>
11:42 pm - Wednesday November 30, 2022

የደጃዝማች በላይ ዘለቀ ሰማዕትነት (ስቅላት) 75ኛ ዓመት መታሰቢያ!!!  (አምደጽዮን ሰርጸድንግል)

የደጃዝማች በላይ ዘለቀ ሰማዕትነት (ስቅላት) 75ኛ ዓመት መታሰቢያ!!!

 አምደጽዮን ሰርጸድንግል
ጀግናው አርበኛ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ (አባ ኮስትር) እና ወንድማቸው እጅጉ ዘለቀ የተሰቀሉት (የተገደሉት) ከዛሬ 75 ዓመታት በፊት (ጥር 5 ቀን 1937 ዓ.ም) ነበር፡፡
በላይ ዘለቀ ከአባታቸው ባሻ ዘለቀ ላቀው እና ከእናታቸው ወ/ሮ ጣይቱ አስኔ በ1904 ዓ.ም ተወለዱ። አባታቸው ባሻ ዘለቀ ላቀው የልጅ ኢያሱ ሚካኤል አንጋች (ባለሟል) ነበሩ፡፡ በላይ ገና ልጅ ሳሉ አባታቸው በሰው እጅ በመገደላቸው ምክንያት በእናታቸው እንክብካቤ ያለአባት አደጉ። እድሜያቸው እየጨመረ ሲመጣም የአባታቸው ገዳይ ማን እንደሆነ በማወቅ ለመበቀል ገዳዩን ማፈላለግ ጀመሩ።
ለምጨን ተሻግረው የአባታቸውን ደም ለመበቀል ሲጠባበቁ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ወረረች፡፡ በላይም ሀገርን የወረረውን የኢጣሊያን ጦር ለመውጋት ቆርጠው ተነሱ።  ብዙ ተከታዮችን በማፍራትም ወደ አርበኝነት ገቡ፡፡ ጀግናው አርበኛ ከፋሺሽት ኢጣሊያ ጋር ባደሩጓቸው ተደጋጋሚ ውጊያዎች ታላላቅ ድሎችን አስመዘግበው በርካታ የኢጣሊያና የባንዳ ወታደሮችን በመማረክና በመግደል እንዲሁም የጠላት ጦር ካምፖችን በማቃጠል ታላላቅ ጀብዶችን ፈፀሙ፡፡
የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ጦር በበላይ ዘለቀና በሌሎች ጀግና ኢትዮጵያውያን ታላቅ ተጋድሎ ድል ሆኖ ከምድረ ኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ ንጉሰ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ከእንግሊዝ ወደ ኢትዮጵያ በሱዳን በኩል ሲገቡ በላይ ዘለቀ የጎጃምን ብዙ ጦር አሰልፈው ንጉሡን በታላቅ ድምቀት በመቀበል ታማኝነታቸውን አሳዩ፡፡ ንጉሡ ወደ መናገሻ ከተማቸው አዲስ አበባ ደርሰው ለአርበኞች ስልጣንና ሹመት ሲሰጡ ከበላይ ዘለቀ ያነሰ ድሎችን ያስመዘገቡ ሁሉ ለከፍተኛ ሹመትና ማዕረግ ሲታደሉ በላይ ዘለቀ ግን እጅግ ከሚገባቸው በታች የ‹‹ደጃዝማች››ነት ማዕረግና የብቸና ገዢ ብቻ  እንዲሆኑ ተሾሙ፡፡
ጀግናው አርበኛ ተበሳጩ፡፡ በዚህም ምክንያት ከበላይ አካል (ከአዲስ አበባ) የሚመጣን ትዕዛዝ አልቀበልም በማለታቸው ከማዕከላዊው መንግሥት ባለስልጣናትና ከመንግሥት ታማኞች ጋር በተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ ገቡ፡፡  ወንድማቸው እጅጉ ዘለቀን፣ አያሌዉ መሸሻን እና ሽፈራዉ ገርባዉን አስከትለው ሶማ በረሃ ገቡ፡፡
በዚያም ሳሉ ከጎጃም፣ ከጎንደርና ከወሎ ከተዉጣጣዉ የመንግሥት ጦር ጋር ለሶስት ወራት ያክል ሲዋጉ ቆይተው በሚያዚያ ወር 1936 ዓ.ም እጃቸውን ለመንግሥት ሰጡ፡፡ በላይ እና እጅጉ ዘለቀም አዲስ አበባ ተወስደው ታሰሩ፡፡ አዲስ አበባ ለተወሰኑ ወራት ያህል በእስር ከቆዩ በኋላ ግን በላይና እጅጉ ከእስር ቤት አምልጠዉ ወደ ጎጃም ሲያመሩ በድጋሚ ተያዙ።
በመጨረሻም ወንድማማቾቹ በላይ ዘለቀና እጅጉ ዘለቀ ጉዳያቸው በልዩ ፍርድ ቤት ታይቶ ታህሳስ 23 ቀን 1937 ዓ.ም የሞት ፍርድ ተፈረደባቸዉ፡፡ ጥር 4 ቀን 1937 ዓ.ም በገነተ ልዑል ቤተ መንግስት ዙፋን ችሎት ፊት ቀርበውም የሞት ፍርዱ ፀናባቸው፡፡ በውሳኔው መሰረትም ቅዳሜ ዕለት ጥር 5 ቀን 1937 ዓ.ም ጀግናዉ አርበኛ ደጃዝማች በላይ ዘለቀና ወንድሙ እጅጉ ዘለቀ በአደባባይ ተሰቀሉ፡፡
ደጃዝማች በላይ ዘለቀ የሻሽወርቅ፣ ባሕሩ፣ መላኩ፣ ጎሹ፣ የሺእመቤት እና የሮምነሽ የተባሉ ስድስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡
ደጃዝማች በላይ ዘለቀ የጠላት ጦር በተለይ ጐጃም ውስጥ መቆሚያ እና መቀመጫ እንዳይኖረው በማድረግ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ውለታ ያበረከቱ ጀግና ናቸው። መቼም ኢትዮጵያ ጀግኖቿን የማክበርና የመንከባከብ ነገር ብዙም አይሆንላትም እንጂ ጀግናው በላይ ዘለቀ ይህ ዓይነቱ የሞት ፍርድ የሚገባቸው ሰው አልነበሩም! የኢትዮጵያ ሕዝብ በጀግናው ሰው ስቅላት ምክንያት የደረሰበትን ሐዘንና ቁጭት ለመረዳት በተለያዩ ወቅቶች የተፃፉ መፃሕፍትን መመልከትና የተዘፈኑ ዘፈኖችን ማዳመጥ በቂ ነው፡፡
Filed in: Amharic