>

ከድሬዳዋ-ጅጅጋ የጉዞ ገጠመኝ!!! (ውብሸት ሙላት)

ከድሬዳዋ-ጅጅጋ የጉዞ ገጠመኝ!!!

ውብሸት ሙላት
*አለማያ ከተማ መግቢያ ላይ ቄሮዎቹ “አማራ እንፈልጋለን አውርዱልን” ብለው ከሹፌሩና ረዳቱ ጋር ትልቅ ግብግብ ቢፈጥሩም፣ ሹፌሩ እግዚአብሔር ይባርከው እና “አንድም አማራ አልያዝኩም፣ ኦሮሞና ሱማሌ ብቻ ነው ብሎ በድንጋይ የመኪናውን ጎን እየመቱ እየሸመጠጠ አለፈ….!
ዛሬ (ጥር 21፣ 2012 ዓ.ም.)  ከድሬዳዋ ጅጅጋ እየተጓዝኩ ነበር። መንገድ ላይ ስጋቶች እንዳሉ ባውቅም ኦሮምኛን  በደንብ ስለምችል በዚያው በመተማመን   መንገድ ገባሁ። በተለምዶ ቅጥቅጥ አይሱዙ የሚባለውን ባለ 24 ሰው ጫኝ መኪና በእጥፍ ታሪፍ (150 ብር ከፍለን ተሳፈርን። በትላንትናው እለት “አራት ጥፍ ግድም (300  ብር) ከፍዬ ከጅጅጋ ድሬዳዋ መጣሁ” ብሎ ነገረኝ አንድ አጠገቤ የተቀመጠ ሱማልኛ ተናጋሪ ተሳፋሪ። ትላንት በማህበራዊ ሚድያ እንደታየውም አብዛኛው የምስራቅ ሐረርጌ መንገዶች ዝግ ነበሩ በእርግጥ። ጎማዎችም ሲቃጠሉም ነበር። ይህ አመጽ በደንብ የተደራጀ ባይሆንም “ወለጋ ላይ መንግስት ህዝባችንን እየጎዳ ስለሆነ የ፫ ቀን የስራ ማቆም አድማ እናድርግ የሚሉ ቅስቀሳዎች ነበሩ።
እናም፣ በጉዞአችን ላይ፣ ደንገጎ አካባቢ (ከድሬዳዋ 18KM) ሶስት ኦሮምኛ የማይናገሩ ክርስቲያኖች  ፈርተው ወረዱ። አማርኛ ተናጋሪ ለጥቃት ይጋለጣል የሚል መረጃ ስላገኙ።
ከዚያ  አዴሌ እና ደንገጎ መሃል፣ አዴሌ ከተማ እንዲሁም አለማያ ከተማ መግቢያ ላይ ቄሮዎቹ “አማራ እንፈልጋለን አውርዱልን” ብለው ከሹፌሩና ረዳቱ ጋር ትልቅ ግብግብ ቢፈጥሩም፣ ሹፌሩ እግዚአብሔር ይባርከው እና “አንድም አማራ አልያዝኩም፣ ኦሮሞና ሱማሌ ብቻ ነው ብሎ በድንጋይ የመኪናውን ጎን እየመቱ እየሸመጠጠ አለፈ። እንደረረዳሁት ሹፌሩ የአካባቢው ተወላጅ መሰለኝ።
ከዚያም አወዳይ አካባቢ ወጣቶች ተደብቀው ድንጋይ ወርውረው መኪናውን መቱት። በተለይ አለማያ ምንም እንቅስቃሴ የለም። ሁሉ ቢዝነስ ዝግ ነው። አወዳይ የተወሰነ እንቅስቃሴ ቢኖርም ተለቅ ተለቅ ያሉ ቢዝነሶች እና ማንኛውም ባንኮች ዝግ ናቸው። በተለይ የጭነት መኪኖች አልፎ አልፎ ውር ውር ይላሉ። መከላከያ በፒካፕ አልፎ አልፎ ሲያልፍ ይታያል። የኦሮሚያ ፖሊስ ጥግ ይዞ ከወጣቶች ጋር ሲሳሳቅ ይታያል። በብዛትም ትጥቅ አልያዙም የኦሮሚያ ፖሊሶች።
የገጠመን ነገር በጣም ያሳዝናል። አማራን ወይም አማርኛ ብቻ ተናጋሪን እንዲህ ለትርጉም አልባ-ጥቃት ማሳደድ። ምንም እንደሚጠቅማቸው ግልጽ አይደለም። ሱማሌ ተወላጆች በዚህ ጉዳይ እንዴት ሲያዝኑ እንደነበር አይቻለሁ። ባቢሌን ከተሻገርን በኋላ በዚህ አሳፋሪ የጭፍን ጥላቻ ጉዳይ ላይ በግልጽ በሃዘን መንፈስ ሲወያዩ አይቻለሁ። (የወዳጄ የዛሬ የሐዘን ትዝብት!)
Filed in: Amharic