>
2:15 am - Tuesday December 7, 2021

"ለዩኒቨርሲቲዎች የተዘጋጀው የታሪክ ሞጁል፣ ታሪክን በከፍተኛ ደረጃ የሚያዛባ ነው" ዶ/ር መንግስቱ ጎበዜ  

“ለዩኒቨርሲቲዎች የተዘጋጀው የታሪክ ሞጁል፣ ታሪክን በከፍተኛ ደረጃ የሚያዛባ ነው”

ዶ/ር መንግስቱ ጎበዜ  
በጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ
* የአገርህን ታሪክ አገርህን የሚጠላ ሰው ሲፅፈው የሚከተለውን ይመስላል!
* ያለ ማስረጃ የሚጻፍ ታሪክ ሕይወት የለውም! 
* ከ3ሺ ዓመት በላይ የዘለቀ የመንግስትነት ታሪክን ይንዳል!
* ኢትዮጵያን ከቅኝ ግዛት ጋር የሚያገናኝ ሰነድ ነው!
.
በዩኒቨርሲቲዎች ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ›› Ethiopian History የተሰኘ ትምህርት መስጠት ከቆመ ብዙ አመታት ተቆጥረዋል:: ምክንያቱ ደሞ የታሪክ ማስተማሪያ “ሁሉን አካታች አይደለም” በሚል ነው ፡፡ ከሰሞኑ ታዲያ በዩኒቨርሲቲዎች የተቋረጠውን የታሪክ ትምህርት ለመጀመር በሚል “የኢትዮጵያና የምሥራቅ አፍሪካ ታሪክ ማስተማሪያ ሞጁል” በአራት የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች ተዘጋጅቶ ለውይይት ቀርቧል፡፡ የአሁኑ ሞጁል ሁሉን አካታች ይሆን? ከቀድሞው በምን ይለያል? ሞጁሉ ከተለያዩ የታሪክ ምሁራን የሰላ ትችት እየቀረበበት ሲሆን የታሪክና አርኪዮሎጂ ጥናት ባለሙያው ዶ/ር መንግስቱ ጎበዜ፤ ሰነዱ በአምስት ጉዳዮች ላይ ችግር ይስተዋልበታል ሲሉ ይተቻሉ፡፡
.
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በታሪክ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአርኪዮሎጂ፣ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በታሪክ ዘመን አርኪዮሎጂ ያገኙትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂና የቅርስ አስተዳደር መምህር የሆኑት እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያና ፈረንሳይ የቅርስ አድን ትብብር ፕሮጀክት፣ የኢትዮጵያ አስተባባሪው ዶ/ር መንግሥቱ፤ አዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በአዲሱ የታሪክ ትምህርት ሞጁል ዙሪያ ሰፊ ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡
.
አምስት ዋና ዋና ችግሮች፦
ይሄ የታሪክ ማስተማሪያ ሰነድ በኔ እይታ፤ አምስት ጉዳዮች ላይ ችግር የሚስተዋልበት ነው፡፡
.
የመጀመሪያው ትልቁ ችግር፤ ሠነዱ፣ የጋራ የምንለውን ሀገራዊ ታሪክ አኮስሶ፣ የየአካባቢውን በተለይም የተወሰኑ ህዝቦች ታሪክ አድርጐ ያስቀምጣል፡፡ ትልቁን ታሪክ አኮስሶ፣ የየአካባቢውን ታሪክ የሚያደምቅ ነው::
.
በአጠቃላይ ሞጁሉ የኢትዮጵያ ታሪክ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያን ታሪክ በሞጁሉ ውስጥ ፈልጐ ለማግኘት የሚያስቸግር ነው፡፡ በሞጁሉ መግቢያ ላይ ፀሐፊዎቹ “ኮርሱ አካታችና ወካይ እንዲሆን በየዘመናቱ ያሉ ክልላዊ ወይም አካባቢያዊ ታሪኮች ተካተውበት ይገኛል” ይላል:: እንግዲህ ገና ከመሠረቱ አላማው ይሄ ነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እነሱ አካታችና ወካይ እንዲሆን›› ቢሉትም፤ የተዘጋጀው ሞጁል ግን አካታችም ወካይም አይደለም፡፡ እጅግ በጣም የሣሣ፣ ወደ አንድ ማህበረሰብ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ፣ የጋራ ሀገራዊ እሣቤ አይታይበትም፡፡  የተወሰኑ አካባቢዎች ጉዳይ በዝርዝር፣ ሌሎች ደግሞ በግርድፉ የቀረቡበት ሞጁል ነው፡፡
.
ሁለተኛው ችግር ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ለመግለጽ የሞከረበት አሉታዊ መንገድ ነው፡፡ በአብዛኛው የቀደመ አስተዋጽኦዋን፣ ሚናዋንና ሀገራዊ ድርሻዋን በመደበቅ፣ ለአሉታዊ ጉዳዮች ትኩረት የሚሰጥ ሰነድ ነው፡፡ ይሄ በአብዛኛው የሚታይ ችግር ነው፡፡ ለምሣሌ የሃይማኖቶች አጀማመርና መስፋፋትን በሚያወሳው ክፍል ሠፊ ትንታኔ የሚሰጠው፤ በባህላዊ ሃይማኖቶች ላይ ነው፤ በተለይ ደግሞ በኦሮሞ ህዝብ የዋቄፈታ ጉዳይ ላይ ሠፊ ሽፋን ይሰጣል፡፡ በአንፃሩ በክርስትና ሃይማኖት ጉዳይ ላይ የሚሰጠው ሽፋን በጣም አናሣ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሃይማኖት ታሪክ ውስጥ በቂ ማስረጃ ያለውና በስፋት መተንተን የሚችለው ክርስትና ቢሆንም የቀረበበት መንገድ ግን ክርስትናን የሚያኮስስ ነው፡፡  ለምሳሌ፡- የቤተ እስራኤል አይሁድ እምነት ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን ይገልጽና፣ ነገር ግን የታወቀው በ4ኛው ክ/ዘመን ‹‹አይሁዳውያን ወደ ክርስትና ለመቀየር አንፈልግም ብለው ተቃውሞ ሲያሰሙ ነው” ይላል፡፡ ስለዚህ “የእነሱ ህልውና የታወቀው ክርስትናን እምቢ ብለው በጉልበት አንጠመቅም ሲሉ ነው›› በማለት ይገልጻል፡፡ ነገር ግን ይሄን የሚደግፍ” ማስረጃ በትክክል አልተቀመጠም:: በተጨማሪም የአይሁድ ሃይማኖትን በዚህ መልኩ መግለጽ እጅግ በጣም ነውር ነው፡፡ አግባብ አይደለም፡፡
.
ሌላው እጅግ አደገኛ አገላለጽ የሆነው፡- የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወደ ደቡብና መካከለኛው ምስራቅና ምዕራብ የተስፋፋችው የክርስቲያን መንግስትን ተከትላ ነው፤ የክርስቲያኑ መንግስት አስገድዶ በሃይል ቦታዎችን ሲቆጣጠር፣ ቤተ ክርስቲያኒቱም በሃይል የተቆጣጠሩትን ቦታ ተከትላ የክርስትና ሃይማኖትን እንዳስፋፋችና ክርስትና ከሰሜን ወደ ሌሎች አካባቢዎች የተስፋፋው በጉልበት፣ በሃይልና በወታደራዊ እገዛ መሆኑን ያትታል:: እንደውም አንድ ቦታ ላይ “በግድ የመቃብር ቦታቸውን በመነጠቃቸው ሳይፈልጉ የተዋህዶ ሃይማኖትን ለመቀበል ተገደዋል” ይላል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በዚህ መልኩ እንደተስፋፋች ያስቀምጥና እዚያው ላይ ከእስልምና ጋር በተያያዘ ደግሞ የእስልምና ሃይማኖት ወይም የመጀመሪያዎቹ የነብዩ መሐመድ ተከታዮች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የተቀበላቸው ንጉስ አልነጃሺ፤ ወደ እስልምና ሃይማኖት መቀየሩን ትውፊታዊ የአረብና የመሳሰሉት ማስረጃዎች ይገልጣሉ” ይላል፡፡ በዚህ መሠረት እስልምና ወደ አፍሪካ ቀንድና ወደ ኢትዮጵያ የገባው በጀሃድ ሣይሆን በሠላማዊ መንገድ ነው ይላል፡፡ የተሰነደ ታሪክ ያላትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ግን በጉልበትና በሃይል የገባች አድርጐ ይገልፃል::
.
ይሄን ስንመለከት በአጠቃላይ ሞጁሉ፤ ማስረጃ ያለውን ጉዳይ አንኳሶ፣ ማስረጃ የሌለውን ጉዳይ አጉልቶ በማስቀመጥ፣ ታሪክን በከፍተኛ ደረጃ የሚያዛባ ነው፡፡
.
ከዚሁ ከቤተ ክርስቲያኑ ጋር በተያያዘ በሞጁሉ ከሠፈረው መካከል የአሩሲ፣ የባሌ፣ የሀረርጌ ህዝቦች እስልምናን የተቀበሉበት ዋነኛ ምክንያት፤ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን መቃወማቸውን ለመግለጽ ነው” ይላል፡፡ ይሄ በጣም ምክንያታዊ ያልሆነ፣ ከእውነታ የራቀ አገላለጽ ነው፡፡ የሚገርመው በሞጁሉ የተቀመጡ ስዕሎች ሣይቀሩ ሚዛናዊነት የጐደላቸው ናቸው፡፡
.
ሌላው አስነዋሪ ነገር ደግሞ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው በግብጽ በኩል መሆኑን ይገልፃል፡፡ እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ክርስትናን ከግብጽ አላመጣችም፡፡ እንደውም ክርስትናን ከተቀበሉ የአለም ሀገሮች ውስጥ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያ ናት፡፡ በዚህ ረገድ በቂ ማስረጃዎች አሉ፡፡ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ከግብጽ የመጣው ጳጳስ እንጂ የክርስትና ሃይማኖት አይደለም፡፡ ጳጳሱም ቢሆን ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ ግብጽ ተልኮ ጳጳስ ሆኖ የመጣ ነው፡፡ እኒህና ሌሎች በርካታ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚያኮስስ፣ ማንነቷን የሚያጥላላ ተረክ በሞጁሉ ተቀምጧል፡፡
.
ሶስተኛው ጉዳይ፤ የማዕከላዊ መንግስቱን የማኮሰስ ነገር ነው፡፡ እንደውም ማዕከላዊ መንግስቱን ጥላሸት የመቀባት አዝማሚያ ይታይበታል፡፡ በዚህ ሰነድ ውስጥ ማዕከላዊ መንግስት እንዳልነበረ ሆኖ ተቀምጧል ማለት ይቻላል፡፡ ለምሣሌ “የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ የተገነባው ከሌሎች ጋር ባለ የንግድ፣ የስደት፣ የጦርነት፣ የባሪያ ንግድ፣ የቅኝ አገዛዝና በመሳሰሉት ነው” ይላል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት የተገነባው በቅኝ ግዛት እንደሆነ አድርጐ ጭምር ይጠቅሳል፡፡  ይሄ የኢትዮጵያን ከ3ሺህ አመት በላይ የዘለቀ የመንግስትነት ታሪክ የሚንድ ነው፡፡ ቀጥታ ከቅኝ ግዛት ጋር የሚያገናኝ እጅግ በጣም “ሃሰተኛ” ሞጁል ነው::
.
ከዚህ ጋር በተገናኘ “በመስቀል ጦርነት ጊዜ የግብፁ ንጉስ ሣለሃዲን በርካታ ቦታዎችን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሰጠ” ይልና ምክንያቱን ሲያስቀምጥ፤ “የኢትዮጵያ የክርስቲያን መንግስት ከአውሮፓ የክርስቲያን መንግስት ጋር እንዳይተባበር ለማድረግ ነው” ይላል፡፡
.
እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን ነው ማንሳት የምፈልገው፡፡ በመሠረቱ የመስቀል ጦርነት በመካከለኛው ዘመን የነበረ ትልቅ ክስተት ነው:: ሣላሃዲን የነበረበት ዘመን እኛው የመስቀል ጦርነት የተካሄደበት ነው፡፡ በወቅቱ ሳላሃዲን በእየሩሣሌም የነበሩ ክርስቲያኖችን አባሮ እየሩሣሌምን የተቆጣጠረበት ጊዜ ነው፡፡ በዚያ ዘመን የነበረው የኢትዮጵያ ንጉስ ደግሞ ቅዱስ ላሊበላ ነው፡፡ ይህ ዘመን ታላላቅ የኢትዮጵያ ነገስታት የነበሩበት፣ ኢትዮጵያ በአለም ደረጃ ከፍ ብላ የምትታይበት ዘመን ነበር፤ ተጽዕኖዋም ጎልቶ የሚታይበት ነው። በዚህ ወቅት የግብፁ ሳላሃዲን ጦርነቱን ካሸነፈ በኋላ ለኢትዮጵያ (ቅዱስ ላሊበላ) በጣም በርካታ ቦታዎችን በኢየሩሳሌም ሰጥቷል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በነበረው ዲፕሎማሲያዊ ታሪክ ኢትዮጵያውያን በኢየሩሳሌም የመኖሪያ ቦታ እንዲኖራቸው ሁሉ አድርጓል። ወደ ኢየሩሳሌም ሲገቡ ግብር እንዳይከፍሉ ያደረገ ሰው ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ስጦታ የተሰጠው ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተለይቶ ሳይሆን ለአገረ ኢትዮጵያ ነው፡፡ በሞጁሉ የቀረበበት መንገድ ግን ይሄን ወደ ቤተክርስቲያ ደረጃ አውርዶ ነገሩን ለማሳነስ የሚሞክር ነው::
.
ሌላው የዘመን አቆጣጠር ጉዳይ ነው፡፡ አሁን የምንገለገልበት የዘመን አቆጣጠር መቼም በአፍሪካም በአለምም መለያችን የሆነ ነው። ነገር ግን ይህ ሞጁል ይሄን የሚያቀርበው በተለየ መንገድ ነው፡፡ የዘመን አቆጣጠርን  ሲተርክ የኦሮሞ፣ የሲዳማ፣ ይልና የኤርትራና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የዘመን አቆጣጠር ብሎ፣ የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር አኮስሶ አሳንሶ ያቀርበዋል፡፡ አገራዊ መሆኑ ቀርቶ የቤተ ክርስቲያን አድርጎ አስቀምጦታል፡፡ ይሄ ትልቅ ኢትዮጵያዊ የሆነን ነገር ማሳነስ ነው፡፡ ያኔኮ ኢትዮጵያና ኤርትራ የሚባል ነገር እንኳ አልነበረም፡፡ በዚህ ደረጃ የወረደ ሞጁል ነው:: ሌላው የኢትዮጵያ ወታደርን “የክርስቲያን ወታደር” እያለም አሳንሶ ለአንድ ወገን ሰጥቶ ያስቀምጠዋል፡፡
.
በአጠቃላይ ይሄ ሞጁል ከሶስት ተቋማት ጋር ጥላቻ አለው- ከክርስቲያኑ መንግስት፣ ከቤተ ክርስቲያንና ሴሜቲክ ተብሎ ከሚጠራው ሕዝብ ጋር ችግር ያለበት ሞጁል ነው፡፡  ሌላው ዘመናዊት ኢትዮጵያ የተገነባችው የተበታተኑ መንግስታትን በጉልበት በማስገበር ነው ይላል፡፡ “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሆኖ የወጣችው በ1900 አካባቢ ነው” በማለት ይገልፃል፡፡ ይሄ ማለት ከዚያ በፊት ኢትዮጵያ የምትባል አገርና መንግሥት (የኢትዮጵያ መንግስት) የለም ማለት ነው። ሞጁሉ በዚህ መነፅር ነው ጉዳዩን የሚያስቀምጠው፡፡ ሌላው ‹‹ሚኒልክ ወደ ደቡብና ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያደረገው ዘመቻ በዋናነት መሬትን፣ የተፈጥሮ ሃብትን፣ የንግድ መስመርን ለመቆጣጠር አላማ ያደረገ ነበር›› ይላል፡፡
.
ሚኒልክ ይሄን ዘመቻ ያደረጉት ግን ቅኝ ገዢዎች ወደ አካባቢዎች ከመስፋፋታቸው በፊት ቦታውን ቀድመው በመቆጣጠር፣ ከለላ ለመስጠትና ድንበር ለማበጀት ነው፡፡ ዋናው አላማ ይሄን ነበር:: ይሄ የመስፋፋት፣ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ እንዳለ አድርጎ ማቅረብ፣ እጅግ በጣም ነውር የተሞላበት ድርጊት ነው:: ጋር በተገናኘ “በሚኒልክ መስፋፋት ወቅት በተለይ እነ ራስ ጎበና ወደ አርሲ ባደረጉት ዘመቻ በሚገርም ሁኔታ ባዮሎጂካል መሳሪያ ተጠቅመዋል። የፈንጣጣ በሽታ እንዲስፋፋ አድርገዋል፡። የሴቶችን የቀኝ ጡትና የወንዶችን የቀኝ ከንፈር በመቁረጥ ወንዶችን የማኮላሸት ሥራ ተሰርቷል” ይላል፡፡ ዝቅ ብሎ ደግሞ “በወላይታና ሌሎች አካባቢዎች በግልጽ ጄኖሳይድ ተፈፅሟል›› ይላል። ይሄ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ታሪክ ማቀራረቢያ መሆን ሲገባው የበለጠ ማለያያ ሆኖ ተዘጋጅቷል፡፡
.
አራተኛ፤ ሚዛናዊ ባልሆነ መልኩ የአንድን ሕዝብ ታሪከ ማጉላት ነው፡፡ በእውነቱ የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ የሁላችንም ታሪክ ነው፤ ግን መፃፍ ያለበት ማስረጃ በተገኘለት ልክ ነበር፡፡  ሞጅሉ አባ ባህሪ ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ያቀረቡትን ታሪክ ይወቅሳል፡፡ የኩሽ ህዝቦችን በተመለከተ በሚናገረው ላይ በተለይ የኦሮሞ ህዝቦች በመላው ኢትዮጵያ ይኖሩ እንደነበር ያስቀምጣል፡፡ በሰሜንም፣ በምዕራብም፣ በምስራቅም በደቡብም የኖሩ ጥንታዊ ህዝቦች እንደነበሩ ያስቀምጥና ሌሎች ህዝቦችን ደግሞ በቦታ ገድቦ ያስቀምጣቸዋል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ በመላው ምስራቅ አፍሪካ ይኖሩ እንደነበር ያለ ምንም ማስረጃ ያትታል፡፡ ይሄ ትክክለኛ አይደለም፡፡ በጣም የሚገርመው ነገር፤ የኢትዮጵያን የህዝብ ቁጥር ይገልጽና ዝቅ ብሎ ቋንቋዎችን በተናጋሪዎች ብዛት ያስቀምጣል:: በዚህም የአፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች፤ 33.8 በመቶ፣ የአማርኛ ተናጋሪዎች፤ 29.33 በመቶ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አማርኛ የሚናገረው የአማራ ህዝብ ብቻ ነው እንዴ? የስራ ቋንቋችን አማርኛ አይደለም እንዴ? ባልሳሳት ከ80 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ አማርኛን ይናገራል:: ስለዚህ ሆን ተብሎ አንዱን አሳንሶ፣ ሌላውን የማግዘፍ ሁኔታ የሚስተዋልበት ሞጁል ነው፡፡ ይሄ አሃዛዊ መረጃ ከየት እንደተገኘ፣ እንዴት እንደተገኘ እንኳ በቂ ማስረጃ አልቀረበበትም፡፡
.
አምስተኛው፡- የተሳሳቱና ወቅታዊነት የሌላቸው የታሪክ ሁነቶች የማስቀመጥ ጉዳይ ነው፡፡ ማስረጃ የሌላቸው ታሪኮች ቁጥር ስፍር የላቸውም፡፡ የተሳሳቱም እንደዚያው፡፡ ስዕሎችና ካርታዎች እንኳ ከየት እንደተወሰዱ ምንጭ አያስቀምጥም፡፡ ታሪክ እንግዲህ ማስረጃን ተመስርቶ የሚፃፍ ነው፡፡ በዚህ ሞጁል ላይ ለተሳሳቱ መረጃዎች ምሣሌ ከሚሆኑት አንዱ፡- የዛጉዌ ስርወ መንግስት ጉዳይ ነው፡፡ እኔ “በስፋት ጥናቴን በዚህ ስርወ መንግስት ላይ እንደማድረጌ፣ በዋናነት የነበሩበት ዘመን መሠረታዊ ስህተት ያለበት ነው፡፡ የዛጉዌ ስርወ መንግስት ከ1150 እስከ 1270 ነው ብሎ ያስቀምጣል፡፡ የሚገርመው የላሊበላ ዘመነ መንግስት ደግሞ ከ1160 እስከ 1211 ተብሎ ነው የተቀመጠው::
.
ሲጀመር እንደዚህ እርግጠኛ ሆኖ ቀኑን ማስቀመጥ አይቻልም፡፡ ግምት ነው ማስቀመጥ የሚቻለው፡፡ ይሄ ምን ያህል አሳሳች ሊሆን እንደሚችል ማንም የሚረዳው ነው፡፡ ሲቀጥል ደግሞ የዛጉዌ ስርወ መንግስት የሚጀምረው በ1150 ነው ብሎ፣ ላሊበላ 1160 ነው የጀመረው ይላል፡፡ ይሄ  ከላሊበላ በፊት የነገሱት ነገስታት እንዴት ነው በ10 አመት ውስጥ ብቻ ተራርቀው የነገሱት? የሚል ጥያቄን ያስነሳል:: በመሠረቱ የዛጉዌ ስርወ መንግስት ወደ 930 ዓ.ም ወደ ኋላ የሚጐትት፣ እስከ 13ኛው መቶ ክ/ዘመን የቆየ፣ ከ300 አመታት ያላነሱ ታሪክ ያለው ነው እንጂ ሞጁሉ ባስቀመጠው ዘመን ውስጥ የሚገለጽ አይደለም፡፡ በዛጉዌ ስርወ መንግስት ላይ በርካታ የተሳሳቱ መረጃዎችን የያዘ ሰነድ ነው:: ስለ አብያተ ክርስቲያናቱ የሚያስቀምጠው ትንተናም በሃሰተኛ መረጃዎች የተሞላ ነው:: ስለ አብያተ ክርስቲያናቱ የተሰጠው ገለፃ እውቀት ላይ ያልተመሰረተ ነው:: የላሊላ አብያተ ክርስቲያናት ዝርዝር በስህተት የተሞላ ነው:: መረጃዎቹ በጣም የተዛቡ ናቸው፡፡ እኔ ጥያቄ የሆነብኝ በቂ ማስረጃ ያለውን ነገር፣ ለምን በዚህ መልኩ ማስቀመጥ እንደተፈለገ ነው፡፡
.
የማስረጃ ፋይዳ – ለታሪክ ትምህርት 
.
ይህ ሰነድ እንግዲህ ለታሪክ ተማሪዎች የተዘጋጀ ነው፡፡ ያዘጋጁት ደግሞ ታሪክ የተማሩ ምሁራን መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ግን ለምንድን ነው እነዚህ ሰዎች በዚህ መልኩ ሊያዘጋጁት የፈለጉት? ሌላው  ጥያቄ ደግሞ ይሄ ሰነድ በዚህ መልኩ ከተዘጋጀ በኋላ እንዴት የሚገመግመው አካል የለም? ትውልድን ወደ ስህተት የሚያመራና ለግጭት የሚጋብዝ ሰነድ ሲዘጋጅ በምን መልኩ ነው ሂደቱን ያለፈው? የሚለው ጥርጣሬ የሚፈጥር ነው፡፡ ያለ ማስረጃ የተፃፈ ሞጁል እንዴት ነው ማስተማሪያ ሊሆን የሚችለው? በአጠቃላይ ነገሩን ሳየው፣ ታሪክን የራስን ስሜት መጫኛና የፖለቲካ ፍላጐትን ማስፈፀሚያ አድርጐ ማቅረቡ አሳዛኝ ነው፡፡
.
በዛሬ መነጽር የትናንትን ታሪክ ማየት ነውር ነው፡፡ ስህተትም ነው፡፡ ፀሐፊዎችም ይሄን በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ያለ ማስረጃ የሚፃፍ ታሪክ ደግሞ ህይወት የለውም፤ ሙት ነው፡፡ አንዱ የሞጁሉ ክፍተት ይሄ ነው፡፡ ሌላው የታሪክ ትምህርትን ጠቀሜታ ያለመገንዘብ ጉዳይ ነው:: ታሪክን ለቀውስ፣ ለግጭትና ለትርምስ በር ከፋች አድርጐ የማስቀመጥ አላማውም ምን እንደሆነ አልገባኝም፡፡
.
በአብዛኛው ያለ ምንም አስረጅ (ሪፈረንስ) ነው የተፃፈው፡፡ የተሳሳቱ ትርክቶች ጭምር የተካተቱት በዚህ መንገድ ነው፡፡ ማስረጃ ያላቸውን ወደ ጐን ትቶ፣ ማስረጃ የሌላቸውን ትኩረት መስጠቱ አስገራሚ ነው፡፡ ታሪክ ስርአት ባለውና ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ተቀናብሮ የሚፃፍ ነው፡፡ ስላለፈው ማህበረሰብ ሃይማኖት፣ ማህበራዊ መስተጋብር፣ ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚተነትን ሳይንስ ነው ታሪክ፡፡
.
የታሪክ አፃፃፍ ሂደቶችስ? 
.
የታሪክ ጽሑፍ በብዙ ሂደት ውስጥ የሚያልፍ ነው፡፡ መጀመሪያ መረጃ ይሰበሰባል፣ በየፈርጅ ይለያል፣ ከዚያ ይደራጃል፣ ቀጥሎ ይቀናበራል፤ ይተነተናል፡፡ መጨረሻ ላይ ህይወትና ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ይሄ ሞጁል ግን ይሄን ሂደት ያለፈ አይደለም፡፡ ስለዚህ ተረት ተረት ነው:: በመሠረቱ አሁን እየተጣላን ያለነው በታሪክ ነው፡፡ ታሪካችንን በቅንነት የትብብራችን፣ የአንድነታችን የእድገት መሠረታችን አድርገን ማስቀመጥ እንችላለን፡፡ ይሄን ለማድረግ የሚያስችል የታሪክ ሃብት ባለቤት ነን፡፡ ነገር ግን እንደዚህ በትክክለኛ ማስረጃ ያልተፃፈ ታሪክ፣ ዞሮ ዞሮ የግጭታችን መንስኤ መሆኑ አይቀርም:: ታሪክ ትናንትን ዛሬንና ነገን የሚያስተሳስር መግባቢያ ቋንቋችን መሆን ይገባው ነበር፡፡ ታሪክ ይሄን የመግባቢያ ቋንቋነት ሚናውን ስቶ ነው አሁን እየተባላን ያለነው፡፡ ይሄን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ወደ ኋላ ሄደን ወደፊት ተራምደን ለመሄድ የሚረዳን ነው፡፡
.
ታሪክን ታሪክ የሚያደርገው ማስረጃ ነው:: የታሪክ ሕያውነት ማረጋገጫው ማስረጃ ነው ታሪክ ያለ ማስረጃ የሞተ ነው፡፡ ታሪክ ያለ ማስረጃ ማለት፣ ነፍስ የተሰዋችው ስጋ ማለት ነው፡፡
.
ነፍስ የተለየችው ስጋ ሽታው መጥፎ ነው፤ ሽታው በሽታ ያመጣል። አሁን የተጻፈው ታሪክም ያለ ማስረጃ ከታሪክ በፊት ይኖራል፤ ታሪክ ግን ከማስረጃ በፊት አይኖርም፡፡ ታሪክ ፈጥሮ ማስረጃ ፍለጋ አይሆንም፤ ትክክለኛ አካሄድ አይደለም፡፡ የኛ ችግር ይሄ ነው፤ ያለ ማስረጃ የሚጻፍ ታሪክ ተረት ተረት ነው፡፡ አፈ ታሪክና ልቦለድ ነው የሚሆነው፡፡
Filed in: Amharic