>
11:25 pm - Sunday May 22, 2022

ከተማ ይፍሩ – የተዘነጋው ታላቁ የአፍሪካ  ኅብረት ኩራትና ባለውለታ!!! (አዲስ ዘመን)

ከተማ ይፍሩ – የተዘነጋው ታላቁ የአፍሪካ  ኅብረት ኩራትና ባለውለታ!!!

አዲስ ዘመን
አንተነህ ቸሬ
ዛሬ «የአፍሪካ ኅብረት» በመባል የሚታወቀው አህጉራዊ ማኅበር «የአፍሪካ አንድነት ድርጅት» በሚል ስያሜ እንዲቋቋም ትልቁን ተግባር ያከናወኑት ከተማ ይፍሩ ደጀን የሚባሉ በዲፕሎማሲ ጥበብ የመጠቁ ፓን አፍሪካኒስት ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያና አፍሪካ ለዚህ ታላቅ ሰው የሰጡት ክብር ታላቁን ሰው «አመድ አፋሽ» ያሰኘ ነው፡፡ የዚህን አርቆ አሳቢ፣ ደፋርና አገር ወዳድ ታሪክና አበርክቶ ዘርዝሮ መጨረስ «ዓባይን በማንኪያ» ቢሆንም ዘመን ተሻጋሪ ሥራቸውን ከብዙ በጥቂቱ እንመልከት፡፡
ከተማ ይፍሩ በ1922 ዓ.ም በቀድሞው ሐረርጌ ክፍለ ሀገር ጋራሙለታ አውራጃ ውስጥ ተወለደ፡፡ አባቱ አቶ ይፍሩ ደጀን እና እናቱ ወይዘሮ ይመኙሻል ጎበና በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ ነበሩ፡፡ በተወለደ በስምንት ዓመቱ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በመውረሯ ምክንያት ከተማና ቤተሰቡ ለስደት መዳረግ ግድ ሆነባቸው፡፡
ቤተሰቡ በስደት ላይ ሳለ ጨርጨር ሲደርሱ ሌሎቹ የቤተሰቡ አባላት እዚያው ቀሩና የአቶ ከተማ አባት ከተማንና የከተማን አጎት (አቶ ተክሉ ደጀንን) ይዘው የስደት ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ ባሌ ደርሰው ጥቂት ከቆዩ በኋላ ወደ ብሪቲሽ ሶማሊላንድ (የአሁኗ ሶማሊላንድ) ሄዱ። የስደት ጉዞው ቀጥሎ ከብሪቲሽ ሶማሊላንድ ወደ ጅቡቲ ከዚያም ወደ ኬንያ ተሰደዱ፡፡ ኬንያ ሳሉ ከተማ ትምህርት ቤት ገባ፡፡ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ እነከተማ ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡
ንጉሰ ነገሥቱ ሐረርን በጎበኙበት ወቅት «ትምህርት የሚያስፈልጋቸው ልጆች አሉ» ሲባል ሰምተው ነበርና ወደ አዲስ አበባ ሄደው መማር እንደሚችሉ ንጉሰ ነገሥቱ በመፍቀዳቸው ታዳጊው ከተማ ከትውልድ ስፍራው ወደ አዲስ አበባ ሄደ፡፡ አዲስ አበባ እንደደረሰ ለመማር ቢያመለክትም «ስምህ የለም» በሚል ምክንያት እንዳይገባ ተከለከለ፡፡ ይሁን እንጂ የወቅቱ የጦር ሠራዊት ኃላፊ የነበሩት ሌተናንት ጀኔራል መርዕድ መንገሻ ስለከተማ ሰምተው ስለነበር በእርሳቸው አማካኝነት ትምህርቱን ጀመረ፡፡ ከተማ በትምህርቱ ጥሩ ውጤት በማስመዝገቡ ከንጉሰ ነገሥቱ ሁለት ጊዜያት ሽልማት ተቀብሏል፡፡
በመቀጠልም ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ወደ ውጭ አገራት ሄደው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ንጉሰ ነገሥቱ በመፍቀዳቸው ከተማ ወደ አሜሪካ በመሄድ በሚቺጋን ሆፕ ኮሌጅ (Hope College) በፖለቲካ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ፡፡ ከዚያም ወደ ቦስተን ዩኒቨርሲቲ በማቅናት ሁለተኛ ዲግሪውን በፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት አጠናቀቀ፡፡ የሁለተኛ ዲግሪውን ሲማር በመጨረሻው ዓመት በኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት መንግሥት ጥያቄ መሠረት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የመስራት ዕድል አገኘ። የዶክትሬት ዲግሪውን እንዲቀጥል ቢጠየቅም «ድሃ አገርና ዘመዶች ስላሉኝ እነርሱን መርዳት አለብኝ» ብሎ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡ አሜሪካ በቆየባቸው ዓመታት በወቅቱ በጥቁሮች ላይ ይደርስ የነበረው የዘር መድሎ/መገለል በእርሱም ላይ ደርሶበታል፡፡ ከተማ ግን ለመሰል ድርጊቶች ብዙም ትኩረት እንዳልሰጣቸውና ከጉዞውም እንዳልገታው ተናግሮ ነበር፡፡
ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰ በ1944 ዓ.ም የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ተቀላቀለ፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ በሚኒስቴሩ የአሜሪካና የእስያ ዳይሬክተር ጀኔራል ሆኖ ተሾመ። ከሦስት ዓመታት በኋላ ደግሞ ረዳት ሚኒስትር ሆኖ መስራት ጀመረ፡፡ በወቅቱ ከተማ ከባላባት ቤተሰብ ባለመገኘቱ ምክንያት አንዳንድ ሹመቶች ያመልጡት እንደነበር ታሪኩ ያስረዳል፡፡ ይህንን ጉዳይ ለንጉሰ ነገሥቱ ጭምር በድፍረት ተናግሮ ነበር፡፡
ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የወጣቱ ከተማ ድፍረት ሳያስገርማቸው ምናልባትም ሳያስደስታቸው አልቀረም፤ምክንያቱም ከዓመት በኋላ ከተማን የግላቸው ልዩ ጸሐፊና ትዕዛዞቻቸው የሚመነጩበትና ከፍተኛ ሥልጣን ያለበት የጽሕፈት ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር አድርገው ሾሙት፡፡ በኋላም የጽሕፈት ሚኒስትር ዴኤታ ሆኖ ተሹሟል፡፡ ከተማ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት መንግሥት አጠቃላይ አሠራርና መዋቅር ምን እንደሚመስል ግልፅና ከቀድሞ መስሪያ ቤቱ (የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር) የተሻለ ግንዛቤ ያገኘው ጽሕፈት ሚኒስቴር ከገባ በኋላ ነው፡፡ የንጉሰ ነገሥቱ ልዩ ጸሐፊና የጽሕፈት ሚኒስትር በመሆኑ ከፍተኛ ሹማምንት ከንጉሰ ነገሥቱ ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት የመታዘብና ወሳኝ የሆኑ ከፍተኛ ስብሰባዎች ላይ የመካፈል ዕድል አገኘ፡፡ ንጉሰ ነገሥቱ ከውጭ መንግሥታት ተወካዮች ጋር በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ እየተገኘ መታዘቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ ላከናወናቸው ተግባራት ጥሩ መሠረት ሆነውታል፡፡
ከተማ ስለኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳዮች የማወቅ ፍላጎቱ ከፍ ያለ ስለነበር የጽሕፈት ሚኒስቴር ለሁለት ተከፍሎ የውጭ ጉዳዮችን የሚመለከተውን ክፍል እርሱ እንዲመራው በመንግሥት መወሰኑን ጸሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሲነግሩት ከተማ ሚኒስቴሩ መከፈል እንደሌለበት፣ እርሱም የውጭ ጉዳዮችን የሚመለከተውን ክፍል የመምራት ፍላጎት እንደሌለውና ስለኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳዮች የበለጠ ማወቅ እንደሚፈልግ ነገራቸው፡፡
ከተማ የጽሕፈት ሚኒስቴር ከተራዘመ ቢሮክራሲያዊ አሠራር ነፃ እንዲሆንና ለተመረጡ እጅግ በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ክፍት መሆኑ ቀርቶ ከሁሉም የመንግሥትና የኅብረተሰቡ የሥራ ዘርፎች ጋር እንዲተሳሰር ከፍተኛ ትግል አድርጓል፡፡ ንጉሰ ነገሥቱ በዚህ የከተማ ሃሳብ በመጀመሪያ ሳይስማሙ ቢቀሩም ከአጭር ጊዜ በኋላ ግን ሃሳቡን ተቀብለዋል፡፡
ከተማ በከፍተኛ አገራዊ ስሜትና ጥበብ ሥራውን እያከናወነ ሳለ በ1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ምክንያት ለእስር ተዳረገ፡፡ ነገር ግን ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ጋር የተገናኘ ጥፋት የለበትም ተብሎ የቅርብ ወዳጁ፣ ምስጢረኛውና መካሪው በነበሩት በመከላከያ ሚኒስትሩ ሌተናንት ጀኔራል መርዕድ መንገሻ እገዛ የንጉሰ ነገሥቱ ልዩ ጸሐፊና የጽሕፈት ሚኒስትር ዴኤታ ሆኖ እንዲቀጥል ተወሰነ፡፡
ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለመሾም ሌተናንት ጀኔራል መርዕድ መንገሻን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ሹማምንትን ሰበሰቡ፡፡ ሹማምንቱም የየራሳቸውን ሰዎች ዕጩ አድርገው አቀረቡ፤ተከራከሩ። ክርክሩን በጥሞና ያዳመጡት ንጉሰ ነገሥቱ፣ እርሳቸው ከተማ ይፍሩን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት እንደመረጡ በመናገር ሹማምንቱን አስገረሙ፤አስደነገጡ፡፡ «የባላባት ዘር ነን» ያሉ ሹማምንት «እንዴት ከድሃ ቤተሰብ የተገኘ ሰው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ ይሾማል?» ብለው ተቃወሙ፡፡ ንጉሰ ነገሥቱ ግን «ውሳኔዬ አይቀየርም» አሉ፡፡
ሹመቱ በአንድ በኩል ከተማ ከታላላቅ ዓለም ፖለቲከኞች ጋር እንዲተዋወቁና አብረው እንዲሰሩ ዕድል የከፈተላቸው ቢሆንም በሌላ በኩል ግን በርካታ «የባላባት ዘር ነን» የሚሉ ሹማምንትና አጋሮቻቸው የከተማ ጠላቶች ሆነው እንዲነሱ በር የከፈተ አጋጣሚም ነበር፡፡ ከተማ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሥራቸውን የጀመሩት ኢትዮጵያ ከአፍሪካውያን ጋር እንድትቀራረብ ለማድረግ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ አምባሳደር ከተማ በአንድ ወቀት ሲናገሩ …
«… እ.አ.አ 1961 ዓ.ም ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንደገባሁ የመጀመሪያ አጀንዳዬ አድርጌ የያዝኩት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ጋር የበለጠ የምትቀራረብበትንና የምትተባበርበትን መንገድ መፈለግ ነበር፡፡ ይህንን ጉዳይ ለጃንሆይ ነገርኳቸው፡፡ ‹ … ፋሺስት ኢጣሊያ በወረረን ጊዜ ወደ ዓለም መንግሥታት ማኅበር ሄደው የጮሁት ብቻዎን ነበር፡፡ ያ ጊዜ መደገም የለበትም፡፡ ከአረቦች ጋር ልንሆን አንችልም፤ከአውሮፓውያንም ጋር መሆን አንችልም፡፡ የእኛ ተፈጥሯዊ ምንጫችን አፍሪካ ስለሆነ ከአፍሪካውያን ጋር ነው መተባበር ያለብን፡፡ በዚህ ጉዳይ መግፋት አለብን። ይህን ጉዳይ ያምኑበታል ወይ?› ብዬ ስጠይቃቸው ‹ዋናው የእኔ ማመን አይደለም፡፡ አንተ ታምንበታለህ?› ሲሉኝ ‹እኔማ አምኜበታለሁ› አልኳቸው። ‹እንግዲያውስ ካመንክበት ቀጥልበት› አሉኝ … » ብለዋል። እንግዲህ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን (የአሁኑን የአፍሪካ ኅብረትን) የመመስረት እንቅስቃሴ የተጀመረው በዚህ ወቅት ነው፡፡
አምባሳደር ከተማ የኢትዮጵያ ዋነኛ ወዳጆች አፍሪካውያን እንደሆኑ ጽኑ እምነት ነበራቸው፡፡ ይህን እምነታቸውን በተግባር ለመተርጎም አፍሪካውያንን በአንድ ጥላ ስር የሚያሰባስብ ኅብረት/ድርጅት ለማቋቋም ደፋ ቀና ማለት ጀመሩ፡፡ በወቅቱ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጡ የአፍሪካ አገራት የካዛብላንካ («የአፍሪካ አገራት በፍጥነት ተዋህደው አፍሪካ አንድ ልትሆን ይገባል») እና የሞኖሮቪያ («አንድ ከመሆን በፊት ሌሎች ትብብሮች ሊቀድሙ ይገባል») በሚባሉ ጎራዎች ተከፋፍለው ነበር። ይህ ክፍፍል የአፍሪካውያንን ኅብረት እንደሚጎዳው የተረዱት አምባሳደር ከተማ ይፍሩ፣ ኢትዮጵያ ሁለቱን ቡድኖች የማስማማትና አፍሪካውያንን በአንድ ኅብረት/ድርጅት ስር የማሰባሰብ ሥራ መስራት እንዳለባት ለንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አጥብቀው ተናገሩ፡፡ ንጉሰ ነገሥቱም በአቶ ከተማ ምክረ ሃሳብ ተስማምተው እንቅስቃሴዎችን ጀመሩ፡፡ አምባሳደር ከተማ ስለዚህ ጉዳይ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር …
«… እኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደነበርኩ በሁለቱም ስብሰባዎች ላይ እንድንካፈል ጥሪ ቀረበልን፡፡ የሞኖሮቪያ ቡድን ጥሪ ቀድሞ ስለደረሰን፣ የሞኖሮቪያ ቡድን አባል የነበሩት አገራት በቁጥር በርከት ያሉና በወቅቱ በአፍሪካ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበራቸው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ስለነበሩ በእርሳቸው ሰብሳቢነት ሁሉም ወገኖች ተሰብስበው ወደ አንድ ሃሳብ እንዲመጡ በማሰብ በሞኖሮቪያ ቡድን ስብሰባ ላይ ተገኘን፡፡ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴም በስብሰባው ላይ ተገኙ፡፡ ቀጣዩ የሞኖሮቪያ ቡድን ስብሰባ አዲስ አበባ ላይ እንዲደረግ ጥያቄ አቅርበን ተቀባይነትን አገኘን፡፡ የካዛብላንካ ቡድን ጥሪ ሲደርሰን ‹በዚህ ዓመት መገኘት አንችልም፤በሚቀጥለው ዓመት ግን እንገኛለን› የሚል ምላሽ ሰጠናቸው፡፡ የካዛብላንካ ቡድን አባላት ደግሞ በዚያው ሰሞን ስብሰባ ነበራቸው፡፡ የወቅቱ የጊኒ ፕሬዚዳንት አህመድ ሴኮ ቱሬ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ተደረገና አፍሪካውያን መለያየት እንደማይበጅና በአንድነት መቆም እንደሚሻል ተወያየንና ‹ኢትዮጵያና ጊኒ ቀጣዩ ስብሰባ የመላው አፍሪካውያን ስብሰባ እንዲሆን ተስማምተዋል› የጋራ መግለጫ አወጣን። በዚህ መሠረት ቡድኖቹን የማግባባት ሥራ እንድንሰራ ተስማማን፡፡ ለመሪዎቹ ሁሉ ደብዳቤ ተፃፈ፡፡ በወቅቱ የእኔ ልዩ ፀሐፊ ከነበሩት ከአቶ አያሌው ማንደፍሮ ጋር በመሆን የንጉሰ ነገሥቱን ደብዳቤዎች ይዘን በየአገራቱ ዞርን፡፡ ‹መሪዎቹ ምላሽ ሳይሰጡን ከተሞቹን አንለቅም› ብለን ወስነን ነበር፡፡ መሪዎቹም በአጭር ቀናት ውስጥ አዎንታዊ የሆነ ምላሽ ሰጡን፡፡ በመጨረሻም በግንቦት ወር 1955 ዓ.ም ጉባዔው ተካሄደና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተመሰረተ፡፡ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ካበረከተቻቸው አስተዋፅዖዎች መካከል አንዱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲቋቋም ያከናወነችው ተግባር ነው፡፡ ይህንን መካድ ታሪካችንን መካድ ነው፡፡»
የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለማቋቋም አምባሳደር ከተማ ይፍሩ ያበረከቱት አስተዋፅዖ በዋጋ የማይተመን፤በቃላት የማይገለፅ ነው፡፡ የሞኖሮቪያ እና የካዛብላንካ ቡድኖች አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችንና መሪዎችን ማነጋገርና ማሳመን በብዙ ውጣ ውረዶች የተሞላ እጅግ ፈታኝ ሥራ ነበር፤ምናልባትም ከአምባሳደር ከተማ በስተቀር ሌላ ሰው የሚያሳካው ተግባር አልነበረም፡፡ አምባሳደር ከተማ ግን ያን ከባድ ትዕግስት፣ ጥበብና ፅናት የሚፈልግ ተግባር በብቃት አልፈውታል፡፡
አምባሳደር ከተማ ከተማ በየሀገራቱ ሲዞሩ «ምላሽ ሳትሰጡኝ ከሀገራችሁ ለቅቄ አልሄድም፤ንጉሱም አያስገቡኝም» የሚሉ ማባበያዎችን ይጠቀሙ ነበር። የቱኒዝያው ፕሬዚዳንት «የሁለቱ ቡድኖች የጋራ አቋም ሳይኖር እንዴት አንድ ላይ እንሰበሰባለን?» የሚል የእምቢታ ምላሽ ሲሰጧቸው አምባሳደር ከተማ በምላሹ «አፄ ኃይለሥላሴ ያለእርስዎ ይህ ስብሰባ አይካሄድም ብለዋል» በማለት ነገሯቸው። በወቅቱ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የነበራቸው ተሰሚነትና ተፅዕኖ ከፍተኛ ስለነበርም የቱኒዚያው ፕሬዚዳንት በአምባሳደር ከተማ ሃሳብ ተስማምተው አዲስ አበባ ተገኙ፡፡
ከድርጅቱ ምስረታ ቀጥሎ የአፍሪካ ፖሊሲዎችን ማርቀቅ፣ «የድርጅቱ ፀሐፊ ማን ይሁን?» እንዲሁም «ዋና ጽሕፈት ቤቱ የት ይሁን?» የሚሉ ወሳኝ ጥያቄዎች ነበሩ። በአምባሳደር ከተማ አመራርነት ፖሊሲዎቹ ተዘጋጅተው ቀረቡ፤ በፖሊሲዎቹ ላይ አንዳንድ አለመስማማቶች ቢፈጠሩም ሰነዱ ተፈረመ። ከዚህ በተጨማሪም አምባሳደር ከተማ «ኢትዮጵያ የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት መቀመጫ ትሁን» የሚል ሀሳብ አቀረቡ። ጠንካራ ተቃውሞዎች ከብዙ አቅጣጫዎች ተደመጡ፡፡ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ አገራት «የሴኔጋሏ ዳካር ከተማ የድርጅቱ ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ እንድትሆን ተስማምተናል» አሉ። ናይጀሪያ በበኩሏ የድርጅቱ ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ የአገሬ አፈር ላይ መተከል አለበት ብላ አቋም ያዘች፡፡
ኢትዮጵያ ድርጅቱን ለመመስረት በብዙ ደክማ አመድ አፋሽ መሆኗ ንጉሰ ነገሥቱንና አምባሳደር ከተማን ቢያስደነግጣቸውም «ሙያ በልብ ነው» ብለው ኢትዮጵያ እንድትመረጥ የማግባባቱን ሥራ ጀመሩ። በወቅቱ «ኢትዮጵያን እንዳትመርጡ» የሚሉ የቴሌግራም መልዕክቶች ጭምር ይሰራጩ ነበር፡፡ በመጨረሻም ከብዙ ማግባባትና ክርክር በኋላ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ እንድትሆን አገራቱ (ከናይጀሪያ በስተቀር) ድምፃቸውን ሰጡ። በወቅቱ በድንበር ውዝግብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር አለመግባባት ውስጥ የነበረችው ሶማሊያ እንኳ ድጋፏን ለኢትዮጵያ እንደሰጠችና የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር «ኢትዮጵያን እንዳትመርጡ» ተብለው ከሌሎች አገራት የተላኩትን የቴሌግራም መልዕክቶች ለአምባሳደር ከተማ ያሳዩዋቸው እንደነበር ይነገራል፡፡
ከተማ በኔልሰን ማንዴላ ታሪክ ውስጥም አሻራ አላቸው፡፡ የማንዴላን የኢትዮጵያ ጉዞ ያሰናዱት አቶ ከተማ ነበሩ፡፡ ኔልሰን ማንዴላም ወደ ኢትዮጵያ በሄዱበት ወቅት ንጉሰ ነገሥቱና አምባሳደር ከተማ ስላደረጉላቸው ድጋፍ « … አዲስ አበባ ስደርስ መጀመሪያ ተቀብለው ያነጋገሩኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ከተማ ይፍሩ ነበሩ፡፡ ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልኝ፡፡ ከዚያም ኮልፌ ወደሚባለው አንድ የከተማው ክፍል ወሰዱኝ … » በማለት በመጽሐፋቸው ላይ ገልጸዋል፡፡ ማንዴላ ከኢትዮጵያ ተመልሰው በደቡብ አፍሪካው የአፓርታይድ መንግሥት ቁጥጥር ስር ሲውሉ በኪሳቸው ውስጥ የአምባሳደር ከተማ ፎቶ ተገኝቷል፡፡
ፓንአፍሪካኒስቱ ኢትዮጵያዊ አምባሳደር ከተማ ይፍሩ በመስከረም ወር 1954 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት በአስቸኳይ እንዲወገድና ሁሉም የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ገዢዎች ነፃ እንዲወጡ በአፅንዖት ጠይቀዋል። አፍሪካውያን ያለውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ችግሮቻቸውን በራሳቸው የመፍታት መብት እንዳላቸውም የድርጅቱን ቻርተር ድንጋጌዎች በመጥቀስ ተከራክረዋል፡፡
አምባሳደር ከተማ አራተኛው የምሥራቅ፣ የማዕከላዊና የደቡባዊ አፍሪካ ፓን አፍሪካ ነፃነት ጉባዔ አዲስ አበባ ላይ እንዲካሄድ ንጉሰ ነገሥቱን በማሳመን ኦሊቨር ታምቦ፣ ኔልሰን ማንዴላ፣ ሮበርት ሙጋቤ፣ ኬኔት ካውንዳ እና ሌሎች በርካታ ስመ ጥር የአፍሪካ ነፃነት ታጋዮች አዲስ አበባ መጥተው እንዲወያዩ ማድረግ ችለዋል፡፡ አምባሳደር ከተማ ኢትዮጵያን በመወከልና የኢትዮጵያን የልዑካን ቡድን በመምራት በበርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባዔዎች ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ከእነዚህም መካከል ከ1947 እስከ 1950 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እና በመጀመሪያው የአፍሮ-እስያ ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያ ልዑክ አባል፤ ከ1954 እስከ 1964 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እና የሊማ የቡድን 77 (Group of «77») አገራት ጉባዔ እንዲሁም በ1960 ዓ.ም ወደ ሶማሊያ የተጓዘው የኢትዮጵያ ልዑክ መሪ፤ ከ1955 እስከ 1963 ዓ.ም በአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉባዔ የኢትዮጵያ ልዑክ ሊቀ መንበር፣ የአራተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና ልማት ጉባዔ ስብሰባ የኢትዮጵያ ልዑክ መሪ እና የአፍሪካ ቀጣና ቃል አቀባይ ሆነው የተሳተፉባቸው ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባዔዎች በተጨማሪ የተሳተፉባቸው ሌሎች ብዙ መድረኮችም አሉ፡፡ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በተገኙባቸው የዓለም ክፍሎች ሁሉ አብረው በመጓዝ ኢትዮጵያን፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋንና ሌሎች መገለጫዎቿን አስተዋውቀዋል፤ከብዙ መሪዎች ጋር ተዋውቀዋል፤ መክረዋል፡፡
አምባሳደር ከተማ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ «ብሔራዊ ጥቅምን ያስከበረና ገለልተኛ የሆነ» እንዲሆን ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህ ጥረታቸውም ኢትዮጵያ በ1950ዎቹና 60ዎቹ ስኬታማ የሆነ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንዲኖራት እንዳስቻላት የአቶ ከተማ ልዩ ጸሐፊና የቅርብ ወዳጅ የነበሩት አምባሳደር አያሌው ማንደፍሮ በፃፉት ማስታወሻ ላይ ገልጸዋል፡፡ አቶ ከተማም በወቅቱ ከነበሩት የአፍሪካ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መካከል ግንባር ቀደሙና ተፅዕኖ ፈጣሪው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሆን ችለዋል፡፡
አምባሳደር ከተማ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት አገራቸውም ሆነ እርሳቸው ከሁሉም የዓለም አካባቢዎች ጋር ሰላማዊና በትብብር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲኖራቸው ደክመዋል፡፡ በአፍሪካ በተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥረው የነበሩ ግጭቶች እንዲበርዱና ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ጥረዋል፡፡ የኮንጎ ግጭት ያለውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እንዲፈታ ለፍተዋል፡፡ በመጨረሻም በኢትዮጵያዊው ሌተናል ጀኔራል ከበደ ገብሬ የተመራው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ኮንጎ እንዲሰማራ ተደርጓል፡፡
የአልጀሪያና የሞሮኮ ግጭት እንዲፈታ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረጉትም የአልጀሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር (በኋላ ፕሬዚዳንት) አብደልአዚዝ ቡተፍሊካ እና የሞሮኮው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ሬዳ ጉየዲራ የጋራ ወዳጅ የነበሩት፣ ከአልጀርስ-ራባት-አዲስ አበባ የተመላለሱትና ጥረታቸው በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆን ፊዝጌራልድ ኬኔዲ ጭምር የተደነቀላቸው ኢትዮጵያዊው አምባሳደር ከተማ ይፍሩ ናቸው፡፡
ከደቡባዊ ሱዳን ተፋላሚዎች ጋር በር ዘግተው መክረው በንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አማካኝነት አዲስ አበባ ላይ የሰላም ስምምነት እንዲፈራረሙም አድርገዋል። የናይጀሪያ መንግሥትና የቢያፍራ ተገንጣዮች ጦርነት ውስጥ በገቡበት ወቅት አምባሳደር ከተማ የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ጀኔራል ያኩቡ ጎዋን እና የቢያፍራው መሪ ኮሎኔል ኦድሜንጉ ኦጁኩ ወዳጅ ስለነበሩ መሪዎቹ አዲስ አበባ መጥተው እንዲወያዩና የግጭቱ ተጎጂዎች እርዳታ እንዲያገኙ የሚያስችል ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር የገባችበት የድንበር ግጭት ለጊዜውም ቢሆን እንዲፈታም ትልቅ ሚና ነበራቸው፡፡
አምባሳደር ከተማ ለአፍሪካ መሪዎች ይሰጡት የነበረው ምክር የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ተተኪ መሪዎችን በማፍራት ረገድ ስላለባቸው ድክመት አጥብቀው ይናገሩ ነበር፡፡ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ሲዘዋወሩ የመንግሥታቱን ሁኔታ ስለተገነዘቡ በወቅቱ በብዙ የአፍሪካ አገራት ዘንድ ሲስተዋል የነበረው ሥልጣንን በኃይል (በመፈንቅለ መንግሥት) የመንጠቅ ድርጊቶች ወደ ኢትዮጵያም መምጣታቸው ስለማይቀር ለንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ደብዳቤ ጽፈውላቸው ነበር፡፡ በደብዳቤያቸውም ንጉሰ ነገሥቱ ከወቅቱ ጋር የሚመጣጠን ሁለንተናዊ ለውጥ ማድረግ እንደሚገባቸው «ድፍረት በተሞላበት» አገላለፅ ገልጸውላዋቸዋል፡፡
ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከዙፋናቸው ተወግደው ዓመታት ካለፉ በኋላ አምባሳደር ከተማ « … የአፍሪካ የመጀመሪያዎቹ መሪዎች ትልቁ ችግር … በእኛም ላይ ደረሰ፡፡ መሪዎች በሥልጣን ላይ በሚቆዩበት ጊዜ ተተኪውን ሥርዓትና ሰው ሳያዘጋጁ ጊዜው ይደርስና አገራቱ ስጋት ላይ ይወድቃሉ፡፡ የዴሞክራሲን መርሆች መከተል ሲቻል፣ ሥልጣን የሰፊው ሕዝብ መሆኑ ሲታወቅና ሕዝብም መብቶቹን እያወቀ ሲሄድ ነው ወደ ሌላ መንግሥት በጤና መዛወር የምንችለው…» ብለው ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ንጉሰ ነገሥቱ የአምባሳደር ከተማን ምክር ከመስማት ይልቅ አምባሳደር ከተማን ከውጭ ጉዳይ ወደ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ቱሪዝም ሚኒስትርነት አዛወሯቸው። አምባሳደር ከተማ የገመቱት አልቀረም … ከደብዳቤው ሦስት ዓመታት በኋላ የ1966ቱ አብዮት መጥቶ ንጉሰ ነገሥቱን በላቸው፡፡
ወታደራዊው መንግሥት ሥልጣን ሲይዝ አምባሳደር ከተማ ታሰሩ፡፡ ከስምንት ዓመታት እስራት በኋላ ተፈቱ፡፡ ከዚያም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር፣ የአፍሪካ ቀጣና ልዩ አማካሪና ተወካይ ሆነው አገልግለዋል፡፡
አምባሳደር ከተማ በ1952 ዓ.ም ከወይዘሮ ራሔል ስነ ጊዮርጊስ ጋር ጋብቻ መስርተው አራት ልጆችን አፍርተዋል። ወይዘሮ ራሔል ስለባለቤታቸው ባህርይ ሲናገሩ ‹‹ … ከሁሉም ሰው መግባባት የሚያስችል ተፈጥሮ ያለው ሰው ነበር …›› ይላሉ፡፡ ልጃቸው አቶ መኮንን ከተማ ይፍሩ በበኩሉ ‹‹ … አባቴ የነበረበትን ማንነቱን አይረሳም፡፡ በሰው እኩልነት ያምናል …›› ብሏል፡፡
አምባሳደር ከተማ እጅግ ደማቅ ለሆኑት አኩሪ ተግባሮቻቸው የኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ አገራትን (የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የሶቪየት ኅብረት፣ የኢጣሊያ፣ የዩጎዝላቪያ፣ የሴኔጋል፣ የኬንያ፣ የናይጀሪያ፣ የጋና፣ የዛየር፣ የግብጽ፣ የብራዚል፣ የሜክሲኮ፣ የካናዳ፣ የጃፓን የኢንዶኔዥያ …) ኒሻኖችን ተሸልመዋል፡፡ አንጋፋ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገራት ዲፕሎማቶችም ስለአምባሳደር ከተማ አስደናቂ ተግባራት በተደጋጋሚ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
« … ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴና አቶ ከተማ ይፍሩ በሁለቱ ጎራ ተሰልፈው የነበሩ መሪዎችን በማግባባት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እውን እንዲሆን አደርገዋል …» የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ
«… አቶ ከተማ ይፍሩን ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ታሪክ መለየት አይቻልም፡፡ በጣም ብዙ ደክመዋል። የአፍሪካ መሪዎች በጃንሆይ ሰብሳቢነት ሲሰባሰቡ ጀምሮ መሪዎችን በማነጋገርና በማግባባት ከፍተኛ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ የሞኖሮቪያና የካዛብላንካ ቡድኖች ተፈጥረው የሃሳብ ልዩነት በነበረበት ወቅት አምባሳደር ከተማ በየአገራቱ እየዞሩ ከመከፋፈል ይልቅ አንድነት እንደሚሻልና የቡድኖቹን ሃሳቦች በውይይት መፍታት እንደሚቻል ያስረዱ ነበር፡፡ በጣም ወደ ግራ ያዘነበሉ የአፍሪካ መሪዎችንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን በማግባባት ያበረከቱት አስተዋፅዖ እጅግ ከፍተኛ ነበር ።» አንጋፋው ጋዜጠኛ፣ የታሪክ ጸሐፊና ዲፕሎማት አምባሳደር ዘውዴ ረታ
«… አምባሳደር ከተማ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ «ብሔራዊ ጥቅምን ያስከበረና ገለልተኛ የሆነ» እንዲሆን ብዙ ጥረት አድርገዋል … ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መካከል የአፍሪካ የነፃነት ታጋዮችን በመደገፍና ወደ ነፃነት የሚያደርሱ መንገዶችን በማመቻቸት እንደአምባሳደር ከተማ ይፍሩ ታላላቅ ተግባራትን ያከናወነ ሰው የለም …» የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትርና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አያሌው ማንደፍሮ
አምባሳደር ከተማ ጥር 6 ቀን 1986 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ በኑዛዜያቸውም የሚከተለውን መልዕክት አስቀምጠው አልፈዋል …
«በራሴ በኩል አገሬን በንጹህ ልቦና አቅሜና የጊዜው ሁኔታ በሚፈቅደው መጠን ከማገልገል በስተቀር የፈፀምኩት ወይም ያደረስኩት አንዳችም በደል ያለመኖሩን ስለማምንና ስለማውቅ ምንጊዜም ቢሆን ህሊናዬ ፍጹም ንጹህ ነው። የፈፀምኩት በደል ቢኖር ከተራ ገበሬ ቤተሰብ ተወልጄ በችሎታዬና በድካሜ ተወዳድሬ በቁጥር አነስተኛ በሆኑ ክፍሎች በሞኖፖል ተይዞ ለነበረው ከፍተኛ የሥራ ቦታ ራሴን ብቁ አድርጌ መገኘቴ ብቻ ነው፡፡ የእኔ ወንጀል ኢትዮጵያ አገሬ በሰጠችኝ ዕድል ተጠቅሜ የእኔ ብጤ፣ ከድሃ ቤተሰብ የሚወለድ ዕድሉ ከተሰጠው ከማንም የማያንስ መሆኑን በሥራ ማስመስከሬ ብቻ ነው፡፡ ሥራ ላይ በነበርኩበት ዘመን በተለይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበርኩበት ጊዜ የፈጸምኳቸው ሥራዎች በተለይ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረትና ዋናው መስሪያ ቤት አዲስ አበባ ላይ እንዲሆን ያደረግሁት ለኔ ምንጊዜም የሚያንጸባርቅና ሐውልት ስለሆነ ለባለቤቴንም ለልጆቼም የሚያኮራቸው ነው፡፡»
ከኢትዮጵያ አልፈው ለአፍሪካ ጭምር ኩራትና ባለውለታ ለሆኑት ለአምባሳደር ከተማ ይፍሩ ስም መታወሻ የሚሆን ተግባር ኢትዮጵያ ውስጥ አለመከናወኑ ብዙዎችን አስገርሟል፤አሳዝኗልም፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 20/2012
Filed in: Amharic