማው፣ ፊልሙ፣ ሚዲያው ወዘተ ተመንድጎና ጉልበት አግኝቶ ሃገርአቀፍ ሀይል ለመሆን የሚችለው ይህን ዝግጅት ካጠናቀቀ በኋላ ይመስለኛል። ይህ ዝግጅትም በትንሹ 25 ዓመታት አለበለዚያም 50 ዓመታት ሊወስድ ይችላል። ይህን አይነት አርቆአሳቢነትን ትቶ አዲስአበባን ወደፊንፊኔነት ለማሳነስ መሥራት ይሻለኛል ብሎ ከወሰነ፣ ፊንፊኔ የኦሮሞ ብሄርተኝነት መቀበሪያ ትሆናለች። መዳኛም የለውም። ከዚህ ይሰውረን በሉ!
Filed in: Amharic