ምርጫው እርግማን እንዳይሆንብን …!!!
ደሴት ኢትዮፕ
አገሪቷ ከብዙ ተግዳሮቶች ጋር ትንቅንቅ ላይ ነች ። መንግስት በእግሩ ለመቆም እንዳይችል ተግዳሮቶቹ ፋታ ነስተዉታል ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለም ምርጫ ቦርድ የምርጫውን ቀን ቆርጧል ። ነሐሴ 23/2012 ዓ/ም…..
.
ምርጫው ቀን ቢቆረጥለትም …. የፖለቲካ ፓርቲዎች የፈለጋቸው ቦታ ሄደው ፕሮግራሞቻቸውን ለሕዝብ ተደራሽ የሚያደርጉበት መንገድ ዝግ ነው ማለት የቻላል ። እንቅስቃሴያቸው በሕግ ሳይሆን ” ክልሉ የኔ ነው ” በሚሉ የጅምላ ፍርደኞች የተገደበ ነው ። ከሁለትና ከ3 ፓርቲዎች ውጪ የምርጫን ቦርድ የምዝገባ ደንብ አሟልተው የምስክር ወረቀት ያገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንኳ የሉም ።
.
በብዙ ቦታዎች የተረጋጋ ሁኔታ የለም ። አንዳንድ አካባቢዎችም ከአመፀኞች እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ናቸው ። በተለያየ ምክንያት የሚቆራቆዙ ክልሎችም አሉ ። የፌዴራል መንግስቱን እንኳ ” ድርሽ እንዳትልብን ” በማለት እንደ ጎረቤት አገር ወሰናቸውን አጥረው የተቀመጡም እንደዚሁ ። ብልጭ ድርግም እያሉ እዚህም እዚያ የሚለኮሱ ግጭቶች ብዙዎች ናቸው ። የምርጫውን ሒደት ለቆሙለት ክልል ፍላጎት ለማዋል አቅም ያለቸው ፤ ወገንትኝነታቸውም ለክልላቸው የሆኑ ሰራዊቶች በየክልሉ ተደራጅተዋል ። እነዚህም ለምርጫው ተግዳሮት ሊሆኑ እንደማይችሉ ዋስትና የለም ። የክልል የፀጥታ አካሎች እንኳን ምርጫን ለመሰለ ወሳኝ የስልጣን ጉዳይ ይቅርና በእያንዳንዱ የመንደር ጉዳይ ላይ ወገንተኝነታቸው በተደጋጋሚ አረጋግጠውልናል ። በመከባበር ይስተናገዱ /ይከበሩ / የነበሩ ሐማኖታዊ በአላትን እንኳ ለማክበር የታየው ውጥረትና ግጭት ምን ያህል እንደነበረ ታይቷል ። በነዚህ በአላት ላይ እንኳ የየክልሉ የፀጥታ አካላትም ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ሲገባ አስተውለናል ። በአላቶቹን ተንተርሰው የተፈናቀሉ የተጎዱ ፣ የተዘረፉ ዜጎችም ነበሩ ፤ ጭራሹኑ እንደ አርባ ጉጉ ባሉ ቦታዎች ምእመኖች ጥምቀትን ማክበር አልቻሉም ። ወንጀለኞች ” ብሔሬ ነው ” በሚሉት ክልሉ ውስጥ በአስደንጋጭ ሁኔታ እንደጀግና ይወደሳሉ ። በወንጀል የተጠረጠሩም ግለሰቦች ክልሎች አሳልፈው አይሰጡም ። ፌዴራሉም አስገድዶ የሚይዝበትና ለፍትህ የሚያቀርብበት ጥንካሬው ደካማ ነው ። ባጠቃላይ ክልሎች ከመከላከያ ያልተናነሰ ሬንጀር የለበሰ ፣ ከዘመናዊ የነፍስ ወከፍ አስከ ቡድን የጦ/መሳሪያ የታጠቀ ፣ አንዳንዶቹ ክልሎች የተሻለ የመከላከያ አደረጃጀት ካላቸው የፍሪካ አገሮች እንኳ የላቀ አስከ 100 ሺህ ሰራዊት ያላቸው ናቸው ። እነዚህም ፍፁም በሆነ መዋቅር ለክላቸው መንግስት ተጠሪ የሆኑ ናቸው ። ከዚህ ጋር ተያይዞ በክልሎች ውስጥ የምርጫው ፍትሐዊነት ላይ ችግር ቢፈጠር እንኳ የፌዴራል የፀጥታ ሰራዊት መግባት አይችልም ፤ የፌዴራል ፖሊስም ሆነ መከላከያ መግባት የሚችለው ክልሎች ሲፈቅዱ ብቻ ነው ። ይህ የሕገመንግስቱ ድንጋጌ ነው ።
.
የምርጫው ጉዳይ የምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ያለቀለት መስሎ ቢታይም ፤ አሁንም ስለስጋቶቹ መጮህ ያስፈልጋል ። እንዲህ ባለ ወጀብና ለምርጫም ምቾት በሌለበት ሁኔታ ምርጫን ለማድረግ መወሰን ለግጭት በር መክፈት ነው ። ይህ ምርጫ ግጭታችንን ለሚፈልጉና በግጭታችንም አጀንዳቸውን ሊዘረጉ ለሚቋምጡ ታሪካዊ ጠላቶቻችን የሰርግና ምላሽ መድረክ ማመቻቸት እንዳይሆን ሁሉም አካል በጥልቀት ሊያስብበት ይገባል ። ምርጫው በረከት ሳይሆን እርግማን ይዞብን እንዳይመጣ ሁላችንም ዜጎች የበኩላችንንና የሚበጀውን ሐሳብ በመሰንዘር መንግስት ላይ ጫና መፍጠር ይገባናል ። ” አገር አስኪረጋጋ ፣ የመንግስት ቁመናም ስርአተ አልበኞችን አደብ ለማስገዛት በሚችልበት ሁኔታ ላይ እስኪገኝ ምርጫው ይዘግይልን ” የሚል ጥሪ እናሰማ ።