>
4:26 am - Friday July 1, 2022

ለምን ተጨካከንን? ሰው የሆንን ዕለት ...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ለምን ተጨካከንን? ሰው የሆንን ዕለት …!!!

ያሬድ ሀይለማርያም
 

* አፋኝም፤ ታፋኝም እኛው ሆነናል። የትላንት አፋኞቻችን ደግሞ ከዳር ቁጭ በልው ድራማውን እየተከታተሉ ይመስላል!

አፋኝ የነበረው ሥርዓት ሰው ሲገድል፣ ሲያስር፣ ሲደበድብ፣ ሲያፈናቅል፣ ሲያሰድድ እና አፍኖ ሲሰውር ሳይ ይሰማኝ የነበረው ስሜት ድርጊቱ የአንባገነን ሥርዓት መገለጫ ባህሪ ስለሆነ ይህን የመብት ጥሰት ለማስቆም ሥርዓቱን መታገልንና ማስወገድ ነበር። ዛሬ ደብዳቢውም፣ አፋኙም፣ ገዳዩም፣ አፈናቃዩም፣ አሳዳጁም ከማህበረሰቡ ጉያ የወጡ መንግስታዊ ሥልጣን የሌላቸው ጉልበተኞች ሲሆኑ ግን የተሰማኝ ስሜል ሌላ ነው። ገዳይም እኛው፤ ሟችም እኛው ሆነናል። አፋኝም፤ ታፋኝም እኛው ሆነናል። የትላንት አፋኞቻችን ደግሞ ከዳር ቁጭ በልው ድራማውን እየተከታተሉ ይመስላል። 
 
ግን ለምን ተጨካከንን? ምንስ ልናተርፍ? ማንስ ከእንዲህ ያለው ማህበረሰባዊ ተቃርኖ እና ጥቃት ተኮር ግጭት ሊተርፍ? ማን በሰላም ሊያድር? 
 
በቅርቡ የግጭት አረዳዳችን በሚል ጠቆም አድርጌ ባለፍኩት አጭር ጽሁፍ ማህበረሰባችን የተሰነቀረበትን ቅርቃር ለማሳየት ሞክሬ ነበር። አዎ እንደ አገር እና እንደ አንድ ማህበረሰብ ካሰብን ትልቅ ችግር ውስጥ ነን። ይህን እላያችን ላይ የተቆለለውን እና እሳት ላይ የጣደንን አደጋ በጥንቃቄ ካላየነው እና እንደ አገር ችግር ቆጥረን የጋራ መፍትሔ ከወዲሁ ካልፈለግንለት እንዳይሆን እንዳይሆን አድርጎ የአለም መሳለቂያ ያደርገናል። ለዛሬው ለምን ተጨካከንን? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ በዳይ እና ተበዳይ፣ ገዳይ እና ሟችን፣ አፋኝ እና ታፋኝን እያሰብኩ ችግሩን እኔ የተረዳሁበትን መንገድ ለውይይት ይረዳ ዘንድ ላካፍላችው።
 
ከዚህ በፊት በሌላ ጽሁፌ እንደገለጽኩት ማህበረሰባችን በሦስት ነገሮች ክፉኛ ተጠቅቷል። አንደኛው ስር የሰደደ ፍርሃት ነው። በዚህ ዙሪያ ብዙ ጽፌበታለሁ። ከስድስት ወር በፊትም ይመስለኛል “ፍርሃትን አታንግሱት!” በሚል አጭር ዳሰሳም ጽፌ ነበር። ሌላው ጨለምተኝነት ነው። በማህበረሰባችን ውስጥ ጨለምተኝነት በሰፊው እንዲነግስ ተደርጎ ሕዝቡ በአገሩ እና በመንግስት ላይ ተስፋ እንዲቆርጥ ተደርጓል። ዛሬ ማተኮር የምፈልገው እና የዚህ ጽሁፌ ዋና ትኩረት ግን ሰዎችን እርህራሄ አልባ ወይም ከሰውነት ስሜት ማራቅ ወይም እንደ ሰው ብቻቸውን ቆመው እንዳያስቡ ማድረግ፤ በእንግሊዘኛው dehumanization ላይ ነው ማተኮር የምፈልገው። የእዚህ ቃል እንግሊዘኛ ትርጉሙ በጣም ግልጽ ነው። Dehumanization ማለት the process of depriving a person or group of positive human qualities ይላል። አንድን ሰው ወይም አንድን የሰዎች ስብስብ የሰው ልጅ መገለጫ ከሆኑ መልካም ባህሪያት ማራቅ እና ሌላ ደባል ባህሪ እንዲላበስ ማድረግ ነው።
 
በእኔ ግምገማ ማህበረሰባችን እረዘም ላለ ጊዜ በአፈና ውስጥ በመቆየቱ፣ ጥልቅ የሆነ ድህነት ተጠቂ በመሆኑ እና ሆን ተብሎ ትውልዱ እራሱን እንደ ሰው እንዳይቆጥር እና መልካም የሆኑ የሰውነት ባህሪያትን እንዲያጣ በተለይም ለሃያ ሰባት አመት በወያኔ እና አጋሮቹ የተተገበርው የጎሳ ፖለቲካ ትልቁን ሚና ተጫውተዋል። ሰዎች እራሳቸውን ከሰው ተራ አውጥተው ሊጨበጡና ሊዳሰሱ በማይችሉ የማንነት መገለጫዎች፤ ጎሳ፣ ብሄር፣ ኃይማኖት፣ ዘር፣ ቋንቋ፣ አካባቢ ውስጥ እራሳቸውን እንዲከቱ በጀት ተመድቦ፣ ሕገ መንግስት ተቀርጾ፣ ፖሊሲ ተነድፎ ትልቅ ስራ ተሰርቶበታል። ትውልድን የማምከኑ ፕሮጀክት በደንብ ስለተተገበረም ዛሬ ፍሬውን እያፈስን ነው። ሰዎች ከሰውነታቸው በፊት ብሔረሰብ ሆነዋል። ሰዎች ከሰውነታቸው በፊት ኃይማኖት ሆነዋል። 
 
የዚህ አይነት ትውልድ መፈጠር ትልቁ አደጋ ራስን ከሰውነት ተራ ማውጣቱ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሰዎችንም እንደ ሰው እንዳንቆጥር አድርጎታል። እኔ ሰው ነኝ ስል እሱ ብሔሬ ወይም ኃይማኖቴ ነው በሰ አምሳል ተቀርጾ የሚታየው። ብሄረተኛ ሆነን ሌሎች ሰዎችን ስናይ መጀመሪያ ወደ አይምሯችን ውስጥ የሚመጣው የሰውየው ዘር፣ ቀለም፣ ጎሳ፣ ብሔር ወይም ኃይማኖት ወይም ሌላ የወል መገለጫ ነው። ሁለት ሆነን ቆመን ስናወራም፣ ስንነታረክም፣ ስንጋጭም፣ ስንቧቀስም፣ ስንፋቀርም፣ ስንዋዋልም፣ ስንደራደርም በመሃላቸን ያለው መስተጋብር የሁለት ግለሰቦች ሳይሆን የብሕሄሮች መንፈስ ይሆናል። የሁለት ጎሳዎች ወይም የሁለት ኃይማኖቶች ፍቅር፣ ጸብ፣ ስምምነት ወይም ንትርክ አድርገን እንቆጥረዋለን። የገብረማርያም እና የሙሃመድ፣ የቶሎሳ እና የአየለ፣ የተክላይ እና የጎንጤ፣ የደብርቱ እና የጫልቱ፣ የያሬድ እና የሸምሱ ጸብም ሆነ ፍቅር የሁለት ብሔሮች ወይም የሁለት ኃይማኖቶች ግንኙነት ተደርጎ ይቆጠራል። ምክንያቱም እራሳችንን ከሰውነት ተራ አርቀን በብሔር ወይም በኃይማኖት ካባ ተከሽነን በውል ማንነት ተውጠናል።
 
እንዲህ መሆኑ ላይከፋ ይችላል አደገኛ የሚሆነው ሰውነታችንን አስጥሎ ብሄር ወይም ኃይማኖት እሚባል ውል አልባ ማንነት ያለበሰን ታሪካዊ፣ ማህበረሰባዊና ፖለቲካዊ  መሰረታችን የተቀመረው በጥላቻ፣ በሃሰት የታሪክ እና የልዩነት ትርክት፣ በፉክክር፣ በተበዳይነት እና በተቃርኖ ላይ ብቻ ያተኮ መሆኑ ነው። ላለፉት አሥርት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ይተዘራው ዘር ተኮል ጥላቻ እና ክቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እየጎላ የመጣው የኃይማኖት ተኮር ቅራኔዎች በቤንዚል ላይ እሳት እንደመለኮስ ያህል በዘር ላይ የተገነባው ማንነት ወደ አካላዊ ቅራኔ እንዲያመራ አድርጎታል።
 
እያንዳንዱን ሰው ዋሻ ያደረጉት የብሔር ማንነቶችና አመለካከቶች ቅራኔያቸውንም በዚሁ ዋሻ ውስጥ ነው የሚቀብሩት። በየሰዉ ውስጥ ጥላቻውንም፣ የሃሰት ትርክቱንም ሆነ የቅዠት ምኞታቸውን ስላሰረጹ የቶሎሳ እና የተምትሜ ጸብ የአማራ እና የኦሮሞ፣ የተክላይ እና ኡጁሉ ጸብ የትግሬና የአኝዋክ ተደርጎ እንዲቆጠር አድርጓል። ተጣዩዎቹም እንደ ግለሰብ ሳይሆን የሚጣሉት እነድ ብሔር ነው።
 
በአሁኗ ኢትዮጵያ አንድ ሰው በጥቃት ሳቢያ ሲሞት መጀመሪያ ስሙ አይደለም የሚገለጸውም፤ የሚጠየቀውም። መጀመሪያ የሚጠየቀው ብሔሩ ወይም ኃይማኖቱ ነው። ቀጥሎ የሚጠየቀው የገዳዩ ሰው ስም ሳይሆን የሱ ብሔር ወይም ኃይማኖት ነው። ከዛ እገሌ ብሔር የእገሌን ቤር አጠቃ የሚል ሰብር ዜና ትሰማለህ። በዚህ ልክፍት ከተጠቁት ሰዎች መካከል ዶ/ር አብይም አንዱ ናቸው። በቅርቡ 86 ሰዎች የተገደሉበትን ክስተት ከራርመው መጥተው እርማቸውን መገልጫ ቢሰጡ የሟቾቹን ስም ሳይሆን ብሄራቸውን ነው ከፋፍለው የገለጹት። ለሳቸው በሳ ክስተት የተጠቁት ሰዎች ሳይሆኑ ብሄሮች ናቸው። ሊያሳዩም የተፍጨረጨሩት ይሄንኑ ነው። እሳቸውም እራሳቸውን እንደ አንድ ሰው ወይስ እንደ ብሄር የሚቆጥሩት? ለዚህ ንግግራቸውን ማድመጥ በቂ ነው። 
 

ስለዚህ፤

+ በየዩንቨርሲቲው የሚገዳደሉት ተማሪዎች ሰዎች ሳይሆኑ ብሔሮች ናቸው፤
+ በየዩንቨርሲቲው የሚታፈኑት እና የሚያፍኑት ሰዎች ሳይሆኑ ብሄሮች ናቸው፤
+ መስጊድ እና ቤተክርስቲያን የሚያቃጥሉት ሰዎች ሳይሆኖ ኃይማኖቶች ወይም ብሄሮች ናቸው፤
+ በያደባባዩ ዱላ የሚማዘዙት፣ ባህር ዳር ላይ ጠመንጃ ይዘው ና ሞክረኝ እያሉ የሚፎክሩት፣ ድሬዳዋ እና ሐረር ላይ ሜንጫ እና መጥረቢያ ይዘው ይዋጣልን የሚሉት ሰዎች ሳይሆኑ ብሔሮች ናቸው፤
+ ሻሸመኔ ሰው ዘቅዝቀው የሰቀሉት፣ ቡራዩ ሕዝብ የጨፈጨፉት፣ የቅማንት ተወላጆች ላይ ጥቃት ያደረሱት፣ ሲዳማ ላይ ሰዎች የገደሉት፣ ጅጅጋ ላይ ሕዝብ የጨረሱት፣ ጎንደር ላይ ሕጻናት አፍነው ወስደው የረሸኑት፣ መተማ ላይ የጉምስ ተወላጆችን በጅምላ የረሸኑት፣ በየቦታው ሕዝብ ያፈናቀሉት ሰዎች ሳይሆኑ ብሔሮች ወይም ኃይማኖቶች ናቸው፤
 
እንግዲህ አጥቂዎቹም እራሳቸውን እንደ ብሔር ወይም ኃይማኖት እያሰቡ ጥቃት በሚጸጽሙበት፤ ተጠቂዎችም ጥቃቱ የተፈጸመብኝ በብሄሬ ወይም በኃይማኖቴ ምክንያት ነው ብለው በሚያስቡበት፤ መንግስት እራሱን በብሔር አዋቅሮ እኛንም እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ብሄር ቢሚሰፍርበት አገር፤ ተቃዋሚዎች በብሄር ተደራጅተው በብሔሪኛ እያሰቡ፣ የብሔር ተቆርቋሪ ሆነው ልዩነትን በሚቦተልኩበት ማህበረሰብ፣ ለማህበረሰ መብት ተሟጋች የሆኑ ሰዎች የጎሳ ወይም የኃይማኖት ተሟጋች በሆኑበት አገር ስንሞትም፣ ስንኖርም ብሄር ወይም ኃይማኖት እንጂ ሰው ሆነን አይደለም።
 
ከሰውነት ተራ እራሱን ያወጣ ወይም በሁኔታዎች ተገፎትም ቢሆን ሰውነት የራቀው ግለሰብ እሲ ሲሞት ብሄር አብሮ የሚሞት፣ እሱ ሲገድል ብሔር አብሮ ገዳይ የሆነ ይመስለዋል። ሲገድልም ሟቹን በሰውነት ማንነቱ እያሰብው አይደለም የሚገድለው። ሰው እየገደለ እሱ የሚያስበው አዕምሮው ውስጥ እንደ አውሬ ወይም ጠላት አድርጎ የሳለው ብሔርን ወይም ኃይማኖትን ነው የሚገድለው። እኛም እገሌ የሚላብል ሰው እገሌን ገደለ ብለው ነገሩን በሰውኛ ልክ አናየውም። የእገሌ ብሔር እገሌን አጠቃ ነው የምንለው። የግጭት ብቻ ሳይሆን ስለራሳችንም ማንነት ያለን አረዳት ውልግድግዱ የወጣ ይመስላል። 
 
ከዚህ ለመውጣት እና ቅድሚያ ሰው ሆኖ ለመቆም፣ ሰው ሆኖ ለመኖር፣ እንደ ሰው እራሳችንን ችለን ቆመን ለማሰብ ማህበራዊ የስነ ልቦና ህክምና ሳያስፈልቀን ይቀራል?
 
ሰው ሆነን መቆም የቻልን ዕለት ዛሬ የገባንበት ቅርቃር ምን ያህል አስፈሪ እንደሆነ ይገለጥልናል። ሰው ሆነን ማሰብ የጀመርን ለት በሌላው ሰው ላይ በፈጸምናቸው አስነዋሪ ነገሮች ሁሉ አንገታችንን እንደፋለን። ሰዎችን እንደ ሰው ማየት የጀመርን ለት መገዳደል እናቆማለን። ለሰዎች ክብር እና መብት መቆርቆር የጀመርን ለት የበለጸገች አገር መገንባት እንችላለን። መጀመሪያ ግን ሰው እንሁን!!!!
 
ቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic