>
5:13 pm - Tuesday April 20, 4528

ኦ.ፌ.ኮ ከ ኦ.ነ.ግ  ተቀላቀለ!

ኦ.ፌ.ኮ ከ ኦ.ነ.ግ  ተቀላቀለ!!!

ነአምን አሸናፊ

 

በቅርቡ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጃዋር መሐመድን በአባልነት የተቀበለው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና ከኦሮሞ ብሔራዊ ፓርቲ (ኦብፓ) ጋር በጥምረት ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ፡፡

የሦስቱ ፓርቲዎች ሊቃነ መናብርት ስምምነቱን ዓርብ ዕለት ታኅሳስ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. የተፈራረሙ ሲሆን፣ ቅዳሜ ታኅሳስ 25 ቀን 2012 ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው አዲሱ የኦፌኮ ቢሮ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ደግሞ አቶ ጃዋር የአባልነት መታወቂያውን ከፓርቲው ተረክቧል፡፡

የጥምረት ስምምነቱን በኦፌኮ በኩል የፓርቲው ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)፣ በኦነግ በኩል ሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ ኦብሳ፣ እንዲሁም ኦብፓን  በመወከል ደግሞ የፓርቲው ሊቀመንበር ከማል ገልቹ (ብርጋዴር ጄኔራል) ፈርመዋል፡፡

ሦስቱ ፓርቲዎች የተፈራረሙት የጥምረት ስምምነት በተለይ ዘንድሮ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ጠቅላላ ምርጫ፣ በኦሮሚያ ክልል አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ያለመ ነው፡፡

ጥምረቱ ለኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት በጋራ ዕጩዎችን በማቅረብ ለመወዳደር የሚያስችላቸው እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃም ከሌሎች ተመሳሳይ ፕሮግራምና ዓላማ ካላቸው ፓርቲዎች ጋር ጥምረት በመፍጠር በአገር አቀፍ ደረጃ ተመራጭ ሆኖ ለመሥራት መታቀዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

‹‹ትብብር ለዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም›› የተሰኘው የሦስቱ ፓርቲዎች ጥምረት የተለያዩ ዕቅዶችን ማውጣቱን አስታውቋል፡፡ በተለይም ዘንድሮ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ምርጫ ውጤት መሠረት ክልላዊ ጥምር መንግሥት መመሥረት፣ መጪው ምርጫ ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን በጋራ ማረጋገጥ፣ በምርጫ ዘመቻ ወቅት የገንዘብና የቁሳቁስ አቅምን በጋራ መጠቀም፣ እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ አቋም ከሚያራምዱ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመሥራት የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች ውስጠ ፓርቲ ሕገ ደንብ፣ መተዳደርያና አደረጃጀትን በተመለከተ ሊከናወኑ ስለሚገቡ ሥራዎች፣ እንዲሁም አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ነጥቦችም በስምምነቱ ተካተዋል፡፡

ሦስቱ ፓርቲዎች በጥምረት ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሕጋዊነት በተመለከተ፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዕውቅና ጥያቄ ማቅረባቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኦፌኮ ከዚህ ቀደም የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረንስ (ኦሕኮ) እና በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ይመራ የነበረው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ተዋህደው የመሠረቱት ፓርቲ ሲሆን፣ ኦነግና ኦብፓ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ፣ ወደ አገር ቤት ከተመለሱ ፓርቲዎች መሀል የሚጠቀሱት ናቸው፡፡

Filed in: Amharic