>
5:19 am - Friday July 1, 2022

እሪ በይ አገሬ! “ለልጆችሽ ላትሆኝ ነው?” (አምባሳደር ዓለማየሁ አበበ ሸንቁጥ)

እሪ በይ አገሬ! 

ለልጆችሽ ላትሆኝ ነው ?”

 ከአምባሳደር ዓለማየሁ አበበ ሸንቁጥ

 

                  ለሺ ዘመናት በማህፀኑዋ ውስጥ ተሸፍኖ የኖረውን የማያልቅ ሀብት ይዛ፤ የሕዝቡዋም ንቃተ ህሊና ሲጎለብት በእጁዋ መዳፍ ሥር  ያለው ሀብት የሚያዝናና ባይሆምም በማገዶ ምጣድ እንጀራ ጋግራ ያችን ሸጣ የምትዳደረው፤ ጫማ ጠርጎ የእለት ጉርሱን የሚሸፍነው በአጠቃላይ በዝቅተኛ ኑሮ ላይ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ከጉሮሮው ላይ ነጥቆ ወንዛችንን ገድበን ለሥልጣኔ በር ከፋች የሆነውን ሀይል ለማምረትና ለመጠቀም    ለመላ ህዝባችን ቀን ይወጣለታል ብሎ የተማመነበትን ለሺ ዓመታት በዘለቀው ታሪካችንም ሆነ ዛሬ ደህንነታችንን የማይመኙ የቅርብ ጎረቤቶቻችን ህልማችንን አውን ልናደርግ ስንሮዋሩዋጥ እንቅፋት ዘርግተውብን መውጫ መግቢያ እንድናጣ እየተንቀሳቀሱ ይገኘሉ፡፡

       ይህን ታላቅና የኢትዮጵያን አጣ ፈንታ ቀያሽ የሆነው ፕሮጄክት ህዝብ ያዋጣውን ገንዘብ የእናት ጡት ነካሽ በሆኑ ልክስክሶች ተመዝብሮ ሥራውን ቢያዘገየውም ህዝቡ አሁንም ግድቡን ለማስጨረስ ካለው ጉጉት ማዋጣቱን ቀጥሎዋል፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለህዝብ ያልተመቹ ቆራጭ ፈላጭ መሆናቸው ለአገር ተቆርቁዋሪውን ሁሉ ያጨስ ቢሆንም በአባይን ግድብ ግንባታ ጉዳይ ሊፈጠሩ የሚችሉትን እንቅፋቶች ሁሉ ንቀው በኢትዮጵያዊያን ላይ ተስፋቸው ጥለውና ደፍረው  ሥራውን ማስጀመራቸው ከብዙ አውዳሚ ሥራቸው ውስጥ አፈትልኮ የተገኘ በጎ ጎን መሆኑ አይካድም፡፡

          በእንቅልፍ ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ  ሌት ተቀኝ የማይተኙልን የቅርብ ጎረቤቶቶቻችን፤ አፍሪካ በአውሮፓውያን ቅኝ ሥር እንድተማቅቅና እንድትዘረፍ የበርሊኑ ስብሰባ ከወሰነ በሁዋላ በጎረቤት አፍሪካውያን መካከል የደህንነትና የጥቅም ጉዳይን ለማስፈጸም ያደረጋቸው ስምምነቶችና ውሎች በአገሬው ልጆች ሳይሆን በቅኝ ገዢዎች ለቅኝ ገዢዎች ጥቅም እንዲያገለግሉ እንጂ የሌላውን ህዝብ ጥቅም ያላገናዘበ ነበር፡፡

          የወንዞች ሁሉ ንጉሥ የሆነው አባይ ፤ የአባይ ጅረት ከሌሎቹ ሰባቱ ተፋሰስ አገሮች የሚደጎመው 20% ሲሆን ከኢትዮጵያ እየተንደረደረ  ውሀውንና ለእርሻ እንደማደበሪያ የሚያገለግው ወርቃማ የኢትዮጵያ አፈር መጠኑ 80% የሆነውን ለዘመናት ያለአንዳች እንከን ሲያቀርብላቸው ኑሮዋል፡፡ ይህም የአደባበይ ምሥጢር በጥናት የተረጋገጠ ነው፡፡

         የውሃው ሰማኒያ በመቶ ባለቤት የበይ ተመልካች አድርጎ ፍትሃዊነትን ባላገናዘበ እኔ ብቻ ተጠቃሚ ልሁን የምትለዋ  ከዘመናት በፊት ጦር የመዘዘችብንና ተዋርዳ የወጣች አገር እነሆ ዛሬ ደግሞ በእጅ አዙር ገባር ልታደርገን ተነሳስታለች፡፡ በዘመነ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አባይን በመገንባት ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ሥልጣኔ ያሸጋግራታል ተብሎ በመታሰቡ እቅድ ወጥቶ ይህን ተግባር ለማስፈጸም በዓለም የብድር ተቁዋማት ቢጠየቅም በጠላትነት ሽንጡዋን ገትራ የቆመቸው ግብፅ በነበራት ተሰሚነት ልታስከለክለን ችላለች፡፡ ይሕ የቅርብ ትዝታችን ነው፡፡

        ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሕዳሴውን ግድብ ግንባታ እውን ለማድረግ በወሰዱት ቆራጥ እርምጃ የማንንም አገር ሆነ የብድር ተቁዋም ደጅ ሳንጠና እኛው እራሳችን እንገነበዋለን ብለው ያስጀመሩት እነሆ በአሁኑ ወቅት ብዙ መሰናክሎችን አልፎ ሊጨረስ አፋፍ ላይ መድረሱ ይታወቃል፡፡

         የግንባታው መገባደጃ ወቅት እየተዳረሰ ሲሄድ የአባይን መገደብ ተቅበዝብዘው ለማምከን በተለመደው አካሄዳቸው ተነሳስተው በቅኝ ገዥዎች ዘመን የነበረው ውል ዛሬም ተግባራዊ ይሁን በማለት ውሉ መቀመቅ የወረደውን ነፍስ ሊዘሩበት ይመኛሉ፡ ፡የህልም እዣት የላሉ ይህ ነው፡፡ እነዚያ የቆረፈዱ ውሎች ኢትዮጵያና ሌሎቹ ሰባት የተፋሰስ አገሮችን አግልሎ ግብጽና ሱዳን ሙሉ የበላይነት መብት የሚያጎናጸፍ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያና ሌሎች የተፋሰስ አገሮች ግን በውሀ ጥም ፍግም ቢሎ ጉዳያቸው አይደለም፡፡

         የግድቡ ግንባታ እየተፋጠነና የውሀ ሙሌት ጊዜ በመቃረቡ የሙሊቱን ዘመን በሦስትዮሽ ውይይት በተከታታይ በግብጽ በሱዳንና በኢትዮጵያ ለአራት ጊዜ ስብሰባ አካሂደው በግብጽ አደናቃፊነት ሳይቁዋጭ ከመቅረቱም በላይ በመጨረሻው አዲስ አበባ ውስጥ በታህሣሥ  2012 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ ሃላፊነት በጎደለው መልኩ ኢትዮጵያ ሙሊቱን በ21 ዓመት ሞልታ እንድታጠናቅቅ ሃሳብ በማቅረቡዋ ምን ያህል በንቀት የተወጠር መንግሥት መሆኑን አሳይቱዋል፡፡ ይህም የመጨረሻው የሚኒስትሮች ስብሰባ ያለስምምነት አክትሞ ለቀጣይ ስብሰባ ወደ አሜሪካ ጉዞ ተደርጎ የዚያ ስብሰባ ውጤት በጉጉት እየተጠበቀ ነው፡፡

         በአባይ ከግብጽና ከሱዳን በስተቀር ሌላ አገር ከውሃው ጠብታ እንኩዋን ቢያስቀር እ.አ.አ. በ1979 ዓ.ም. የወቅቱ የግብጽ ፕሬዚዴንት አንዋር ሳዳት የአባይ ብቸኛ ባለቤቱዋ ግብጽ ስለሆነች ባለቤትንቱዋን ለማረጋገጥ ወደ ጦርነት እንሄዳለን ሲሉ የደነፉት የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ሙርሲ የተባለውም የእስላሞች አክራሪ ቡድን መሪ የግብጽ ፕሬዚዴንት በነበረበት ወቅት ሀይል ተጠቅመን በአባይ ላይ የባለቤትነት መብታችንን እናስረክባለን ብሎ እንደፎከር ዕናውቃለን፡፡ ይህ ማለት ግብጽ በዚህ ድርድር የምታሳየው አሉታዊ አሳቦች ሁሉ ዞሮ ዞሮ አባይን ጠቅልላ ለማያዝ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

          ያለኛ ተሳትፎና ጋባዥነት በግብጽ ተማጽኖ አሜሪካና የአለም ባንክ በስብሰባው ላይ በተመልካችነት እየተሳተፉ ባሉበት ሂደቱ እልባቱ ለኢትዮጵያ አስደሳች ይሆናል ብሎ መገመት ያስቸግራል፡፡ ለኢትዮጵያዊያን የአባይ ጉዳይ የህልውና የልዑላዊነት ጉዳይ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይም ሆኑ መንግሥታቸው ያለሕዝብ ውሳኔ እጣ ፋንታችን ላይ ሊወስኑ ሥልጣኑም መብቱም የላቸውም፡፡

          የአባይን ግድብ ጉዳይ መንግሥት እየያዘ የሚመራው አካሄድ ግልጽነት በጎደለው መልኩ ስለሆን በኢትዮጵያና በውጭ ካሉ ሊቆቹዋ እንዳትጠቀም አድረጉዋታል፡፡ ሌላው ቀርቶ እዚሁ ከጎናቸው ካሉ የአባይን ጉዳይ ጊዜ ወስደው ጥናት አካሂደው መጻህፍት የጻፉትን እነኩዋን በአግባቡ ለማሳተፍ አልተጣረም፡፡ 

           በዲፕሎማሲውም ዘርፍ የጉዳዩን ካባድነት በመገንዘብ ሰባቱን የተፋሰሰ አገሮች ለማሳተፍ አለሞመከራችን አጋርና ደጋፊዎች የሚሆኑትን አግለላናቸዋል፡፡ ከዚህም አልፈን ወንድሞቻችን አፍረካዊያን ከጎናችን እንዲሰለፍ አለመጣሩ ተዘንግቶ ነው ብሎ ማሰብ አያስደፍርም፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ ግብጽ ተጽኖዋን በኢትዮጵያ ላይ ለመጫን በዓለም ዙሪያ ስትሮዋሩዋጥ እናያለን፡፡ የፍትሃዊ ሥርዓት ትርጉም የማይገባቸው የአረብ መንግሥታት ዘር ከልጉዋም ይስባል እነዲሉ ዓይናቸውን በጨው አጥበው በጭፍን የግብጽን አቁዋም ያለአንዳች ቅሬታ ደግፈዋል፡፡ የቅርብ ጎረቤት የሆኑት ሳየቀሩ ያለአንዳች ማቅማማት ሽንጣቸውን ገትረው እየተከራከሩላት ነው፡፡ እነዚህ የዘመኑን የመንግሥት ባህርያት ያልተላበሱ አስተሳሰባቸው አንደ አያቶቻቸውና ቅድመ አያቶቻቸው የግመል ጭራ በመከተል ይኖሩ የነበረ ዘላኖች አስተሳሰብ ለሌላው የሰው ልጅ ህልውና መብት ደንታ የማይሰጣቸው ፤በአጋጣሚ ተፈጥሮ በለገሰቻቸው ሀብት እየተጠቀሙ ዙሪያቸውን ማመስ የተያያዙ ናቸው፡፡

        ስለሆነም ኢትዮጵያ የአባይ ባለቤት መሆኑዋን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ ይህ ማለት ሌሎች ተጠቃሚ የሆኑና የህልወናቸው ማረጋገጫ የሆነውን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡

         መንግሠት ለሚሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ባለቤቱ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲወስንበት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

          ከዚህ ውጭ የሚደረግ ውሳኔ ጊዜውን ጠብቆ ያስጠይቃል፡፡

                           ኢትዮጵያ ህልውና ተጠብቆ ለዘላለም ትኑር 

       

Filed in: Amharic