>
5:13 pm - Wednesday April 18, 9759

ከጸሎት ሁሉ የሚመቸኝ: '...ሕዝብን አድን፣ እርስትህንም ባርክ'!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ከጸሎት ሁሉ የሚመቸኝ: ‘…ሕዝብን አድን፣ እርስትህንም ባርክ’!!!

 

ያሬድ ሀይለማርያም
ከልጅነቴ ጀምሮ ለምን እንደሆነ አላውቅም ይቺ የረጅም ጸሎት ዝንጣፊ ከልቤ ውስጥ ተሰንቅራ ደጋግማ ወደ አዕምሮዬ ትመጣለች። አንዳንዴም ጸሎት ላይ ሰነፍ ብሆንም ብቸኛ የጸሎት ቃሌ ትሆናለች። አዎ ‘…ሕዝብን አድን፣ እርስትህንም ባርክ’ እራሱን የቻለ፣ ጥልቅ ትርጉም ያለው፣ ትልቅ ጸሎት።
ስርዓት አልበኝነት ሲነግስ፣ ዜጎች በሰላም ከቤታቸው ወጥተው በሰላም መመለስ ሲሳናቸው፣ ወገን በወገኑ ላይ አቂሞ አንዱ ሌላውን ሊያጠፋ በአደባባይ ሲዛዛት፣ የአንድ አገር ህዝብ በብሔር  አራሱን እያቧደነና ሌላውን እያገለለ በተዘጋጀለተ የልዩነት ስልቻዎች ውስጥ ጓዙን ሰትሮ በገባበት፣ ሰው በማንነቱ በሚሳደድበት፣ አንደ እባብ ተቀጥቅጦ በሚገደልበት፣ በአደባባይ ተዘቀዝቆ በሚሰቀልበት፣ ተማሪ ከፎቅ በሚወረወርበት፣ ልጆች ከትምርት ገበታቸው ላይ ታፍነው ተወስደው ለወራት የደረሱበት የማይታወቅበት፣ ሰው ባገሩ አገር አይደለም ተብሎ በሚፈናቀልበት፣ የድሀ ገበሬ ልጅ አፍኖ ወስዶ በመቶ ሺዎች ገንዘብ የሚጠየቅበት፣ ከመቶ በላይ የፖለቲካ ድርጅት በየጎራው በሚያቅራራበትና እኔ ብቻ  ልቅደም እያለ ሚደነፋበት፣ መንግሥት ሕግና ሥርዓት ማስከበር ተስኖት ሕዝብ በመንጋዎች በሚዋከብበት አገር ላይ የጠዋትና የማታ ጸሎትህ የጠየኩኸን ሌላ ነገር ሁሉ ተወውና ‘…ሕዝብን አድን፣ እርስትህንም ባርክ’ ቢሆን ምን ይደንቃል?
እውነት ነው አንዳንዱን ነገር ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም። መጥፎ እና አንባገነናዊ ሥርዓትን ታግሎ  መለወጥ ይቻላል። በዛሬዋ ኢትዮጵያ ግን እኛ ዘንድ ያሉት ችግርች ከዛም ያለፉ እና ውላቸውም ያልታወቀ ነው።
‘…ሕዝብን አድን፣ እርስትህንም ባርክ’ ማለት ይሄኔ ነው።
መልካም የሥራ ሳምንት!!
Filed in: Amharic