>
5:38 pm - Monday May 16, 2022

በመለሲዝም አስተምህሮ የናወዘው ነጩ ፕሮፌሰር!!! (ብሩክ አለሙ)

በመለሲዝም አስተምህሮ የናወዘው ነጩ ፕሮፌሰር!!!

 

ብሩክ አለሙ
የዶክትሬት ዲግሪያቸውን መመረቂያ ጽሁፍ በኢትዮጵያው ጀግና ራስ አሉላ አባ ነጋ ሰርተዋል፡፡ እኚህ ሰው ፕሮፌሰር ሐጋይ ኤልሪች ይባላሉ፡፡ ዘገባችን የፕሮፌሰሩን ታሪክ ለማብዛት ወይንም የህይወት ታሪካቸውን ለመከተብ አይደለም፡፡ ይልቁንስ የዚህ ጽሁፍ አላማ የግለሰቡን በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ታሪክ የማዛባት አባዜ ለአንባቢ ለማድረስ ነው፡፡
ከአመታት በፊት ከዚህ አለም በሞት የተሰናበቱት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ አብዛኞቹ በአምባገነንነት የሚከሷቸው መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ የመቶ አመት ታሪክ ብቻ ያላት አገር አድርገው አቅርበዋት ነበረ፡፡ መለሰ ዜናዊ የውስጥ ቀጋ የውጭ አልጋ ተብለውም ይጠሩ ነበረ፡፡ በውጪ ሃይላትም በተለይም በምእራባውያን አስታዋይ የልማት ሰው ተብለው ይጠሩ ነበረ፡፡
ከነዚህም አንዱ አድናቂያቸው የእስራኤላዊው ፕሮፌሰር ሐጋይ አንዱ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር ሓጋይ አቶ መለስን ከማድነቅ በላይ የሄዱ ይመስላሉ ለዚህ ማስረጃ በቢሮአቸው በትልቁ ግድግዳ ላይ የተሰቀለው የሟቹ መለስ ዜናዊና የፕሮፌሰሩ ምስል ይታያል፡፡ በቅርብ የሚያውቋቸውም ሃዘኑ እንደጎዳቸው ይናገራሉ፡፡
ፕሮፌሰር ሓጋይ ኢትዮጵያን ነክ ጉዳዮች ከአራት የማያንሱ መጽሃፎችን የጻፉ ሲሆን በርካታ አጫጭር መጽሃፎችም ከትበዋል፡፡ መጻፉ ባልከፋ ችግሩ ወዲህ ነው፡፡ ከ80 ብሄረሰቦች ባለበት ሃገር ውስጥ የፕሮፌሰሩ ጽሁፍ አዘውትሮ የሚያጠነጥነው የትግራይ እና የአማራ ልዩነት አጉልቶ በማውጣት ያጠነጠነ መሆኑ ብቻ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊው ኦሮሞው ወላይታው ጉራጌው ከምባታው ሃዲያው ሃረሬው አኙዋኩ ለሳቸው ምንም ማለት አይደለም፡፡ ጽሁፋቸው በአጠቃላይ ፋሺስት ኢጣልያንና እንግሊዚ ጥለውልን በሄዱት ሂሳብ ዘር ላይ ያተኮረ መሆኑ ብቻ ነው፡፡
ለፕሮፌሰሩ ነጻነት ስለእኩልነት ስለዲሞክራሲ መጠየቅ ማለት ልዩነቶች በአጠቃላይ የትግራይና የአማራ አድርጎ መጻፍ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ አጠናው በዛውም መመረቂያ ጽሁፍ ሰራው ከሚል የማይጠበቅ ነው፡፡
የቅርብ ጊዜ ታሪካችንን የምርጫ 97 (2005) በተመለከተ እንኳን እንደታሪክ ተመራማሪነት ሳይሆን በተለይም የኢትዮጵያን ታሪክ እንዳጠና ፕሮፌሰር ሳይሆን እንደ ዜና ዘጋቢ ከአንድ ወገን ብቻ የቀረበላቸውን ታሪክ በመዘገብ ምሁራዊ ትንተና ሳያቀርቡ ዘለውታል፡፡
እንደሚታወቀው በምርጫ 97 ሚሊዮኖች የዲሞክራሲ የነፃነት የፕሬስ እና የተለያዩ መብቶች የጠየቁበትን ክስተት አሳጥረው ልዩነቶቹ በአማራና በትግራይ ብሄር ልዩነት የተከሰተ አድርገው በወቅቱ በአያድ ድረ ገፅ በተለቀቀ ጽሁፋቸው ለቀውት ነበረ፡፡
በወቅቱ በዛ ቁጣ እና ህዝባዊ ማእበል በመንግስት ታጣቂዎች በግፍ የተገደሉትን የገዢውን ፓርቲ ዘገባ እንዳለ በመቀበል ቁጥራቸው 45 መሆኑን ዘግበው ነበረ፡፡የገዢው መንግስት እራሱ አጣሪ ኮሚሽን አቋቁሞ ከ200 ሰዎች በላይ መገደላቸውን በጊዜው ለህዝቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡የዚህ ፅሁፍ አላማ መነሻ የሆነው በቅርቡ አኚህ ፕሮፌሰር በታሪክ ተመራማሪነታቸው ላበረከቱት ስራ በመሸለማቸው ከበርካታ እስራኤላውያን ምሁራን ለሸላሚው ድርጅት ተቃውሞ ማቅረባቸውን በተመለከተ ነው፡፡
ከእስራኤል የታወቁ  ሁለት በኢትዮጵያ ጉዳይ ምርምር ያካሄዱ ምሁራን አሏት፡፡ አንደኛው ሞርደካይ አቢር (Mordechai Abir) የሚባሉ ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ ከላይ ስማቸው የተገለፀው ፕሮፌሰር ሃጋይ ኤልድሪች ናቸው፡፡
ሞርደካይ አቢር ከፃፏቸው እና ኢትዮጵያዊያን አበክረው የሚስማሙባቸው መፃሃፍት በዘመነ መሳፍንት ዙሪያ የተጻፉ ናቸው፡፡ “The era of princes”, “Ethiopia and the Red sea” የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በኚህ ምሁር የተጻፉ ፅሁፎች ከሞላ ጎደል ሚዛናዊ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡
ሌላው አወዛጋቢ ምሁር በመግቢያችን ላይ የገለጽናቸው ፕሮፌሰር ሃጋይ ኦልሪች ናቸው፡፡ ታሪክነ እንደፈለጉት እያገለባበጡ በመፃፍና አወዛጋቢ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ “The Grandchildren of Abraha” በሚል ርእስ ጽሁፍ አላቸው፡፡ የአሁኖቹ የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ታጋዮችን የአብርሃ የልጅ ልጆች ናቸው ይሏቸዋል፡፡ አብርሀ ነቢዩ መሃመድ በተወለዱበት ዘመን የመንን ሲገዛ የነበረው የአክሱም ንጉስ እንደራሴ ነው፡፡ ይህንን ሃቅ ስለሰውየውም ለማጣራት በስማቸው የተፃፉ መፅሃፍትን አንባቢያን እንዲያነቡ እንመክራለን፡፡
Filed in: Amharic